“ወታደርነቴ ያስተማረኝ በራስ መተማመንና ሥራ ወዳድነትን ነው” – ወታደር ከበደ ደቀማ

“ወታደርነቴ ያስተማረኝ በራስ መተማመንና ሥራ ወዳድነትን ነው” – ወታደር ከበደ ደቀማ

በአብርሃም ማጋ

ጥንካሬና በራስ መተማመን ከብዙ ነገሮች ሊገኝ ይችላል፡፡ ወታደር በመሆን ከሚገኘው ጋር ግን በፍፁም አይነፃፀርም። ትጋት፣ ታታሪነት በራስ መተማመን በሕይወት ውጣውረድ ውስጥ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በጣም ያግዛል፡፡ የዛሬው ባለታሪካችንም በዚህ ሂደት ያለፉ ክንደ ብርቱ ወታደር ናቸው፡፡

ወታደር ከበደ ደቀማ የዛሬው ባለታሪካችን ሲሆኑ በወታደርነታቸው ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ እንዳልሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ወታደርነት ቁርጠኝነትንና ችግሮችን ተጋፍጦ ማለፍ አስተምሯቸዋል፡፡ በልበ ሙሉነት ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ የሚሠሩ ታታሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በራስ መተማመንን አጐናፅፏቸዋል፡፡

ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ ተመልምለው በተለያዩ የኤርትራ ግንባሮች ብቻ ከ5 ዓመት በላይ ሲዋጉ መቆየታቸው ጠንካራ፣ ንቁ፣ ታታሪ፣ ልበ ሙሉ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ከውትድርና ዓለም በኋላም በግል ሥራ ተሠማርተው የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ጥሰው ዛሬ ላይ ከማንም በታች ሳይሆኑ ጥሩ ህይወት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡

ለመግቢያነት ይህንን ካልን ምርጥ ተሞክሯቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን መልካም ንባብ፡፡

ወታደር ከበደ ደቀማ በቀድሞው መንግስታዊ አወቃቀር በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ በሲዳማ አውራጃ፣ በዳሌ ወረዳ፣ በደቡብ መሰንቀላ ቀበሌ በ1962 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በአሁኑ ወቅት የ56 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ የልጅነት ህይወታቸው ሲታይ እንደማንኛውም አርሶ አደር ልጅ በከብት እረኝነትና እርሻ ሥራ ተሠማርተው ነው ያደጉት፡፡

እድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ በ1970 ዓ.ም በ8 ዓመታቸው ነበር ደቡብ መሰንቀለ ተብሎ በሚጠራው ት/ቤት 1ኛ ክፍል የገቡት። በት/ቤቱ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ተምረዋል። በወቅቱ ት/ቤቱ እስከ 5ኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምር በመሆኑ 6ኛ ክፍልን የተማሩት በጐረቤት ቀበሌ ባለው ት/ቤት ነበር፡፡ ቀበሌውም ሰሜን መሰንቀላ ይባላል፡፡

በመሆኑም በወቅቱ በትምህርት ጐበዝ ተማሪ በመሆናቸው በ6ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ 98 ከመቶ በማምጣት ነበር ወደ 7ኛ ክፍል የተዛወሩት፡፡

ከ7ኛ -8ኛ ክፍል አፖስቶ በሚገኘውና የካቲት 25 ተብሎ በሚጠራው መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረዋል፡፡

በ1978 ዓ.ም ይርጋዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጀ ት/ቤት ይገባሉ፡፡ ይሁን እንጂ በትምህርት ቤቱ ለጥቂት ወራት ብቻ ከተማሩ በኋላ ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡ በወቅቱ በትምህርት ላይ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጐት ያለያያቸው ብሔራዊ ውትድርና ነበር፡፡ የደርግ መንግስት ያለፍላጐታቸው በግዳጅ ለውትድርና መለመላቸው፡፡

በመሆኑም በ1978 ዓ.ም ላይ በ3ኛ ዙር ብሔራዊ ውትድርና ተመልምለው ወለጋ ክ/ሃገር ዲዴሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ገብተው ለ6 ወራት ያህል ሰልጥነዋል፡፡

ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ በተለያዩ የኤርትራ ግንባሮች ለውጊያ ተሰለፉ፡፡ ለአብነት ያህል ተለብሶ፣ ጀንጌሪን፣ አጓሮ፣ ከሬን፣ ሐላል አዲተክለ ዛን፣ ተወርዋሪ እግረኛ ጦር ተዋጊ ሆነው ተዋግተዋል፡፡

ከ1978- 1981 ዓ.ም ድረስ በመለብሶ ግንባር ዋሊያ ክ/ጦር፣ 8ኛና 6ኛ ብርጌድ እግረኛ ተወርዋሪ ወታደር ሆነው ለ3 ዓመታት ያህል ተዋግተዋል፡፡

ከ1981-1983 ዓ.ም ድረስ 607ኛ ኮር፣ 999ኛ ብርጌድ ከአሥመራ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በክሬን፣ በእለበርድ፣ በኦዴ ተክለ ዛን፣ ተወርዋሪ ወታደር ሆነው ግምባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡

በ1981 ዓ.ም ጄነራሎቹ የመንግስት ግልበጣ ሴራ ሲጠነስሱ እሳቸው ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስለነበራቸው ድርጊታቸውን በመቃወም ፅኑ ዓላማ ይዘው ሳይበገር ከፍተኛ የትጥቅ ትግል አድርገዋል፡፡

ፅኑ ዓላማ ይዘው ድርጊቱን ለማክሸፍ ከተሰለፉት ወታደሮች አንዱ በመሆናቸው የምስጋና የምስክር ወረቀት ከሀገሪቷ መሪ ተሰጥቷቸዋል፡፡፡

ጄኔራል ጥላሁን የተባለ አዛዥ በ1982 ዓ.ም ያደረገውን አፀያፊ ድርጊትን በመኮነን ይናገራሉ፡፡ ጀነራሉ ያደረገው ነገር ቢኖር ከኤርትራ ተዋጊዎች /ከሻዕቢያ/ ጋር ድብቅ ግንኙነት በማድረግ በ3 ሚሊዮን ብር ተስማምቶ ምፅዋን ለሻዕቢያ አሳልፎ ሰጥቷል።

የአሰጣጡ ሂደት ሲዘረዘር እንዲህ ነበር፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም ልብስ፣ ጫማ፣ መለዮ ከመጋዘን ውስጥ አውጥቶ በድብቅ ለሻዕቢያ ወታደሮች አሳልፎ ይሰጣል፡፡

በዚሁም የሻዕቢያ ወታደሮች ልብሱን ለብሰው በቀጥታ ከሠራዊቱ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡

ጀኔራሉም ለኢትዮጵያ ወታደሮች ያስተላለፈው መልእክት የኛ ጦር ነውና መሳሪያችሁን እንዳታነሱ የሚል ነበር። በዚሁም ተቀላቅለው ገብተው ኖሮ የሻዕቢያ ወታደሮች ምፅዋን በቁጥጥር ሥራ ማዋላቸውን በቁጭት ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ጀኔራሉ የተሰማው 3 ሚሊዮን ብር ሐሰተኛ ኖት በመሆኑ ተጐጂ መሆኑን በማፌዝ ከመግለፅ ወደ ኋላ አላሉም።

በ1983 ዓ.ም ግንቦት 19 ላይ በጦር ግንባር ተሰልፈው እያሉ ኤርትራን ሻዕቢያን ሲቆጣጠር እነሱ ሙሉ ትጥቅ ይዘው ጉዞ ወደ ሱዳን ያደርጋሉ፡፡

ጉዞ ያደረጉት በኮሬን፣ በሀጋዝ፣ በአቅርዶት፣ በተሲኒ በባሬንቱ አድርገው ለ3 ቀናት ያህል በመንገድ ላይ እየተዋጉ ሱዳን ድንበር ይደርሳሉ፡፡

ሱዳን እንደደረሱም መሳሪያዎቻቸውን /ሎጂስቲካቸውን/ ለአብነት ያህል ታንክ፣ መድፍ፣ ዙ23ን ሁሉ ለሱዳን መንግስት አስረከቡ፡፡

ከዚያም ሱዳን ከገቡ በኋላ የስደተኞች እርዳታ ሰጪ ድርጅት /ቀይ መስቀል/ ቀድሞ ባይደርስላቸውም እድሜ ለሱዳን ህዝብ ምንም ችግር እንዳልደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡

ለ3 ቀናት ያህል ምግብና ውሃ በመስጠት ላደረገላቸው በጐ አድራጐት ትብብር ከምስጋና ጭምር ይናገራሉ፡፡

ከ3 ቀን በኋላ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ድርጅት የስደተኞች ካምኘ መሥርቶ ድንኳን፣ ምግብና ውሃ እየሰጣቸው 15 ወራት ያህል በጥሩ ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡ በወቅቱ ሱዳን የገባው የኢትዮጵያ ጦር 60 ሺህ እንደሚደርስ ገልፀው የካምፖቸው መጠሪያ ፋኦ አንድ መሆኑን ከአንደበታቸው ተደምጧል፡፡

በሱዳን እያሉ ወታደር ከበደ ደቀማ ሥራ ወዳድና ታታሪ በመሆናቸው እጃቸውን አጣጥፈው በካምኘ ውስጥ ብቻ ቁጭ አላሉም ነበር፡

በባለሃብቶች የተመረተውን የሰሊጥ ምርት እየወጡ አጭደው በየቀኑ ገንዘብ ያግኙ ነበር፡፡ የሰሊጥ ምርት አጭደው በቀን 80 የሱዳን ገንዘብ /ጂኒ/ ያገኛሉ፡፡ ይህ ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 8 ብር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን በዚህን ወቅት አንድ ያጋጠማቸውንና የኩራት ስሜት የጫረባቸውን ነገር ሳያወጉን አላለፉም ነገሩ እንዲህ ነበር፡፡ ሥራ ፍለጋ ሁሌ በሰፊው ባለበት ሰሊጥ ማሳ ይዘዋወራሉ፡፡ ነገር ግን የት ነው የምትሄዱት ብለው የሚጠይቃቸው አካል አልነበረም። እንደፈለጉ በማሳ ውስጥ ተዘዋውረው ሥራ ፈልገው ይሠራሉ፡፡ ይህ ነገር በጣም ይገርማቸው ነበር፡፡

አንድ ቀን በሰፊ እርሻ ማሳ ውስጥ ሲሄዱ የእርሻውን ባለቤት ያገኛሉ፡፡ እንደተለመደው ሰላምታ ሰጥቶ ዝም ይላቸዋል፡፡ ይህ ባለሃብት አማርኛን ትንሽ ትንሽ ይናገር ነበር፡፡ ወታደሩም የሱዳንኛ ቋንቋን በትንሹ ይሞክር ነበር፡፡ በዚሁም ሰውየውን በማሳ ውስጥ ስንሄድ ለምንድነው? የት ትሄዳላችሁ? የማትለን ብለው ይጠይቁታል፡፡

ባለሃብቱ የሰጠው ምላሽ ቢኖር “እኛ እናንተ ሞት የማትፈሩ ጀግኖች ስለሆናችሁ ስለምንወዳችሁና ስለምናከብራችሁ ነው” በማለት ይመልስላቸዋል፡፡ ቀጥሎም በጥቁሮች ዘንድ የማይታሰበውን ትልቅ ገድል ለማንም ሳትንበረከኩ የአፍሪካን ስም ያስጠራችሁ ታላቅ ህዝብ መሆናችሁ ያኮራኛል በማለትም አክለዋል ይላሉ፡፡

ሌላው ደግሞ የሚያነሱት ነገር ቢኖር በስደተኛ ካምኘ ውስጥ እያሉ የሚሰጣቸው የስንዴ ዱቄት አገንፍተው በርበሬ /ሱጐ/ ጨምረው ይበላሉ፡

አንድ ቀን አንድ ሱዳናዊ ወደ ካምፑ መጥቶ ኖሮ ገንፎውን እያዩ አንድ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል፡፡ ጥያቄውም ይህ ምንድነው ገንፎ ውስጥ የጨመራችሁት የሚል ነበር፡፡ በሱዳን ውስጥ በርበሬ ይፈራል፡፡ በዚሁም ስለማያውቁም አይጠቁመም ነበር፡፡

እና ወታደር ከበደ የሰጠው ምላሽ ቢኖር በርበሬ እንደሆነ ገለፃቸው፡፡

በዚሁም ሱዳናዊው እናንተን ጀግኖችን ሃይለኞች እንድትሆኑ ያደረጋቸሁ በርበሬ ሳይሆን አይቀርም እንዳላቸው ያብራራሉ፡፡

በመቀጠልም ቀጫጭኖችን አይናችሁ እንዲሆን ያደረጋችሁም በርበሬ ነው በማለትም ደምድምአል፡፡

እኔም ቢሆን የሱዳኖች ዓይን እንዴት ነው? ብዬ ሳልጠይቃቸው አላለፍኩም፡፡ ሱዳኖች ዓይናቸው ነጭ ቁመታቸው ረጅም ነው በማለት ገልፀውልኛል፡፡

ወታደር ከበደን በኢትዮጵያ ውስጥ በውትድርና ዓለም ባሳለፈባቸው እንደ ችግር ያዩት ነገር ምን እንደሆነ ሳንጠይቃቸው አላለፍንም ነገር ግን የሰጡን ምላሽ፡- ከፍተኛ የሬሽን፣ የውሃ፣ ችግሮች ነበሩ ብለውናል፡ አካባቢው በረሃማ መሆኑም ከፍተኛ ችግር ነው ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የውሃ ችግር እጅግ ከፍተኛ ነበር ብለው በውሃ ጥም የበርካቶችን ህይወት ጐድቷል ይላሉ፡፡

በውትድርና ዓለም ውስጥ በተወርዋሪ እግረኛ ጦር ሆነው በተለያዩ ግንባሮች ተሰልፈዋልና በአካልም ላይ የደረሰብዎት ጉዳት አለን? ብለንም ጠይቀናቸዋል፡፡

ከምላሻቸው እንደተደመጠው ከሆነ ምንም ዓይነት ጉዳት በጠላት ጥይት አልደረሰባቸውም፡፡ ሚስጥሩን ጠይቀናቸው እንደተአምር የሚያነሱት ነገር፡- ወደ ግንባር ሲሄዱ ለአምላካቸው ያቀረቡት ፀሎት ነበር፡፡ አትግደለኝ አላሉም፡፡ ነገር ግን ያሉት አካለ ጐዶሎ አድርገህኝ ወደ ሃገር አትመልሰኝ፡፡ አካለ ጐዶሎ ከምታደርገኝ ጨርሰኝ በማለት መማፀናቸውን ያወሳሉ፡፡

ወታደር ከበደ በሱዳን በስደት በሚኖሩበት ጊዜ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው 5 ወር ከቆዩ በኋላ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግስት በተደረገው ስምምነት ነበር ጥቅምት ወር 1984 ዓ.ም ወደ ሃገራቸው የገቡት፡፡

በተሐድሶ ስልጠና ውስጥ ወደ ገጠር ለሚሄዱ የእርሻ መሬትና በሬ፣ ከተማ ለሚቀሩት የ6 ወር 50 ብር ዘይት፣ ሳሙና፣ ዱቄት ይሰጣችኋል የሚል ነበር፡፡

በዚሁም መሠረት እሳቸውም ወደቀያቸው ወደ ገጠር ሲመለሱ የእርሻ መሬት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከአባታቸው ያገኙትንና ከመንግስት የተሰጣቸውን መሬት ይዘው ወደ ግብርና ሥራ ገብተዋል፡፡

ከዚህ በፊት አንድ መጠቀስ የሚገባው ነገር ቢኖር፡- ለወላጆቻቸው ታላቅ ወንድ ልጅ በመሆናቸው በቤተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ወላጆቻቸው ልጃቸውን በህይወት ኖሮ ይመጣል የሚል እምነት አልነበራቸውም። ሁሌ በሚያደርጉት ፀሎት ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በሰላም መመለሳቸው ከነሱም በላይ በጐረቤቶቻቸውም ዘንድ ታላቅ ደስታን ፈጥሯል፡፡ በዚሁም ፈጣሪ እንኳን በሰላም አመጣህ ለሚሉት ለአካባቢው ህዝብ ትልቅ ሰንጋ በሬ አርደው ማብላታቸውን የገለፁት ከምስጋና ጭምር ነው፡፡

ወታደር ከበደ ወደ ግብርና ሥራ ሲገቡ የራሳቸውን እርሻ ብቻ አይሠሩም ነበር። ለዓመታት እዳሪ የነበረውን የአያታቸው መሬትም አርሰው ቡና እና እንሰት ተክለው እንዲጠቀሙ አድርገዋል፡፡ ለዚህም ሴት አያታቸው /የአባታቸው እናት/ አንድ ላም ከምርቃት ጋር የሰጡአቸው ራሳቸውን እንዲያቋቁም ረድቶአቸዋል፡፡

ምንም እንኳን ከብሔራዊ ውትድርና መልስ በ1985 ዓ.ም ያቋረጡትን ትምህርት ጀምረው ከ9-12ኛ ክፍል ይርጋዓለም አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በትምህርታቸው ጎበዝና ከ1-3 የሚወጡ ቢሆንም የ12ኛ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ዩኒቨርስቲ የማያስገባቸው ሆነ፡፡ በዚህም ብስጭት ትምህርትን እርግፍ አድርገው በመተው ወደ ንግድ ሥራ ገቡ፡፡

ወታደር ከበደ የግብርና ሥራ እየሠሩ ጐን ለጐን ንግድ ሥራንም ያካሂዱ ነበር፡፡ የንግዱ ሥራም ቡና ነበር፡፡ ከዲላ ከተማ ገዝተው ሐዋሣ ከተማ ወስደው ይሸጡ ነበር፡፡ በዚሁም ጥሩ ገቢ ማግኘት ሲጀምሩ አንድ ቀን ኬላ ጠባቂዎች ኮንትሮባንድ ነው ብለው ቡናቸውን ይይዙባቸዋል፡፡

በዚሁም ተፈናቅዬ ሥራ አጥቼ ነው የምሠራው ብለው ተማፅነዋቸው ከአሁን በኋላ ስትሠራ እንዳናገኝህ ብለው አስጠንቅቀው ለቀቁአቸው፡፡

በመሆኑም የቡና ንግድ ሥራን አቁመው ወደ አጠና ንግድ ሥራ ገቡ፡፡ በአካባቢያቸው በቁም ያለ ባህር ዛፍ ገዝተው አስቆርጠው ሐዋሣ ወስደው ለችርቻሮ ነጋዴዎች ያከፋፍሉ ነበር፡፡

በዚህ ሥራም ጥሩ ገቢ ማግኘት ቢችሉም በተለያዩ ምክንያቶች አቁመው ባጃጅ ገዝተው መሥራት ጀመሩ፡፡ በትርፍ ሰዓታቸው ባጃጅ እየሠሩ በመደበኛ ጊዜ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ የጥበቃዎች ሺፍት መሪ /አስተባባሪ/ ሆነው ይሠራሉ፡፡

ስለወታደርነት ሥራ ያላቸው ፍቅር ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ የሰጡን ምላሽ ቢኖር፡- “ወታደርነት ያስተማረኝ በራስ መተመማንን፣ ሥራ ሳልንቅ ይህንን አልችልም ከአቅሜ በላይ ነው እንዳልል አድርጐኛል” በማለት ፍቅሩን ይገልፃሉ፡፡

አይይዘውም “በወታደርነቴ ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ አይደለሁም” በማለትም ያክላሉ።

ታታሪ፣ ሥራ ወዳድ፣ ብርቱና ጠንካራ እንዲሆኑ አስችሎአቸዋል ወታደር መሆናቸው፡፡

በተፈጥሮአቸው የሚጠሉት ነገር ቢኖር፦ ሥራ የሚንቅ፣ ተስፋ የሚቆርጥ በውሸት የሚምል ሰው እንደሆነ ሲገልፁ ተደምጧል፡፡

የሰው ልጅ በሥራ ዓለም ውስጥ ውጤታማ የሚሆነው በመፈቃቀር፣ በመተሳሰብ፣ በመነጋገር፣ በመወያየትና በመስማማት እንደሆነም ያብራራሉ፡፡

ሥራ በመሥራታቸው የመጣው ለውጥ ምን እንደሆነም ጠይቀናቸዋል፡፡ አንድ ወንድና 2 ሴት በድምር 3 ልጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ እያሳደጉ በግል ት/ቤቶች ለማስተማር መብቃታቸው፣ በሐዋሣ ከተማ ዘመናዊ ቤት መሥራታቸው ለእሳቸው ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

ይህ ምርጥ ተሞክሮ በሌሎቹም ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምኩኝ የዛሬውን ዝግጅቴን በዚሁ ቋጨሁ፡፡ ሰላም፡፡