በገነት ደጉ
አካል ጉዳተኞች በተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ሳይሆኑ የቀሩበት ጊዜ ቀርቶ ዛሬ ዛሬ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረላቸው በሕይወታቸው ተጽዕኖ እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ በዚህም የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡
ስለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ሲነሳ በተለይም ማየት የተሳናቸው ወገኖች ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ይበልጥ በሚፈጠረው የተግባቦች ችግር ምክንያት አገልግሎት ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡
የዛሬዋ የችያለሁ ዓምድ ባለተሞክሮ እነዚህን መሰል ችግሮችንና ከሴትነት ጋር ተያይዞ ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ተሻግራ በስኬት ማማ ላይ ደርሳ አርዓያነቷን ያስመሰከረች ናት፡፡
መምህር ቃልኪዳን መንክር ትባላለች። ትውልድና እድገቷ በሀገራችን መዲና አዲስ አበባ ልዩ ስሙ በተለምዶ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀጨኔ መድሀኒዓለም በሚባልበት አካባቢ ነው፡፡
ቤተሰቦቿ እንደነገሯት በልጅነት ዕድሜዋ በጤንነት ከተወለደች በኋላ ቀስ በቀስ ሁለቱም ዓኖቿ ማየት እየቀነሱ በሂደት ሙሉ ለሙሉ ማየት እንዳልቻሉ ነው የምትናገረው፡፡
ቤተሰቦቿ በወቅቱ ያልደረሱበት የህክምና ቦታ እና በእምነትም ወደ ተለያዩ የፀበል ቦታዎች ፈውስን ፈልገው እንደወሰዷት ያጫወተችን መምህር ቃልኪዳን፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ መስተካከልና ዓይኖቿ ማየት እንደማይችሉ በዶክተሮች እንደተነገራት ነው ያስረዳችን፡፡
በወቅቱም አዲስ አበባ ላይ ማየት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ወደ ሻሸመኔ መምጣት ግድ ሆኖባት በዚያ በሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባች፡፡
በዚሁ በሻሸመኔ በሚገኘው ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በአምስት ዓመቷ ተቀላቅላ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ ከስድስተኛ ክፍል ወደ 7ኛ ክፍል ስትዛወርም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች።
በኋላም ለትምህርት ጽኑ ጥማት ስለነበራት ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በአዲስ አበባ አጼ ልብነድንግል ትምህርት ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ በደብረ ሰላም ትምህርት ቤት፣ 11ኛ ክፍል በእቴጌመነን እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በአጼ ምኒልክ ትምህርት ቤት በመከታተል በ2008 ዓ.ም ትምህርቷን አጠናቀቀች፡፡
በመቀጠልም በ2009 ዓ.ም ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመቀላቀል በኢጁኬሽናል ፕላኒንግ ኤንድ ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታ በ2011 ዓ.ም ለመመረቅ በቃች፡፡ ትምህርቷንም ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ከ3 ነጥብ 7 ሳትወርድ በጥሩ ውጤት ነው ያጠናቀቀችው።
“እኔ አካል ጉዳተኝነት ምንም ማለት አይደለም ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ችግሩን ከተቀበልኩ በኋላ በምን ዓይነት መንገድ አስተናገድኩት የሚለው ነው ትልቁ ቁም ነገር፡፡ አብዛኛውን ዕድሜዬን በትምህርት ስለጨረስኩ አካል ጉዳት ፈታኝም ከባድም መሆኑን አይቻለሁ።
“እስከ ስድስተኛ ክፍል ስማር ልጅ ስለነበርኩ አካል ጉዳተኝነት ምንም ማለት አይደለም ከሚሉት ወገን ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ጉዳቴን አላስታውሰውም ነበር፡፡ አካል ጉዳተኝነት እንዲሰማሽም እንዳይሰማሽም የሚያደርገው የአካባቢው ሁኔታ ነው፡፡
“በወቅቱ አዳሪ ትምህርት ቤት ለእኛ ብቻ ተብሎ የተስተካከለ ስለነበር ምንም አይመስለንም ነበር፡፡ እንደፈለግን ነበር የምንሆነው፡፡ ምንም ዓይነት እክል አይገጥመንም ነበር፡፡ ለዚያም ነበር ምንም ማለት አይደለም ብለን የተቀበልነው፡፡ መጻህፍቱ በብሬል ስለነበሩ እገሌ ያንብብልን ብለን የምንቸገረው ነገር አልነበረም፡፡ የማንም እገዛም አያስፈልገንም ነበር፡፡
“ከአዳሪ ትምህርት ቤት ተለይቼ 7ኛ ክፍል እንደገባሁ ግን አካል ጉዳት በሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ተረዳሁ፡፡ ነገር ግን ተረዳሁ ማለት በዚያ ተጽዕኖ ምክንያት ወደ ኋላ ቀረሁ ማለት አይደለም፡፡ ችግሩ በሕይወቴ ምን ዓይነት ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ግን መረዳቴ አልቀረም፡፡ ያንን ከተረዳሁ በኋላ የገጠመኝን ችግር ለመሻገር ብልሀት አብሮ እንደሚያስፈልግ ገባኝ፡፡
“ልክ ሰባተኛ ክፍል ስገባ እኔ የለመድኩት በብሬል ነበር፡፡ የፊቴንና የዓይኔን ገጽታ እየተመለከቱ ብዙ ሰዎች ዓይነ ስውር አልመልሳቸውም ነበር፡፡ በወቅቱም ጉዳቱ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ብዙም ስለማልረዳው ለማንኛውም ሰው ምላሽ ከምሰጥ ይልቅ እከፋ ነበር፡፡” በማለት በትምህርቷ አካል ጉዳተኝነት ያመጣውን ተጽዕኖ ታስታውሳለች፡፡
ጉዳቴን ያስተናገድኩት ባልበሰልኩበት ወቅት ነው ያለችን መምህርት ቃልኪዳን፣ ቤተሰቦቿ በተለይም እናቷ ዛሬ እዚህ ደረጃ እንድትደርስ ትልቁን ዋጋ እንደከፈሉላት ነው ያጫወተችን፡፡
“ባሳለፍኳቸው ወቅቶች ሁሉ ራሴን እንድችል ያደረገኝ በትምህርቴ ጎበዝ ተማሪ መሆኔ ነበር፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ራስን ለማሻገር እና የገጠሙንን ተግዳሮቶች አሸንፎ ለመውጣት መማር ወሳኝ ነው፡፡
“በየትኛውም መንገድ ጠንክረን ከሰራን ሰዎችን መሳብ እንችላለን፡፡ በዚህም በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን ጎበዝ በመሆን ማቅረብ የቻልኩ ሲሆን እኔም ጥንካሬዬ እንደጠቀመኝ በመረዳቴ በዚያ መንገድ ራሴን እያሳደግኩ መጥቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ ያሳለፉኳቸው ጎዳናዎቼ ዛሬ ላይ እንድደርስ መልካም አጋጣሚዎችን ፈጥረውልኛል፡፡” ስትል በሕይወቷ የገጠሟትን ፈተናዎች በጥንካሬ ያለፈችበትን መንገድ አስታውሳለች፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ እየሰራች ያለችው መምህር ቃልኪዳን፣ የትምህርት ዕድል አግኝታ የሁለተኛ ድግሪ ትምህርቷን እዛው በኢጁኬሽናል ፕላኒንግ ኤንድ ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ተከታትላ በጥሩ ውጤት በ2014 ዓ.ም መመረቋን አጫውታናለች፡፡
ሕይወቷን በጥሩ ሁኔቷ እየመራች ያለችው መምህርት ቃልኪዳን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች እየተሰጠ ያለው ትኩረት በመጨመሩ አሁን ላይ በኮምፒዩተር ማንበቢያው ስላለ ሕይወትን ቀለል እንዳደረገላት አስረድታለች፡፡
“ሕይወት ውጣ ውረድ አላት” ያለችው መምህርት ቃልኪዳን፣ ውጣ ውረዱን እንደ መስፈንጠሪያ ከተጠቀምን አትችልም ያሉትን ሰዎችም ወደ ራስ መሳብ እንደሚቻል ካሳለፈችው ህይወት ተሞክሮዋ አካፍላናለች፡፡
አሁን ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተመረቀችበት የትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ የምትገኝ ሲሆን “አካል ጉዳተኞች በተለይም ማየት የተሳናቸው ማለፍ የማይቻሉ የሚመስሉትን የሕይወት ውጣ ውረዶችን በጥንካሬ ማለፍ እንደሚችሉ እኔ ጥሩ ማሳያ ልሆን ስለምችል፤ በርቱ የማይታለፍ ቀን የለም፡፡” ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

More Stories
የቱሪስት መዳረሻዎች – በሲዳማ ክልል
የጉዞ ጅማሮ
“ከአለቆቼና ከባልደረቦቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት በሥራ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” – አቶ ሰለሞን ፋንቱ