ኢድ ሙባረክ
በፈረኦን ደበበ
ረመዳን፤ የእምነቱ ተከታዮች ፈጣሪያቸውን በጥልቀት ሲያስቡና ሲያከብሩ የሚቆዩበት ጊዜ ነው፡፡ ከምግብ፣ መጠጥና ሌሎች ሥጋዊ ፍላጎቶች ታቅበው የሚቆዩበት እንደመሆኑ ትልቅ ትርጉም ይፈጥራል፡፡
ጨረቃዋ ተገልጣ ጾሙ በሚፈታበት ጊዜ የሚፈጠረው ደስታም በጾም የደከመውን አካልና አዕምሮ ለማደስ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የሚፈጠረውን ደስታና አብሮነት ለማብሰር ሲባል ነው ጾም ፍቺው ኢድ ሙባረክ ወይም ኢድ አልፈጥር ተብሎ የሚጠራው፡፡
ሰዎች ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት ሲባል በረመዳን ከምግብና መጠጥ ታቅበው በፀሎት/ዱአ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ብርታትና ጽናትም ሸምተው ወደ አላህ ቀረብ ይላሉ፡፡ መንፈስና ሥጋቸውን በማጠንከር ታማኝነታቸውንም ይገልጻሉ፡፡
የዓለምን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚረዳው ይህ ጊዜ መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት ያግዛል፡፡ በህይወት ዘይቤ ትዕግሥትን እንዲማሩ ሲያስችል ለፈጣሪያቸው ያለውን ታማኝነት ለመግለጽም ይጠቅማል፡፡
ስለሆነም ኢድ-አል-ፈጥር ላሳለፉበት ጾምና ጸሎት ምህረትን ለማግኘት ይረዳቸዋል። ለከፈሉበት መስዋዕትነት ካሳ በማለትም ነው በጉዳዩ ላይ የሚጽፉ ምሁራን የሚናገሩት። የጌታን ፍቅርና ጸጋ ከማግኘትና ምህረቱን ለመጎናጸፍ እንደሚረዳም ነው ያስታወቁት፡፡ ለድሆች የሚያሳዩት ርህራሄና ፍቅርም በረመዳን ከተጎናጸፋቸው በረከቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
የኢድ ጸሎት
የእስልምና እምነት ዋና ጾም የሆነው ረመዳን ማብቂያ በተለያዩ ሥነ- ሥርዓቶች ይከበራል። ከእነዚህም መካከል የጾሙ መፈታትን የሚያበስረው የኢድ ጸሎት ወይም ሶላት ተጠቃሽ ነው፡፡
የጠዋት ጸሀይ መውጣቷን ተከትሎ የሚደረገው ይህ ጸሎት ወደ ዋናው የበዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት የሚያመራ ሲሆን በዚህም ብዙ ምዕመናን አንድ ላይ ተሰባስበው ወደ ማክበሪያ አደባበይ ይሄዳሉ፡፡
በዚያ ሥፍራ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ጸሎት ካደረጉና ፈጣሪን በዜማ ካመሰገኑ በኋላ “ኩትባህ” የተባለው ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ታላቅ የመንፈሳዊ መሪ ወይም ኢማም በረመዳን ጾም ስለተከናወኑ በጎ ተግባራት ለምዕመኑ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ የሚደረግ ሲሆን መግለጫውም በተከፈሉ መስዋዕትነቶች፣ መልካም ሥራዎችና በተገኙ መንፈሳዊ ጥንካሬዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡
ዛካት- አል-ፈጥር
ዛካት በድምቀት የሚከበረው የኢድ-አል-ፈጥር በዓል እንደ ዋነኛ ተግባር የሚታይ ሲሆን ሰደቃ በተባለው የበጎ አድራጎት ሥራ ይገለጻል። ማንኛውም ሙስሊም ለፈጣሪው ያለውን ታማኝነት የሚገልጽበት አንዱ መንገድ ሲሆን ይህም ለድሆች በዓይነት ወይም በገንዘብ የሚሰጡ ሥጦታዎችን ያጠቃልላል፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን በዋናነት በገንዘብ መልክ የሚሰጠው ዛካት አል-ፈጥር ለእሥላማዊ ተቋም ወይም መስጂድ የሚሰጥ ሲሆን አቅም የሌላቸው በዓሉን እንዲያከብሩ ለማድረግ የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡
የዕድሜ ወይም ጾታ ልዩነት ሳይደረግበት የሚሰጠው ዛካት በተለይ የመጨረሻው ረመዳን ቀን ማታ የሚፈጸም ሲሆን ድሆችና አቅም የሌላቸው በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ይረዳቸዋል፡፡
የበዓሉ አከባበር
ከሶላት አል-ፈጥር በኋላ የሚጀምረው ክብረ-በዓል በደስታና ፈንጠዚያ የታጀበ ነው፡፡ ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤትና ጓደኛን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አብሮነትን ያጠናክራል፡፡
ብዙ ጊዜ አዲስ በተገዙ ልብሶች የሚያጌጡት የዕምነቱ ተከታዮች ሥጦታ ይለዋወጣሉ፣ በቤታቸው ሆነው ከሚያከብሩት በተጨማሪ ወደ ሩቅ ቦታ በመሄድ ዘመድ አዝማዶችንም ይጠይሉ።
ጨረቃ የሚታይ ከሆነ በመጪው እሁድ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው የዘንድሮ ኢድ- አል-ፈጥር በዓል በዙ የእምነቱ ተከታዮች ባሉባቸው ሀገራት በድምቀት ይከበራል፡፡ ቤቶቻቸውን በማስዋብ ያሳምሩታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደ ሬስቶራንት በመሄድ ጣፋጭ ምግቦችንም ይመገባሉ፡፡ ምግብ የበዓሉ ማድመቂያ በሚባልበት በዚህ ጊዜ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ምግቦች ቀርበው ይመገቡበታል፡፡
የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ
ከላይ እንደተገለጸው ኢድ-አል-ፈጥር ሞቅ ያለና ደስታን የሚያጎናጽፍ በዓል ነው። ተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆን አቅም የሌላቸው ዜጎችን ሁሉ በማሳተፍ የደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ አንዱ ዘዴ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥርዓት ሲሆን በየጊዜው አሠራሩን ማዘመኑም ለምዕመናን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል፡፡ በበጎ አድራጎት መልኮች ገንዘብ ማዋጣትና ለተቸገሩት ማድረስ አስደናቂ የአከባበር ገጽታ እንደሆነ ተወስቷል፡፡
ዛካት መስጠት ለሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ አባል እንደ ግዴታ የሚታይ ሲሆን ይህ ታማኝነትን በማሳደግ ከአላህ ምህረት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ከረመዳን ጾም ማብቃት ቀደም ብለው የሚጀምሩት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎቹ አብዛኛው እስላማዊ በሆኑና ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች የሚከናወኑ ናቸው፡፡
አሠራሩን ለማቀላጠፍ ከእጅ ንኪኪ ውጭ የሆኑ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ሁሉ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሲሆን እነዚህ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ የሚጠቀሙባቸው እንደ ኪሬዲት/ ዴቢት ካርድ፣ ስማርት ስልኮችና እንዲሁም ስማርት ሰዓቶችን ሁሉ ያጠቃልላል ተብሏል፡፡
በመስጂድ መግቢያ ወይም መውጫ ላይ የሚከፈቱ ትናንሽ ሱቆች ወይም ኪዮስኮችም ገንዘቡን በቀላሉ ለምዕመኑ ለማድረስ እንደሚረዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡
More Stories
የልጅነት ፍቅር
መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ
“ሰው የሚለኝን ብሰማ ኖሮ፥ ለዛሬ አልበቃም ነበር”