አማራጭ የኢነርጂ ልማት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

አማራጭ የኢነርጂ ልማት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

በምንተስኖት ብርሃኑ

እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለመመለስ መንግስት ከውሃ፣ ንፋስና ፀሐይ ኃይል የሚመነጩ አማራጭ ልማት ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከአምስት ሺህ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀውን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም ለዜጎች እና ኢንደስትሪዎች የሚያስፈልገውና የኤሌክትሪክ ኃይል ከማዳረስ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እየተቻለ ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገው ጥረትም አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ እየተሰራ ባለው የኤሌክትሪክ ኃይል የማዳረስ ሥራ የገጠሩንም ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ ዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር /ግሪድ/ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የገጠር ቀበሌያትን ከዚህ መስመር የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የገጠሩን ሕዝብ የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት እንደ ፀሐይ ኃይልና ባዮ ጋዝ ባሉ የኢነርጂ አማራጮች ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ከ200 የማያንሱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ሕዝብ ለማድረስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይሁን እንጂ እስከ አሁን በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ማድረግ የተቻለው ከሀገሪቱ ሕዝብ 54 በመቶውን ብቻ ስለመሆኑ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ የገጠሩን ሕዝብ በስፋት ማዳረስ ባለመቻሉ ከ90 በመቶው በላይ አሁንም የሚጠቀመው ማገዶ መሆኑንም መረጃው ያመላክታል፡፡

በመሆኑም የገጠሩን ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በፀሐይ እና በባዮ ጋዝ ኃይል ልማት ላይ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ እንደ ትምህርት፣ ጤናና የመሳሰሉ ተቋማትና ግለሰቦች የሶላር ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ ኃይልን ከብክነት መታደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ሕዝብ የማድረሱ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ለእዚህም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማውጣት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ አምጥቶ ማላመድ ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ሥራ እስከ አሁን ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን የተሻሻሉ የምድጃ ቴክኖሎጂዎች መሰራጨታቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህንን አሃዝ እስከ 2030 ድረስ ወደ 31 ነጥብ አምስት ሚሊየን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡ ዘንድሮ ወደ ሁለት ሚሊየን የተሻሻሉና ንጹህ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት ታቅዷል፡፡

ክልሎችም በተመሳሳይ ይህንኑ በማድረግ ላይ ስለመሆናቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለው እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ አማራጭ የኢነርጂ ልማትና ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ተከተል ማቴዎስ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ከሀገሪቱ የገጠር ሕዝብ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚጠቀመው ኢነርጂ ማገዶና የመሳሰሉትን /ባዮ ማስ/ በመሆኑ የዚህን ኢነርጂ አጠቃቀም ማሻሻል ብዙ ለውጥ ማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

ለዚህም ቀደም ሲል ተሞክረው ሥራ ላይ የዋሉ ጥቂት የምድጃ ዓይነቶችን ቁጥር፣ አሁን ላይ ወደ 26 ማድረስ መቻሉን አመላክተዋል፡፡ ጠጣር /ሶሊድ/ የባዮ ማስ ኢነርጂ ገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም እንደሚሰራበት እና የዚህን አጠቃቀም ማሻሻል ፋይዳው ብዙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ከቴክኖሎጂው ፋይዳዎች መካከልም ደንን ከመጨፍጨፍ ማዳን፣ ቤት ውስጥ የሕፃናትንና የእናቶችን ጤንነት መጠበቅ፣ የማገዶ ወጪን መቆጠብ፣ የካርቦን ፋይናንስ ማግኘት የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ምድጃዎችን ከሚያመርቱት አኳያ ሲታይ ደግሞ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ሥራው ይበልጥ እየተጠናከረ መሄድ ይኖርበታል፡፡

እንደ ሀገር ከውሃ ኃይል የማመንጨት ሥራ ትኩረት እደተሰጠው አስታውሰው፤ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተሰሩ ማለት ግን ሁሉንም ዜጋ በአንዴ በየቤቱ ይደርሳል ማለት አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱም የኛ ሕዝብ የተበታተነ በመሆኑ በቤተሰብ ደረጃ የምንጠቀማቸውን ቴክኖሎጂዎችን ጎን ለጎን ማስኬድ ይኖርብናል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ክልሉ ሶላር ላይ በስፋት እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ላይ ጂ.አይ.ዜ.ድን ጨምሮ ከሌሎች አጋሮች ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ በገጠር በጤናና በትምህርት ተቋማት በኩል የሚሰራም አለ የሚሉት ኃላፊው፤ በቀላሉ ኃይል በማይደርስባቸው የገጠር አካባቢዎች ደግሞ በሶላር ሚኒ ግሪድ አማካይነት ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአነስተኛ ወንዞች ላይ ኃይል የማልማቱ ሥራ ቀጥሏል የሚሉት ዳይሬክተሩ በዚህ ላይ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት በኩል እየተሰራ ይገኛል፡፡ በቤተሰብ ደረጃ እንደ ሶላር ሩም ሲስተም ያሉ ሥራዎች በስፋት የሚሰራባቸው ሲሆን እነዚህ በግለሰብ ደረጃ የሚሰራባቸው መሆናቸውን አመላክተዋል። ሌሎች ሶላር የሚያሰራጩ አካላትን አቅም የማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በማከል፡፡

ሶላር በገጠር በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቴክኖሎጂውን ለመስኖ ሥራ የማዋል፣ እንደ ጸጉር አስተካካዮች ያሉት ደግሞ ለገቢ ምንጭ ማግኛነት እየተጠቀሙበት መሆናቸውን እና በጣም ንጹህ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ዘመኑም ወቅቱም ነው ብለዋል፡፡

ባዮ ጋዝን መጠቀም በተመለከተ፣ በክልል ደረጃ አዋጭ በሆኑ አካባቢዎች የባዮ ጋዝ ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ሶሊድ ባዮ ጋዝ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ቁጠባ የግድ መሆን አለበት በሚል እሳቤ እየተሰራበት ነው ይላሉ፡፡

በሀገር ደረጃ ወደ 48 ሺህ የሚደርሱ ባዮ ጋዞች መገንባታቸውን እና በክልሉ እሰከ አሁን ሁለት ሺህ 300 አካባቢ የቤተሰብ ባዮ ጋዞች ተገንብተዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በየዓመቱ ብዙ ቴክኖሎጂዎች ይሰራጫሉ። በ2016 ወደ 40 ሺህ አካባቢ ሶላር ላንትሪን እንዲሁም ወደ 60 ሺህ ሆም ሲስተም መሰራጨቱን ጠቅሰዋል፡፡ ሰዎች ከኩራዝ መውጣት ስለሚፈልጉ በህብረተሰቡ ዘንድ የሶላር ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማሰራጨት በማስፈለጉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሶላር ላይ ትልቁ ችግር አስመጪዎች አካባቢ ያለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቴክኖሎጂ ማላመድ ላይ ብዙ ትኩረት እየተሰጠ እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ ሥራ ላይ ያሉት ምርጥ ምድጃዎች የቆዩ በመሆናቸው ይህን ማሻሻል፣ ሶላር አስመጪዎች በሰፊው የሚያመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

መጸዳጃ ቤቶች ጭምር ለባዮ ጋዝነት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን አስታውቀው፣ ይህ ሲሆን ከሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች የሚቀንሱበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ገልጸዋል፡፡ የባዮ ጋዝ ልማት ከአካባቢ ጋር ተያይዞ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡

የቆጣቢ ምድጃ ፋይዳ ብዙ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ የደን መጨፍጨፍን መቀነሱ በራሱ አካባቢን ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ 50 በመቶ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ ተጠቀምን ማለት 50 በመቶ ደን ቆጠብን ማለት ነው ሲሉም ፋይዳውን አብራርተዋል፡፡ ደኑን ከማዳን በተጨማሪ ማገዶው ሲቀጣጠል የሚለቀቀውን ካርቦን መቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ከሰው ጤና፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከቤተሰብ ጋር ተይይዞ የሚሰራ በመሆኑ ፋይዳው ዘርፈ-ብዙ በመሆኑ በክልሉ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

All reactions:

1818