7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች በግንባር ቀደምነት በመሳተፍ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

‎

‎ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሴቶች ድርሻ የጎላ መሆን አለበት ሲሉ አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሴት አመራሮች ገልፀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ‎ወ/ሮ ፀሀይ ወራሳ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሠላማዊ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ዋነኛ ግብ ነው በማለት ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች በግንባር ቀደምነት በመሳተፍ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎

‎ለሀገር ግንባታና ሠላም የሴቶች ድርሻ የጎላ መሆኑን የ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ሀገራችን ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍና የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉም አመላክተዋል።

‎

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ‎ወ/ሮ ተስፋነሽ ጥላሁን፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሠላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምክር ቤት አባላትና ሴቶች በተገቢው ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

‎

‎የወናጎ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፍሬነሽ ሮባ በበኩላቸው፤ ለምርጫ ሂደት ውጤታማነት በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሴቶች ተሳትፎ የነበሩ ጥንካሬዎችን በመውሰድና ጉድለቶችን በማረም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ በላቀ ደረጃ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

‎

‎ዘጋቢ: ፅጌ ደምሴ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን