“አብዛኞቹ የጥርስ ጤና ችግሮች መከላከል የምንችላቸው ናቸው” – ዶክተር አማኑኤል ኢዳሶ

በአለምሸት ግርማ

የዛሬው የንጋት እንግዳችን ዶክተር አማኑኤል ኢዳሶ ይባላሉ። በሃዋሳ ስፔሻሊቲ የጥርስ ክሊኒክ የጥርስ ሀኪም ናቸው። በጥርስ ጤናና ውበት አጠባበቅ ዙሪያ ባደረግነው ቆይታ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል። መልካም ንባብ፦

ንጋት፦ ዶክተር አማኑኤል በቅድሚያ ፈቃደኛ ስለሆኑ በጋዜጣ ዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።

ዶክተር አማኑኤል፦ እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።

ንጋት፦ የጥርስ ጤና እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር አማኑኤል፦ የጥርስ ጤንነት ሰዎች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ የጥርስ ጤና ችግሮች መከላከል የምንችላቸው ናቸው። ሆኖም ለተፈጠሩ ችግሮች ደግሞ በህክምና መፍትሔ መስጠት ይቻላል። የጥርስ ህመምን መከላከል የጥርስን ጤንነት ለመጠበቅ ቀዳሚው መንገድ ነው። ከዚያ ባሻገር በጊዜ ወደ ባለሙያ መምጣት፣ የጥርስን ንፅህና መጠበቅ፣ ቋሚ ክትትል ማድረግ፣ ልጆችን መከታተል፣ በተለይም የልጅነት የጥርስ መብቀያ ጊዜን ማለትም ከ6ወር እስከ ሶስት ዓመት ድረስ የልጅነት ጥርሶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው ካልበቀሉ ሀኪም ዘንድ መሔድና መከታተል ያስፈልጋል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ጤናማ ጥርስ እንዲኖረን ያስችላሉ። 

ንጋት፦ የጥርስን ጤንነት ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ምንድናቸው? ውጫዊም ውስጣዊም

ዶክተር አማኑኤል፦ የጥርስን ጤንነት ሊጎዱ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። በቅድሚያ ውስጣዊውን ስንመለከት አመጋገብ አንዱ ነው። በካልሺየም የበለፀጉ ምግቦችን በበቂ መጠን የማንወስድ ከሆነ ጥርሳችን ሊጎዳ ይችላል። ሌላው የአፍ ውስጥ ምራቅ መድረቅ ነው። ምራቅ በተለያየ ምክንያት ሊደርቅ ይችላል።

በዚህ ጊዜ ጥርስን የሚጎዱ ነገሮች በጥርስ ላይ ለመለጠፍ ዕድል ያገኛሉ። እነዚህ የተለጠፉ ነገሮች ደግሞ ጥርስን ለመቦርቦርም ሆነ ለህመም ለመዳረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል። ሌላው የአሲድ ይዘት ያላቸውን ምግቦች በብዛት መውሰድ ነው። ይህም የጥርስን ጤና የሚጎዳ ነው። እንዲሁም በእርግዝና ወቅት የሚፈጠር የሆርሞን መዛባትና የድድ መድማት ህመም ተጠቃሽ ሲሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች በእርግዝና ወቅት የጥርስ ክትትል ቢያደርጉ መልካም ነው። በተለይም የጥርስ ህክምና ላይ ያለች ሴት ከሆነች ክትትሏን ማቋረጥ የለባትም።

ሌላው የተጓዳኝ ህመሞች መኖር ነው። የስኳር፣ የደም ግፊትና የድድ ህመም ያለባቸው ግለሰቦች የጥርስ ህክምና ክትትል ማድረግ አለባቸው።

ውጫዊውን ስንመለከት ደግሞ፦ አመጋገብ ሁለቱም ጋ የሚጠቀስ ነው። ስኳር የበዛበትን ምግብ አብዝቶ መመገብ፣ ለስላሳ መጠጦችን አብዝቶ መውሰድ፣ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ኒኮቲን የበዛባቸውን ነገሮች መጠቀም፣ አንዳንድ መድሐኒቶች(የደም ግፊት፣ የጭንቀት የመሳሰሉት)፣ ጥርስን ማፏጨት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ጥርስ ሲታመም ሳይሆን ቋሚ ክትትልና እንክብካቤ በማድረግ ጤናውን መጠበቅ ይቻላል። በተለይም በእርግዝና ጊዜ እናቶች ቴትራሳይክሊን መድሐኒት የሚወስዱ ከሆነ የጥርስ ቀለም በቋሚነት እስከመቀየር የሚያደርስ ችግር ሊያጋጥም ይችላል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተከለከሉ ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብ፣ ቋሚ የጥርስ ህክምና ክትትል ማድረግ፣ ስኳር የበዛባቸው መድሐኒቶች ከተወሰዱ በኋላ አፍን ማፅዳትና ፈሳሽ ነገር በደንብ መውሰድ ይመከራል።

ንጋት፦ የፍሎራይድ ምንነትን ቢያብራሩልን፤ በተያያዘ ፍሎረሲስ መንስኤዎች፣ ምልክቶችና ህክምናው ምን ይመስላል?

ዶክተር አማኑኤል፦ ፍሎረሲስ ከገፅታና ከውበት ጋር የሚገናኝ የጥርስ ችግር ነው። የሚከሰተውም የፍሎራይድ መጠናቸው ከፍ ያለበትን ውሃ ወይም የጥርስ ማፅጃ ሳሙና በመጠቀም ነው። የፍሎራይድ መጠን በአንድ ሊትር ውሃ ውስጥ ከ1.5 መብለጥ የለበትም። 

በእርግጥ ይሔ ችግር የሚፈጠረው ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ ሲሆን፤ ፍሎራይድ ችግሮች የሚጀምሩት የጥርስን ቀለም በመቀየር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ቀጫጭን ነጫጭ መስመሮች ቀጥሎም ቡኒ ቀለም ያላቸው ነጠብጣቦች ይፈጠራሉ። በተለይ እነዚህ ትንንሽ ቡኒ ነጠብጣቦች እርስ በርስ በመጣበቅ ጥርሱን የመብሳት ምልክት ያመጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ፍሎራይድ መጠን ከፍ ሲል ጠንካራውን የጥርስ ክፍል ደካማ ያደርገዋል።

ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ፍሎሮሲስ ወደ ቋሚ የጥርስ ቀለም መቀየር፣ የአናሜል ጉዳት እና አጠቃላይ የጥርስ እና የአጥንት ጤናን እንዲሁም የልብ ጤናን ሊጎዳ ይችላል።

ህክምናውም እንደየደረጃው ይለያያል። በመጀመሪያ ደረጃ ያሉት ነጠብጣቦች በእጥበት ህክምና የሚፀዱ ሲሆን፤ ደካማ ደረጃ የደረሱትን ደግሞ የመተካት ህክምና ይደረግላቸዋል። ሁሉም ታካሚ በተመሳሳይ መንገድ አይታከምም። ቅድመ ምርመራ ተደርጎለት እንደአስፈላጊነቱ ህክምና ይደረግለታል። ውበቱም ይመለሳል።

በመሆኑም ሰዎች በጊዜ ወደ ህክምና በመሄድ ተገቢውን ህክምና በማድረግ መፍትሔ ማግኘት አለባቸው። ነገር ግን በቆየ ቁጥር ህክምናውን ውስብስብ ከማድረጉም በላይ ለታካሚዎች መፍትሔውን በቀላሉ እንዳያገኙ ያደርጋል። በተለይም ህፃናት ጥርሳቸውን ሲቦርሹ ሳሙናውን እንዳይውጡት ወላጆች ክትትል ማድረግ አለባቸው።

ትክክለኛ መጠን ከ0.7እስከ 1.5 ሚሊግራም በ1 ሊትር ውስጥ ሲሆን፤ ከዚያ በላይ ከሆነ አንድ ህጻን በፍሎራይድ የመጠቃት እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። የአሜሪካ ህብረተሰብ ጤና ተቋም እና የአለም የጤና ድርጅት መሰረት 0.7 ሚሊግራም በቂ ሲሆን፤ ከ1.5 ሚሊግራም ደግሞ መብለጥ የለበትም።

ለአዋቂ የዘወትር አጠቃቀም ከሚሊዮን 1000 እስከ 1500 እጅ ወይም ክፍል ያህል ፍሎራይድ ማካተት ይኖርበታል።. ለህጻናት እስከ 6 አመት ላሉት ደግሞ ከሚሊዮን 500_1000 እጅ ፍሎራይድ መያዝ አለበት። ከእነዚህ ውጪ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ታካሚዎች በሐኪም የሚታዘዝበት ሁኔታ አለ።

ንጋት፦ ጤናማ የልጆች የጥርስ አበቃቀልን የሚጎዱ ነገሮች ምንድናቸው?

ዶክተር አማኑኤል፦ ጤናማ የልጆች ጥርስ አበቃቀል የሚጎዳባቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ችግሮቹን ለሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን። በቅድሚያ ውስጣዊውን ስንመለከት፦ አመጋገብ ዋናውና ቀዳሚው ነው። በተለይም የካልሺየም ይዘት የሌላቸውን ምግቦች የሚያዘወትሩ ከሆነ፤ በዘር የሚመጣ የአበቃቀል ችግር ማለትም የመፍጠን ወይም የመዘግየት ችግር፤ እንዲሁም ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህፃናት ላይ የዕድገት ሆርሞን ዕጥረት፤ የመንጋጋ መጥበብ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ የህፃናት ጥርሶች በመደበኛ የመብቀያ ጊዜ ሳይበቅሉ ከዘገዩ ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።

ምክንያቱም የልጅነት ጥርስ በሚነቀልበት ወቅት ማለትም ከአምስት ዓመት ተኩል ጀምሮ ጥርሶቹ ተነቅለው ለቋሚው ጥርስ ቦታ ካልለቀቁ ቋሚው ጥርስ መውጫ ስለሚያጣ ድርብ ሆኖ ሊበቅል ይችላል። የልጅነት ጥርሶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው እስከ 13 ዓመት ድረስ ተነቅለው ሊያልቁ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን የመጨረሻ መንጋጋ ሊዘገይ ይችላል፤ አልፎ አልፎም በተለይም የመንጋጋ ጥበት ካለ ተቀብረው የሚቀሩበት ሁኔታ አለ።

ውጫዊው በተመለከተ፦ ረጅም ጊዜ ጡጦ መጥባት፣ ጣት መጥባት (የጥርስ አቀማመጥ ሊቀይር ይችላል)፣ አደጋ፣ በትክክለኛ ጊዜ አለመብቀልና የመንጋጋ መጥበብ ናቸው።

መፍትሔውን ስንመለከት ደግሞ፦ የጥርስ መብቀያ ጊዜን መከታተል፣ ልጆችን፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የአፍ ጤናን መጠበቅና ጎጂ ልማዶችን ማስወገድ ናቸው።

ንጋት፦ ዘመናዊ የጥርስ ህክምናዎች የሚያካትቱት አገልግሎት ምን ምን ናቸው?

ዶክተር አማኑኤል፦ ዘመናዊ የጥርስ ህክምና የሚባለው ቀድሞ በመከላከልና ዘመናዊ በሆኑ መሳሪያዎች በመታገዝ የሚደረግ ህክምና ነው። እንዲሁም ህክምናው በተሻለ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለታካሚዎች የሚሰጥበት መንገድ ነው። መሳሪያዎቹ በተለይም ማንኛውም ታካሚ ወደ ህክምና ተቋም ሲመጣ ምርመራ ከማድረግ ጀምሮ፥ የሚሰጠውን የህክምና ዓይነት እስከመወሰን ድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። እንዲሁም በህክምናው ሒደት ውስጥ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከኬሚካል ነፃ መሆናቸውን በማረጋገጥ ነው ህክምናው የሚሰጠው። ለምሳሌ “ካድካም” የሚባለው መሳሪያ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተሻለ መሳሪያ ሲሆን፤ የታካሚውን ሁኔታ በተሻለ መንገድ መመርመር የሚያስችል ነው። በተመሳሳይ ሌሎችም ዘመኑ የደረሰባቸው መሳሪያዎች እንዲሁ በጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።

ለምሳሌ በአደጋ ወይም በሌላ ምክንያት ጥርሱን ላጣ ታካሚ ካሉት ጥርሶች ጋር አብሮ የሚሄድ ደጋፊ ጥርስ ወይም ሙሉ በሙሉ በመተካት አገልግሎት ይሰጣል። የጥርስ ህመምን ቀድሞ መከላከል ዘመናዊነት ነው። እንዲሁም ችግሩ ሲከሰት በፍጥነት ወደ ባለሙያ በመሔድ መፍትሔ መፈለግም እንዲሁ።

ብሬስ የሚሰራበት ህክምናም ከነዚሁ መካከል ተጠቃሽ ነው። ብሬስ በዋናነት ውበት ነክ ስራ ቢሆንም፤ መሰራት የሚያስፈልጋቸው በአደጋ ወይም በተፈጥሮ የአበቃቀል ችግር ማለትም ትክክለኛ ያልሆነ አነካከስ ያላቸው ጥርሶች ናቸው። ስለዚህ ብሬስ እንደነዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን በማስተካከል ወደሚፈለገው ደረጃ የሚያደርስ ህክምና ነው። በተያያዘ የተቦረቦሩ ጥርሶች ይሞላሉ፤ በተለያየ ምክንያት ቀለማቸው የተቀየረ ጥርሶችም የእጥበት ህክምና ይደረግላቸዋል።

ንጋት፡- እንደባለሙያ የህብረተሰቡ ግንዛቤና የህክምናው ጥራት ምን ደረጃ ላይ ነው?

ዶክተር አማኑኤል፦ ከዚህ ቀደም በጥርስ ህመም ከሚመጡ ታካሚዎች አብዛኛዎቹ ለማስነቀል ነበር የሚመጡት። አሁን አሁን ግን ያ ልማድ እየተሻሻለ መጥቷል። የታመመ ጥርስ ሁሉ እንደማይነቀል ሰው እየተረዳ ነው። በመሆኑም የግንዛቤው ደረጃ ጥሩ ነው። ነገር ግን ይሔ ማለት ሙሉ ነው ማለት አይደለምና የሚቀሩ ስራዎች ይኖራሉ። በተለይም ሰፊው ችግር የሚቀረፈው በዚያ ነውና በቤት ውስጥ የሚደረግ የጥርስ ጤናና ንፅህና አጠባበቅ እና ፈሳሽ ከመውሰድ ጋር በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

ህክምናውን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የጥርስ ህክምና ተደራሽነትም ሆነ ጥራት ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። አብዛኛዎቹ ክሊኒኮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ነው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት። ይህም በሁሉም ተቋማት ደረጃ ሊስፋፋ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ንጋት፦ የጥርስ ጤና አጠባበቅን በተመለከተ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

ዶክተር አማኑኤል፦ ጥሩ ፈገግታ ጥሩ የጥርስ ጤና መኖሩን ያመላክታል። በመሆኑም ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ በማፅዳት(በመቦረሽ)፣ የተመጣጠነ(በካልሽየም የበለፀገ) ምግብ በመመገብ፣ ቋሚ ክትትል በማድረግ፣ የተፈቀደ መጠን ፍሎራይድ ያላቸውን የጥርስ ማፅጃ ሳሙናዎች በመጠቀም፣ አላስፈላጊ ልማዶችን (ማጬስ፣ አልኮል መጠጣት የመሳሰሉትን) በማስወደግ የጥርስን ጤና መጠበቅ ያስፈልጋል። የምንመገበው ምግብ ሁሉ የሚያልፈው በአፋችን በኩል በመሆኑ የአፍ ንፅህናን መጠበቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ንጋት፦ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

ዶክተር አማኑኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ!