በ2017/18 የመኸር አዝመራ ምርት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከ1 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በፀደይ አዝመራ ለመሸፈን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን በስልጤ ዞን የሁልባራግ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በ2017/18 የመኸር አዝመራ ምርት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከ1 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በፀደይ አዝመራ ለመሸፈን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን በስልጤ ዞን የሁልባራግ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው በመኸር ያለሙት ማሳ ምርት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን የፀደይ አዝማራ የሚሆን ማሳ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2017/18 የመኸር አዝመራ ወቅት 6 ሚሊየን 8 መቶ 21 ሄክታር ማሳ በስንዴ፣ በበቆሎ በጤፍ እና በሌልችም የአዝርዕት አይነቶች የተሸፈነ ሲሆን 80 ከመቶው በክላስተር የአስተራረስ ዘዴ የለማ መሆኑን የሁልባራግ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል ጀማል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የበቆሎን ማሳን ጨምሮ 250 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ የስንዴ ክላስተር ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት።

አሁን ላይ የተሰበሰበው እና በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የመኸር አዝመራ ምርታማነት ለመጨመር ከቅድመ መኸር ጀምሮ በየቀበሌው ክላስተርን መሰረት ያደረገ የበሽታ መከላከል እና የአረም ቁጥጥር ስራ መሰራቱን አቶ አወል ተናግረዋል።

በተወሰኑ የስንዴ ማሳ ላይ የተከሰተውን የዋግ በሽታ ኬሚካል በመርጨት በፍጥነት ከመከላከል በተጨማሪ ወደሌላው ማሳ እንዳይዛመት የእለት ተዕለት የክትትል እና ቁጥጥር ስራ በመሰራቱ በምርት ዘመኑ የተሻላ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ከምርት አሰባሰብ ጎን ለጎን የወረዳውን የአየር ፀባይ መሰረት ባደረገ መልኩ የፀደይ አዝመራ መጀመራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ወረዳው ሶስት አይነት አግሮ ኢኮሎጂ የአየር ፀባይ ያለው ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም የአየር ፀባይ መሰረት አድርጎ የሚለማ የሽምብራ እና የጓያ አዝዕርት አርሶ አደሮች እንዲያለሙ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቶ ወደ ተግባር ተገብቶዋል ነው ያሉት፡፡

በወረዳው በዘንድሮው የፀደይ አዝመራ 1 ሺ 1 መቶ 96 ሄ/ር ማሳን ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን ያነሱት አቶ አወል፤ አርሶ አደሮች የመኸር ማሳ ምርት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን የፀደይ አዝመራ ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የፀደይ አዝመራ ብዙ የሰው ጉልበትና ጊዜ የማይፈጅ በመሆኑ ሁሉም አርሶአደሮች ፆሙን የሚያድር ማሳቸውን በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን በፀደይ አዝመራ በመዝራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የተቻላ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ አወል ጀማል ተናግረዋል።

በወረዳው አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች በመኸር አዝመራ ያለሙትን የደረሰ ማሳቸውን ምርት በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመኸር አዝመራ ወቅት ለማሳቸው አስፈላጊውን ክትትልና እንክብካቤ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያነሱት አርሶ አደሮች ከሌሎች ጊዜያት የተሻላ ምርት እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ከምርት አሰባሰብ ጎን ለጎን ለፀደይ አዝመራ የሚሆን ማሳቸው አዘጋጅተው ወደ ተግባር መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን