“አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው” – ወጣት ታምራት አማረ 

“አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው” – ወጣት ታምራት አማረ 

በአለምሸት ግርማ

አካል ጉዳተኝነት ማንንም ሰው ሊጋጥም የሚችል ሲሆን፤ ችግሩን አምኖ በመቀበል ለስኬት መብቃት ግን የግለሰቡ የጥንካሬ መገለጫ ነው። የዛሬው የችያለሁ አምድ ማሳያችን በወጣትነት ዕድሜው ነው ጉዳቱ የደረሰበት። ነገር ግን ለምን ጉዳት ደረሰብኝ ከማለት ይልቅ ጉዳቱን አምኖ በመቀበል ጠንክሮ በመማርና በመስራት ህይወቱን እየመራ የሚገኝ ጠንካራ ወጣት ነው። ተሞክሮውን እንዲህ አካፍሎናል፦

ወጣት ታምራት አማረ  ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ሐረር ሲሆን፤ ለቤተሰቡ ሶስተኛ ልጅ ነው። ልጅነቱን ያሳለፈው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው። ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እስከ ሰባተኛ ድረስ ምዕራብ ሐረርጌ ከአሰበ ተፈሪ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሒርና ከተማ ”ሒርና ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በተለምዶ ኢትዮጵያ ትቅደም(ሐይሉ ትምህርት ቤት)” ነው። ወደ ስምንት ሲሸጋገር ወላጅ አባቱ በስራ ምክንያት ወደ ገብረ ጉራቻ ከተማ ተዘዋወሩ። የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱንም ገብረ ጉራቻ ቁጥር ሶስት ትምህርት ቤት” በመግባት ሚኒስትሪ ተፈትኗል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያው ገብረ ጉራቻ ከተማ በሚገኘው ”ገብረ ጉራቻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት” እስከ አስረኛ ክፍል ተከታትሏል። በአጋጣሚ የአስረኛ ክፍል ውጤቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ቴክኒክና ሙያ በመግባት ብረታ ብረትና ማኑፋክቸሪንግ በዲፕሎማ ተመረቀ። በዚያ ወቅት ነበር አባቱ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀው ሃዋሳ መምህራን ኮሌጅ የሚገቡበት አጋጣሚ የተፈጠረው። ከጥቂት ቆይታ በኋላ በተማረበት ሙያ ዱከም ከተማ ስራ በማግኘቱ ወደዚያ አቀና።

ዱከም ከተማ “አርቲ ቆርቆሮ ፋብሪካ” እየተገነባ ባለበት ወቅት ነበር የስራ ዕድል ያገኘው። በፋብሪካው የብረታ ብረት ብየዳ እና ማሽን ማሳረፊያ ውስጥ ስራ በመቀጠር ኑሮን በጀመረበት ወቅት ነበር ያላሰበው አካል ጉዳት የገጠመው። በወቅቱ ፋብሪካ ውስጥ እየሰራ ስድስት ወራትን በሰላም አሳልፏል። እሱም ስራውን በታታሪነት እየሰራ በነበረበት ሒደት ላይ በ2004ዓ.ም  ከዕለታት በአንዱ ቀን የተሽከርካሪ አደጋ ደረሰበት። በአደጋው የቀኝ እግሩንና ሌሎች ጉዳቶች ተጠቂ ሆነ። ከዚያም ለህክምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብቶ ህክምናውን ሲከታተል ቆየ። በመቀጠልም የካቲት 12 የፕላስቲክ ሰርጀሪ ለማሰራት ቢያስብም፥ በሀኪሞች የምርመራ ውጤት አጥንቱ መጎዳቱ ስለተረጋገጠ እግሩ እንዲቆረጥ ተወሰነ። በዚያ መሰረት ለአንድ ዓመት ያህል የእግሩንና ተያያዥ ህክምናውን ተከታትሎ በማጠናቀቁ  ወደ ሃዋሳ መጣ።

ከህመሙ ለማገገምና ወደ ስራ የሚገባበትን አቅም ለማሰባሰብ የተወሰኑ ጊዜያትን በቤት ውስጥ አሳልፏል። ከቆይታ በኋላ በ2009ዓ.ም ሃዋሳ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ በመግባት ሀርድዌር ኤንድ ኔትወርክ ሰርቪስ በደረጃ አራት ለሁለት ዓመታት ተከታትሎ በ2011 ዓ.ም አጠናቀቀ።

በመቀጠልም ዕውቀቱን ለማሳደግ በማሰብ በዲግሪ መርሃ ግብር ኢንፎሊንክ ኮሌጅ ሃዋሳ በኮምፒውተር ሳይንስ በ2012 ዓ.ም መማር ጀመረ። ትምህርቱን በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብር በሚገባ ከተከታተለ በኋላ በ2015 ዓ.ም መመረቅ ችሏል። ይሁን እንጂ ከሰኞ እስከ አርብ ያሉትን ቀናት እንዲሁ በዋዛ አላሳለፈም። በጉዳቱ ምክንያት የተሰጠውን የኢንሹራንስ ገንዘብ እንዲሁም ከቅርብ ሰዎች በመበደር ባጃጅ ሊገዛ ችሏል። ባጃጁንም ታላቅ ወንድሙ እየሰራ ራሱንም ቤተሰቡንም ያግዝ ነበር።

ይሁን እንጂ፥ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ የባጃጁ ስራ እንደፈለጉት አዋጪ አልሆነላቸውም። ከገቢው ይልቅ ወጪው እየጨመረ ሲመጣ ባጃጁን ለመሸጥ ወሰኑ። ባጃጁ ከተሸጠ በኋላ ከሰው የተበደረውን ገንዘብ በመመለስ በቀሪው በቤተሰብ ቤት በር ላይ የሱቅ ስራ ጀመረ። በስራው ብዙ ትርፍ ባያገኝም መስራት በመቻሉ ደስተኛ መሆን ችሏል። የሚያገኘው ገቢም የትምህርቱን ከፊል ወጪ እንዲሸፍን አስችሎታል።

ወላጅ እናቱ የቤት እመቤት ሲሆኑ፤ አባቱ ደግሞ መምህር እንደሆኑም አጫውቶናል። የተወለደበት ከተማ እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በስራ ዝውውር ምክንያት በገብረ ጉራቻ ከተማ ኑሯቸውን አደረጉ። በመቀጠልም አባቱ በትምህርት ራሳቸውን በማብቃታቸው ሃዋሳ መምህራን ኮሌጅን በመምህርነት ተቀላቅለው በ2002 ዓ.ም ቤተሰቡ በሙሉ ወደ ሃዋሳ መምጣቱንም አጫውቶናል።

በአሁኑ ወቅት ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ ሲሆን፥ የሱቅ ስራውንም አላቋረጠም። እኛም ባገኘነው ወቅት ቼሻየር ኢትዮጵያ ሃዋሳ ቅርንጫፍ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ እየተሳተፈ ባለበት ወቅት ነው።

የስልጠናውን ዕድል እንዴት እንዳገኘም እንዲህ በማለት አጫውቶናል፦

“ስለቼሻየር ኢትዮጵያ እሰማ ስለነበር ድጋፍ ቢያደርጉልኝ ብዬ ነበር ወደ ማዕከሉ የመጣሁት። ነገር ግን እነሱ የገንዘብ ድጋፍ ብዙም እንደማያደርጉ ነግረውኝ የምሰራበትን ቦታ መጥተው ከጎበኙ በኋላ ስልጠና እንዳገኝ ዕድሉን አመቻቹልኝ። ስልጠናውም ለስራዬ እንዲሁም ለህይወቴ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን አግኝቼበታለሁ።”

ወደ ፊት ስራውን ማሳደግ እና ማስፋፋት ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሞክሮ ያልተሳካለትን የመውጫ ፈተና (ኤግዚት  ኤግዛም) በማለፍ በሙያው መስራት እንደሚፈልግም አጫውቶናል። እንዲሁም ቤተሰቡንም ለማገዝ ስለሚፈልግ ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

“አካል ጉዳተኝነት ሰው ፈልጎ የሚያመጣው አይደለም። እኔ ጉዳት ሲደርስብኝ የተቸገርኩት ከጉዳት በፊት የሚያውቀኝ ማህበረሰብ መካከል፥ ከጉዳት ጋር ሆኜ መቀላቀል ትልቁ ጭንቀቴ ነበር። በራሴም እንዳየሁት ለአካል ጉዳተኛ የመጀመሪያ ተግባር መሆን ያለበት ጉዳትን አምኖ መቀበል ነው።

አካል ጉዳተኝነት መስራት አለመቻል አይደለም የሚለውን አባባል አምንበታለሁ። ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ስለሆኑ ብቻ ራስን ከስራ ማግለል ተገቢ አይደለም። የሰው ድጋፍ ማግኘት መስራት አያስችልም፤ ድጋፍ አለማግኘትም መስራት አይከለክልም። አንዳንድ በቅርበት ከማውቃቸው አካል ጉዳተኛ ወዳጆቼ መካከል መጠነኛ ጉዳት እያለባቸው ስራ መስራት የማይፈልጉ አሉ። ጉዳታቸውን እንደምክንያት በመጠቀም ከስራ የመሸሽ ፍላጎት አይባቸዋለሁ።

አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው። ሁለቱንም አውቀዋለሁ፤ አካልጉዳተኛ ሲኮንና ሳይኮን ያለው አመለካከት ይለያያል። ቢሆንም ግን አካል ጉዳት አንዴ ከደረሰ በኋላ የሚመለስ ባለመሆኑ ያለውን ችግር አምኖ ተቀብሎ መኖር ግን ያስፈልጋል። እናቴ ’ከሔደው ይልቅ ያለው ጠቀመኝ‘ ትላለች እኔም ያጣሁትን አካሌን መልሼ ስለማላገኘው፥ ያለውን በአግባቡ በመያዝ እየኖርኩ ነው። ስለዚህ አካል ጉዳተኞች ከአካል ጉዳታቸው ጋር የሚስማማና የሚችሉትን ስራ በመስራት ቢኖሩ መልካም ነው በማለት ምክሩን ለግሷል”

“በአካሌ ላይ ጉዳት በመድረሱ የምገደብበት ነገር ቢኖርም፤ በአካል ጉዳተኝነቴ ያጣሁት ወይም የደረሰብኝ የከፋ ነገር ግን የለም። አልፎ አልፎ ያልተቀረፉ የአመለካከት ችግሮች አሉ። በአንድ ወቅት ዲፕሎማዬን እንደጨረስኩ የቅጥር ማስታወቂያ ወጥቶ ተወዳደርኩ። ነገር ግን ፈታኞቹ ሲመለከቱኝ ‘ስራው ላንተ ይሆንሃል እንዴ? ይመችሃል?’ ብለው ጠየቁኝ። እኔም ስራውን ስጡኝና ከከበደኝ አስወጡኝ አልኳቸው። እሺ እንደውላለን ብለው ሸኙኝ፤ ከዚያም ሳላልፍ ቀረሁ። አንዳንዶች ፊት ለፊት ባይናገሩም፤ ግን አትችልም የሚለውን በድርጊት የሚያንፀባርቁ አሉ። በአንፃሩ  ጓደኞቼ ግን ጉዳቴን እንዳላስበው ትልቅ ነገር አድርገዋል። በመንፈሳዊ ዓይን ስመለከተው ደግሞ ጉዳቴ ለበጎም ሊሆን ይችላል።

“ነገር ግን አካል ጉዳት ስላለ ብቻ አለመስራት ተገቢ አይደለም። ከጉዳት ጋርም በመሆን የምንችለውን ጥረት ማድረግ አለብን። ሙከራ ሳናደርግ በፍርሃት የምንቀመጥ ከሆነ ሁልጊዜ የሌሎች ጥገኛ እንሆናለን።

“አንዳንዶች አካል ጉዳተኛን ሲያዩ ለልመና የቆመ የሚመስላቸው አሉ። በተደጋጋሚ አጋጥሞኝ ያውቃል፤ ሰው ለመጠበቅ በቆምኩበት ብር ሊሰጡኝ እጃቸውን የዘረጉልኝ ሰዎች አሉ። እኔም ነገሩን ከግንዛቤ ክፍተት እንደሆነ ተረድቼ አልፋለሁ። ይህ ማለት ግን በህብረተሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ የለም ማለት አይደለም። ብዙ ለውጦች አሉ፤ በትራንስፖርት እንዲሁም በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ቅድሚያ የመስጠት ነገር እየተለመደ መጥቷል ይህም ሊመሰገን፣ ሊበረታታና ሊቀጥል ይገባል።

ጉዳት ሁሉም በትከሻው ይዞት የሚኖረው ነገር ነው። ማን፣ መቼ፣ ምን፣ እንደሚገጥመው አናውቅምና ተሳስቦ መኖሩ የጋራ ጥቅም አለው” በማለት ነው የተናገረው።

ማመስገን የሚፈልገው አካል ካለ ዕድሉን ሰጥተነው እንዲህ ብሏል፦

“ከሁሉም በላይ በነገር ሁሉ የረዳኝን ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። ልጅነቷን ያጣችብኝ፣ ብዙ ጉዳቶችን ከእኔ ጋር ያሳለፈችውን፣ እኔን ስታስታምም ለህመም የተጋለጠችውን እናቴን(እቴነሽ ሞገስ) ‘የእናትና የልጅ ፍቅርና፥ የጅረት ውሃ ከላይ ወደታች እንጂ ከታች ወደላይ አይፈስም’ እንደሚባለው ምንም አድርጌ ውለታዋን መክፈል ባልችልም፤ ግን በጣም አመሰግናታለሁ። አባቴ በመንፈሳዊ ህይወት እንድበረታ፤ አደጋ ካጋጠመኝ በኋላ እንድጠነክር አድርጎኛል፤ እህትና ወንድሞቼም ከእኔ ጋር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፣ ተሰቃይተዋል፤ ሁሉንም አመሰግናለሁ። ጓደኞቼም በብዙ ከእኔ ጋር ደክመዋልና ሁሉንም አመሰግናቸዋለሁ ዕድሜና ጤና ለሁሉም ይስጥልኝ” ሲል ምስጋናውን አቅርቧል፡፡