በቶኪዮ ጎዳናዎች

በቶኪዮ ጎዳናዎች

በአንዱዓለም ሰለሞን

በሩጫ ውድድር ረጅም ርቀት የሚሸፍነው የማራቶን ውድድር በዓለም ላይ ተወዳጅ ከሆኑ የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ የሀገራችንን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ውድድሮች ዝናን አትርፈው፣ ስፖርቱ ተወዳጅ እንዲሆን ምክንያት ሆነዋል፡፡

ይህ ብርታት፣ ጥንካሬና ጽናትን የሚጠይቀው ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተቸረው ነው፡፡ እንደ ኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባሻገር፣ በ6 ታላላቅ ከተሞች፣ በስፖርቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚደረጉ ሲሆን በርሊን፣ ቦስተን፣ ቺካጎ፣ ለንደን፣ ኒውዮርክ እና ቶኪዮ ደግሞ ውድድሩ የሚካሔድባቸው ከተሞች ናቸው፡፡

በየዓመቱ በወርሀ የካቲት የሚደረገው የቶኪዮ ማራቶን ሰሞኑን በከተማዋ ተካሂዷል። በዓለም ዝነኛ ከሆኑት የማራቶን ውድድሮች ሁሉ ረጅም ጊዜን ያላስቆጠረው ይህ ውድድር፣ በ2007 ነበር የተመሰረተው፡፡ በወቅቱም 26 ሺህ 058 ሯጮች በውድድሩ ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በመጀመሪያው የቶኪዮ ማራቶን፣ በወንዶቹ ኬንያዊው ዳንኤል ንጄንጋ፣ በሴቶቹ ደግሞ ጃፓናዊቷ ኒያ ሂቶሚ አሸናፊዎች ሆነዋል፤ ውድድሩን 2:9:45 እና 2:31:01 በመፈጸም፡፡

በቀጣዩ ዓመት ድሉ በሁለቱም ጾታ ለአውሮፓዊያን ሆነ፡፡ በወንዶቹ ሲውዘርላንዳዊው ቪክቶር ሮትህሊን፣ በሴቶቹ ጀርመናዊቷ ካሉዲያ ድሬሄር አሸናፊ ሆኑ፡፡

በቀጣዩ ውድድር አሸናፊዎቹ እንደ መጀመሪያው ውድድር ሁሉ የኬንያ እና የጃፓን አትሌቶች ነበሩ፤  በወንዶቹ ሳሊም ኪፕሳንግ፣ በሴቶቹ ደግሞ ናሱካዋ ሚዙሆ፡፡

በ2010፣ በወንዶቹ ፉጂዋራ ማሳካዙ ከጃፓን፣ በሴቶቹ አሌቭቲና ቢክቲሚሮቫ ከሩሲያ የውድድሩ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡

በ2011 የኢትዮጵያን ስም ባሸናፊነት ያስጠራ አትሌት ብቅ አለ – ውድድሩን 2:7:35 በማጠናቀቅ ያሸነፈው ሀይሉ መኮንን፡፡ በሴቶቹ ምድብ በተካሄደው ወድድር ደግሞ፣ ጃፓናዊቷ ሂጉቺ ኖሪኮ ባለ ድል ሆነች፡፡

ከ2012 ጀምሮ ግን ውድድሩን የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በበላይነት ተቆጣጠሩት። በዚህ ዓመት በተደረገው ውድድር በወንዶቹ ኬንያዊው ሚካኤል ኪፕኤጎ ሲያሸንፍ፣ በሴቶቹ አጸደ ሀብታሙ ባለድል ሆናለች፡፡

በ2013፣ በወንዶቹ ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ፣ በሴቶቹ ኢትዮጵያዊቷ አበሩ ከበደ ሲያሸንፉ፤ በቀጣዩ ዓመት በተደረገው ውድድር ደግሞ፣ በወንዶቹ ኬንያዊው ዲክሰን ቹሙባ፣ በሴቶቹ ትርፌ ጸጋዬ ባለድል ሆነዋል፡፡

በ2015፣ በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ማሸነፍ ችለዋል፤ በወንዶቹ እንደሻው ነገሰ እና በሴቶቹ ብርሀኔ ዲባባ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በወንዶቹ ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሌሊሳ፣ በሴቶቹ ሄላህ ኪፕሮፕ ውድድሩን በቀዳሚነት አጠናቀዋል፡፡

በ2017፣ ኬንያዊያኑ በሁለቱም ጾታ ማሸነፍ ችለዋል፤ በወንዶቹ በዊልሰን ኪፕሳንግ እና በሴቶቹ ሳራ ቸብቺርችር፡፡

በ2018፣ በወንዶች ኬንያ በዲክሰን ቹምባ፣ በሴቶች ኢትዮጵያ በብርሀኔ ዲባባ አማካኝነት ባለ ድል ሆነዋል፡፡

በ2019፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ልክ እንደ 2015 ሁሉ በሁለቱም ጾታ ባለድል መሆን ችለዋል፤ በወንዶች ብርሀኑ ለገሰ፣ በሴቶች፣ ሩቲ አጋ ቀዳሚ ሆነው ውድድሩን በማጠናቀቅ፡፡

በ2020፣ በወንዶቹ ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሀኑ ለገሰ የቀድሞ ክብሩን አስጠብቆ ዳግም ለድል ሲበቃ፣ በሴቶቹ እስራኤላዊቷ ሎናህ ቼማቲ ሳለፕተር አሸናፊ ሆናለች፡፡

በ2021፣ ኬንያዊያኑ በወንድም በሴትም በማሸነፍ የ2017ቱን ድርብ ድል ደግመውታል። በወንዶቹ ኢልውድ ኪፕቾጌ፣ በሴቶቹ ደግሞ ብሪጅድ ኮስጌ የውድድሩ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡

በ2023፣ በወንዶቹ ደሶ ገልሚሳ ከኢትዮጵያ፣ በሴቶቹ ሮዝማሪ ዋንጅሩ ከኬንያ ሲያሸንፉ፤ በ2024 ድግሞ፣ በወንዶቹ ኬንያዊው ቤንሶ ኪፕሩቶ፣ በሴቶቹ ሲቱኡሜ ከበደ ከኢትዮጵያ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በ2025ቱ የዘንድሮ የቶኪዮ ማራቶን ደግሞ በወንዶቹም ሆነ በሴቶቹ ምድብ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ 3 ጊዜ በሁለቱም ጾታ እንድታሸንፍና ባለድርብ ድል እንድትሆን አስችሏታል፡፡

በወንዶቹ፣ ውድድሩን 2:3:23 የፈጸመው አትሌት ታደሰ ተክሌ፣ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ችሏል፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 4 ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት ከተፎካካሪዎቹ ተነጥሎ የወጣው አትሌቱ፣ በዚህ ውድድር ሲያሸንፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡

“የዓየር ጸባዩ በጣም ሞቃታማ ቢሆንም ችግር አልፈጠረብኝም፣ ለኔ ተመችቶኝ ነበር” በማለት ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን የሰጠው አትሌቱ፣ በዚህም መደሰቱንና በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ሰዓት ውድድሩን የማጠናቀቅ ሀሳብ እንዳለው መግለጹን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡

ውድድሩን 2:03:51 በሆነ ሰዓት ያጠናቀቀው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደረሳ ገለታ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃን ሲያገኝ፣ ኬንያዊው ቪሰንት ኪፕኬሞይ ደግሞ 2:04:00 በመግባት ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል፡፡

በሴቶቹ ምድብ በተካሔደ ውድድር፣ ኢትዮጵያዊቷ ሲቱ ኡሜ ከበደ 2:16:31 በመግባት አሸንፋለች፡፡ ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው አትሌቷ፣ የአሁኑ ድሏ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ይህም በእስከ አሁኑ የውድድሩ ታሪክ በተከታታይ ያሸነፈች መጀመሪያዋ ሴት አትሌት አሰኝቷታል፡፡

ከውድድሩ አስቀድሞ፣ “ማራቶን ለእኔ አዲስ ምዕራፍ ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቶ የነበረው የ5 እና የ10 ሺህ ሜትር የክብረ ወሰን ባለቤቱ ዑጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጌ፣ ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፤ 2:5:59 በመግባት፡፡ አትሌቱ በ2023 በቫሌንሺያ ካደረገው የማራቶን ውድድር በኋላ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተሳተፈበት የውድድር መድረክ ነው፡፡ የአምናው የውድድሩ አሸናፊ፣ ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ደግሞ 2:05:46 በመግባት ስድስተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል፡፡

በዘንድሮው የቶኪዮ ማራቶን ከታዩ አስደናቂ ክስተቶች መካከል የቀድሞዋ የዓለም የክብረ ወሰን ባለቤት እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ከ10 ዓመት በኋላ በተሳተፈችበት በዚህ ውድድር 2:57:26 በመግባት ውድድሩን ማጠናቀቋ ነው፡፡

አትሌቷ በቀጣይ በቦስተን በሚካሔደው የማራቶን ውድድርም እንደምትሳተፍ የገለጸች ሲሆን፣ በሌሎቹ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ የመሳተፍና ሀሳብ እንዳላትም ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች የበላይነታቸውን ባሳዩበት በዚህ ውድድር፣ እስከ አሁን ኢትዮጵያ በወንዶች 7፣ በሴቶች 8፣ በአጠቃላይ 15 ጊዜ ስታሸንፍ፣ ኬንያ በአንጻሩ፣ በወንዶች 9፣ በሴቶች 4 በአጠቃላይ 13 ጊዜ ባለ ድል ሆናለች፡፡

የውድድሩን ክብረ ወሰን በተመለከተም ሪከርዱ ከሁለቱ ሀገራት አትሌቶች አልወጣም። በወንዶቹ ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ በ2024 ሲያሸንፍ የገባበት ሰዓት (2:02:16) በክብረ ወሰንነት ተመዝግቧል፡፡ ይህ ሰዓትም በሀገሩ ልጅ ኢልውድ ኪፕቾጌ በ2022 የተያዘውን ሪከርድ (2:02:40) ያሻሻለበት ነው፡፡

በሴቶቹ፣ ኢትዮጵያዊቷ ሲቱኡሜ አሰፋ በ2024 በተካሄደው ውድድር 2:15:55 በመግባት ስታሸንፍ የክብረ ወሰኑ ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት አስቀድማ ሪከርዱን ይዛ የነበረችው ኬንያዊቷ ብሪጅ ኮስጌ ስትሆን፣ በ2021 በውድድሩ ስታሸንፍ 2:16:02 በመግባት ነበር፡፡

(በጽሁፉ የተጠቀሱት ጊዜያት በሙሉ እ.ኤ.አ ናቸው)