በደረጀ ጥላሁን
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን መላከ ኤዶም ቀሲስ ተዋበ ምትኩ ይባላሉ። በመንፈሳዊ ትምህርት በቲዮዎሎጂ የተመረቁ ሲሆን በዓለማዊ ትምህርት ደግሞ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ሁለተኛ ድግሪ አላቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ በመንፈሳዊ አገልግሎት ቆይተዋል፡፡ በስብከት አገልግሎት ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን ከባለፈው አመት ጀምሮ በሀዋሳ ደብረ መድሐኒት መስቀለ ክርስቶስ ወአባ ገሪማ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። የጥምቀት በዓል በማስመልከት እንግዳ አድርገናቸው በዓሉ ከቱሪዝም ጋር ስላለው ግንኙነትና በተለይ በአሁኑ ወቅት የሚያገለግሉበት ደብር የጥምቀት በዓል በልዩ ሁኔታ ታቦተ ህጉ በሃዋሣ ሃይቅ ላይ ሽኝት የሚደረግለት በመሆኑና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፦ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ቀሲስ ተዋበ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ የጥምቀት በዓል አመጣጥና አከባበር በቤተ እምነቱ አስተምህሮ እንዴት ይገለፃል።
ቀሲስ ተዋበ፦ የጥምቀት በዓል አመጣጥ በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ አምላካችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ የተጠመቀበት ከዘጠኙ አበይት በአላት አንዱ ነው። በጥምቀቱ ድህነትን ሚስጥረ ጥምቀትን ያስተማረበት ነው።
እርግጥ አስተምህሮቱ ክርስቶስ የተጠመቀበትና እኛ የምንጠመቅበት ለየቅል ነው። ክርስቶስ የተጠመቀበት አንደኛ አርአያ እና ምሳሌ ሊሆን ነው። ሁለተኛ ደግሞ የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ ሊቀድ ነው። ምክንያቱም በኛ አስተምህሮ ከይሁዳና ሰማሪያ የሚመጡ በኢየሩሳሌም መካከለኛ ከተማ ላይ ዮርዳኖስ በምትባል ዮርና ዳኖስ በሚገናኙበት መካከል በታሪክ አስተምሮ አባቶች እንዳስቀመጡት ዲያቢሎስ አዳምና ሄዋንን በእምነ በረድ አስፈርሞ ዮርዳኖስ ላይ ቀብሮ ስለነበር ክርስቶስ በዚያ መጥመቁ የዕዳ ደብዳቤያችንን የቀደደበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው።
የድህነት ጅማሬ ስለሆነ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ የተጠመቀበት እኛም ታቦታትን ከመንበረ ክብራቸው ይዘን አምላካችን እንደተጓዘ ከቤተክርስቲያን ወደ ባህረ ጥምቀት ተጉዘን በአሉን እናከብራለን።
ሁለተኛው አስተምህሮ ኢትዮዽያ የምትጠቀምበት የብሉይ ስርአት ከግብጽ እስራኤልን እግዚአብሄር አርነት ባወጣ ጊዜ ታቦቱን ለሙሴ ሰጥቶ ታቦቱን ያከበሩት ካህናቱ በኢያሱ ዘመን መጽሀፈ ኢያሱ ምእራፍ 4 ጀምሮ ስናነብ ኢያሪኮን ከተሻገሩ በኋላ በዮርዳኖስ ታቦቱን ይዘው ካህናቱ ከፊት ለፊት ቀድመው ህዝቡ የተሻገረበት ማሳያ መሆኑን የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብሉይን ከአዲስ አስተሳስራ የያዘችበት ነው።
ንጋት፦ ምእመናኑ ከአስተምህሮቱ ምን ይማራሉ?
ቀሲስ ተዋበ፦ ጥምቀት ትልቁ የቤተክርስቲያን የአደባባይ በዓል ነው። የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ ምእመናን ታቦታቱን በማጀብ በሀይማኖታዊ ሥርዓት በትህትና እና በፍቅር እናከብራለን፡፡ በዓሉ እግዚአብሔርን ባለን ፀጋ የምናገለግልበት እንደ ዳዊት እየዘመርን በታቦታቱ ፊት ሆነን አምላካችን እያመለክን የትህትና ተምሳሌት የሆነውን ክርሰቶስ በመምሰል በፍቅርና በትህትና የምናከብርበት መሆኑን እና ለምስጋና ራሳችንን ማዘጋጀት እንዳለብን ነው የምንማረው፡፡
ንጋት፦ እርስዎ ከሚያገለግሉበት ቤተ-ክርስቲያን ጋር አያይዘው በሀይቅ ላይ የሚደረግ የታቦታት ሽኝት ከቱሪዝም አንፃር ያለውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?
ቀሲስ ተዋበ፦ ደብራችን ደብረ መድሀኒት መስቀለ ክርስቶስ ታቦቱ ከገባ ጀምሮ ጎዞውን እንደሌሎቹ በየብስ ወይም በመንገድ ከተማውን አቋርጦ አይደለም ወደ ማደሪያው የሚሄደው፡፡ የኛን ለየት የሚያደርገው ሀይቁን እየባረከ በውሀ ላይ ነው የሚሄደው፡፡ ይሄ ደግሞ የሀዋሳ ከተማን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የገጽታ ግንባታን ፈጥሯል፡፡ ታቦታቱን ለመሸኘት ውሀው አመቺ ስለሆነ ጀልባዎችን በመጠቀም ይህን ትእይንት መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም ህዝቡ ታቦታቱን በጀልባ ሆነው እየዘመሩ መሸኘታቸው ለቱሪዝም ስበት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
እንደሚታወቀው በሀገራችን በሀይቅ ላይ የሚደረግ ታቦታትን የማጀብ ሥነ ሥርዓት በሶስት ከተሞች ላይ ይከናወናል፡፡ በባህር ዳር ጣና ሐይቅ ላይ ታቦታቱን ሲሸኙ ህዝቡ ይህን ሀይማኖታዊ ገጽታ ለማየት ከውጪ ሀገራትና ከሀገር ውስጥም ትልቅ የቱሪዝም ስበት ፈጥሯል፡፡ በዝዋይም እንዲሁ በየአመቱ ይህን ትእይንት ለመመልከት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ሥፍራው ያቀናሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ ደግሞ ታቦታቱ በሀዋሳ ሐይቅ ላይ ለየት ባለ መልኩ በጀልባ መሸኘት ልዩ የሆነ ገፀ በረከት ፈጥሮልናል፡፡
በሀዋሳ ከተማ እንደ ቅዱስ ገብርኤል በታህሳስና ሐምሌ ወር እንደሚነግሰው በዓል ሁሉ ለጥምቀት በዓል የሚመጣው ህዝብ ይህን የአደባባይ በዓል ለመታደም እና ለመቅረጽ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማችን በመምጣት በዓሉን ይታደማሉ፡፡ ይህም በየጊዜው የጎብኚዎችን ቁጥር እንዲጨምር የራሱ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡
ሌላው የከተማው ትልቁ መስህብ ሀይቁ ነው፡፡ የሀዋሳ ሀይቅ ለኛ ትልቁ በረከታችን ነው፡፡ አቀማመጡ ለሁሉም የተመቸ ነው፡፡ ስለዚህ ታቦታቱ በሀይቁ ሲሄድ መንፈሳዊ ውበት አለው፡፡ ዝማሬ፣ አምላክን ማገልገል ለተመልካች ልዩ እርካታን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ ጀልባዎች በሥርዓቱ ላይ ታቦታቱን ይዘው ሲሄዱ ማየት ልዩ የሆነ ውበትን በመፍጠር የምዕመናኑንም ሆነ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛ ነው፡ የዚህ ሁነት መፈጠር በዓሉን ከማክበር ባለፈ ለዓለም የማስተዋወቅ እንዲሁም የሀይቁን ጥቅምም በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራበታል፡፡ በዓለም ደረጃ እንደመታየቱ ሀዋሳ የፍቅር ከተማ መሆኗን የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቤተክርስቲያናችንን ያለበት ሥፍራ አስተዋውቆልናል፡፡
ንጋት፦ በሀይቅ ላይ ጉዞ ከተጀመረ ወዲህ የቤተክርስቲያን እድገት ምን ይመስላል?
ቀሲስ ተዋበ፦ የደብረ መድሐኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሎቄ ሆስፒታል አለፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቦታው ለወደፊት ትልቅ እድገት የሚያሳይ ሥፍራ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑም ሀይቁ አጠገብ መሆኑ ትልቅ ገጽታን ፈጥሯል፡፡ ለጥምቀት በዓልም ታቦታቱ ከየብስ ይልቅ በሀይቅ ላይ በመሄዱ ቤተክርስቲያኒቱን ከማስተዋወቅ ባሻገር በርካታ ምእመናን ቤተክርስቲያንን እንዲጎበኙ አድርጓል፡፡ ለዚህም የጀልባ ባለቤቶች ቅንነትና ደግነታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ አገልግሎቱን በነፃ ነው የሚሰጡት፡፡ እኛ ነዳጁን እንዲያገኙ የማስተባበር ሥራ ነው የምንሰራው፡፡ ይህ ትልቅ በረከት ነው፡፡
በጥምቀት በዓል በሚከወነው የሐይቅ ላይ ጉዞ በመጀመሩ ቤተክርስቲያኒቱ በህዝቡ ዘንድ ትኩረት አግኝታለች፡፡ ቦታው ህዝብ የሚባረክበት እና የበረከት እንደመሆኑ መጠን ቤተክርስቲያናችን በሚገባ ተዋውቋል ማለት ይቻላል፡፡
የጥምቀት በዓል አከባበራችን ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት ከክልል ቢሮ ጀምሮ የሚመለከታቸው ተቋማት በተለይም ደግሞ የከተማው ከንቲባ እና መላው አመራርና ሰራተኞች እጅግ በትህትና በቅንነት ቤተክርስቲያን ለዚህ አገልግሎት የኛ ነው በማለትና ቦታው ድረስ በመሄድ በማጽዳት ጭምር ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል፡፡ በሀይቁ ላይ የጀልባ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ድጋፍ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለተቋማቱ ምስጋና ታቀርባለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከነዳጅ አገልግሎት አንፃር ጀልባዎች ነዳጅ እንዲያገኙ እና በበዓሉ እለት የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር ነዳጅ በመፍቀድ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለበዓሉ ድምቀትም ሆነ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የቱሪዝም ፍሰት ትልቅ ድርሻ ያበረከቱ በመሆኑ ለመንግስት አካላትና ተባባሪ ድርጅቶች ከፍተኛ ምስጋና አለን፡፡
ንጋት፦ በዓሉን በሰላም ለማክበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ምን ይመስላል?
ቀሲስ ተዋበ፦ የጥምቀት በዓል በሰላምና በድምቀት እንዲከበር የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ የሚመለከተው ተቋም አገልግሎትን በቅንነት በመስጠት በዓሉ በፍቅር እንዲከበር እየተሰራ ይገኛል፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ጥምቀት በሰላምና በፍቅር ሲከበር እንደነበረው ሁሉ አሁንም ይበልጥ ተሽሎና ደምቆ እንዲከበር ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
ንጋት፦ የቤተክርስቲያኗ እድገት እና በልማት ያላት ተሳትፎ እንዴት ይገልጹታል?
ቀሲስ ተዋበ፦ የሀዋሳ ደብረ መድሐኒት መስቀለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለውጥ እያመጣች ትገኛለች፡፡ ለዚህም የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ይገኛል፡፡ የአካባቢው ሰዎች እና የከተማ አስተዳደርም ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል፡፡ በዚህም ቀድሞ ከነበረው የቤተክርስቲያኗ መሬት አሁን ላይ ስፋቱ ሰባት ሺህ ካሬ ደርሷል፡፡ አሁንም በራስ አገዝ እየፈጠረች እየሰራች ያለች ሲሆን ትልቅ እድገት ላይ ትገኛለች፡፡ በየአመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓልም ብዙ ገጽታ እንዲኖራት ያስቻላት ሲሆን የምእመናን ቁጥርም እየሰፋ መጥቷል፡፡
መብራትና ውሃን ጨምሮ አንዳንድ መሰረተ ልማቶች ከቤተክርስቲያኗ መመስረት ጀምሮ ተሰርተዋል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ በዚህ ተጠቅሟል፡፡ ልማት በትብብር እየተሰራ ሲሆን በቀጣይም ለመስራት የታሰቡ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡
ከዚህ ሌላ የአካባቢው ህብረተሰብ የቤተክርስቲያኗ መሬት እንዲሰፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ መሬት በመስጠት እንዲሁም ይዞታቸውን በቅናሽ በመሸጥ ትብብራቸውን አሳይተዋል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያኗ ወደ አካባቢው በመምጣቷ አካባቢው የልማት አገልግሎት ማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ሰዎች ወደ አካባቢው የመስፈር ሁኔታ በመኖሩ ወደ ከተማነት ማደግ ችሏል፡፡
ቤተክርስቲያኗ ብዙ እቅዶች አሏት። ከነዚህም ውስጥ የሀይቁ ዳር ማልማት እንፈልጋለን፡፡
ሀይቁ ላይ የጽዳት ሥራ መስራት፣ በአካባቢው ቤተ መጽሐፍ እንዲሁም በጎ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፤ ከዚህ ሌላ መንፈሳዊ የመዝናኛ አገልግሎት፣ በአካባቢው ላይ ትምህርት ቤት ከመስራት በተጨማሪም ሀይቁ ላይ የራሳችን ጀልባ እንዲኖረን አቅደናል፡፡
እንደ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የአካባቢው ንጽህና በተመለከተ ቀደም ሲል ቆሻሻ ይጣል ነበር፡፡ አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት ጸድቷል፡፡ ሌላው የቦታ ጥበት ነበረብን ይሁንና ከሚመለከታቸው ጋር በመስራት ተጽእኖ የሚፈጥሩብንን ነገሮች እናስተካክላለን የሚል እምነት አለን፡፡
ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ እንዲገልጹ እድሉን ልስጥዎት
ቀሲስ ተዋበ፦ በሀገራችን ከሚገኙ በርካታ የቱሪስት መሰህቦች ውስጥ አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ ይህ የአደባባይ በዓል በሁሉም አካባቢ ይከበራል፡፡ በሀዋሳ ላይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከሌሎች የሚለየው በጎዳና እና በሀይቅ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ለበዓሉ የተለየ ገጽታ ፈጥሯል፡፡ ከዚህ አኳያ በየጊዜው በዓሉ ላይ የሚታደሙ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል፡፡ ለወደፊቱም ይህን አካሄድ የበለጠ በማዘመን ወደ ፍቅር ከተማችን የሚመጣውን ጎብኚ ቁጥር ማሳደግ ይጠበቅብናል እላለሁ፡፡
በመጨረሻም እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን እያልኩ በዓሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያላችሁ እግዚአብሔር አምላክ በዓሉን የበረከት ያድርግልን እላለሁ፡፡ አሜን
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
ቀሲስ ተዋበ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

More Stories
“ጠንክረን ከሰራን ሰዎችን መሳብ እንችላለን” – መምህር ቃልኪዳን መንክር
የቱሪስት መዳረሻዎች – በሲዳማ ክልል
የጉዞ ጅማሮ