በአለምሸት ግርማ
የሰው ስኬቱ የሚጀምረው ከአስተሳሰቡ ነው። ትልቅ ዓላማ የሰነቀ ሰው እንቅፋት ወይም ፈተና አያስቆመውም። ሩቅ የመድረስ ህልም ስላለው በሚያጋጥሙት ፈተናዎች በመቆዘም ጊዜውን አያባክንም። አንዳንዶች በሚያጋጥማቸው ትንንሽ ፈተናዎች ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ አልያም ዓላማቸውን በመዘንጋት በህይወታቸው ለውጥ ማምጣት ሲያቅታቸው ይታያል። በአንፃሩ አንዳንዶች ደግሞ ምንም ተስፋ በሌለበት ቦታ ዓላማቸውን ብቻ በማሰብ ስራን ሳይንቁ በመስራትና ፈተናዎቻቸውን በመጋፈጥ የትጋታቸውን ፍሬ ይበላሉ። የዛሬዋ እቱ መለኛችንም ገና ታዳጊ ወጣት ብትሆንም በፊቷ ላይ የሚነበበው ጥንካሬና የስራ ተነሳሽነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው።
ተማሪ እርቅነሽ ስንታየሁ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በሲዳማ ክልል ቦና አካባቢ ነው። ልጅነቷን እዚያው በተወለደችበት ስፍራ ያሳለፈች ሲሆን፥ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም መደበኛ ትምህርት እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ እዚያው ቦና ነው የተማረችው።
ለትምህርቷ ከፍተኛ ፍቅር ስላላት በሚገባ በመማርና በማጥናት ነበር ጊዜዋን የምታሳልፈው። ተምራ ወላጆቿንና ወንድም እህቶቿን የማገዝ ጥልቅ ፍላጎትም እንዳላት አጫውታናለች።
ከአራተኛ ወደ አምስተኛ ክፍል ስትዘዋወር ነበር ወደ ሃዋሳ የምትመጣበት አጋጣሚ የተፈጠረው። የመጣችበትም ምክንያት ወንድሞቿ ቀድመው መጥተው ስለነበር እሷም እንደእነሱ ስራ እየሰራች ለመኖር የሚል ዓላማ መሰነቋ ነው።
ከዚያም ሃዋሳ መጥታ ሰው ቤት በመቀጠር ቀን ስራዋን እየሰራች ማታ ትምህርቷን ትማር ነበር። ስራው አድካሚ ቢሆንም ትምህርቷን ግን አላቋረጠችም። ይልቁንም ከትምህርት ቤት መልስ የሚሰጣትን የቤት ስራ በመስራትና የተማረችውን በማጥናት ነበር የምታሳልፈው። በዚያም ሁኔታ ከተቀጠረችባቸው ሰዎች ጋር ተስማምታ በመኖር ቆየች። ንግስት ፉራ ትምህርት ቤት ገብታ ትምህርቷን መከታተል ቀጠለች።
ከቆይታ በኋላ ከወንድሞቿ ጋር በመመካከር የሰው ቤት ስራውን ለማቆም ትወስናለች። “የሰው ቤት ስራ አድካሚና ዕረፍት የሌለው ነው” በማለት ነበር በወቅቱ የነበረውን ስሜት የገለፀችው። በውሳኔዋ መሰረት ከምትሰራበት ቤት ወጥታ ኑሮዋን ከወንድሞቿ ጋር ትጀምራለች።
ታላቅ ወንድሟ ጫማ ማስዋብና ማፅዳት ስለሚሰራ ስራው እንዴት እንደሚሰራ አጠገቡ አስቀምጦ እንድታይና እንድትማር ማድረግ ጀመረ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ስራውን ቀስ በቀስ እየለመደች መጣች። ስራውን በደንብ ስትለምድ በራሷ መስራት ጀመረች። ወንድሟም በቅርብ ርቀት ሆኖ ክትትል ያደርግላታል።
በአሁኑ ወቅት በስራዋ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችላለች። ስራዋን በጥንቃቄ ስለምትሰራ ደንበኞቿ እየበዙ መምጣታቸውንም በደስታ ስሜት ሆና ነው የነገረችን። በምትሰራበት አቶቴ ታቦር መካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን አስፋልት መንገድ ዳር ባሰናዳችው የደንበኞቿ ማረፊያ ላይ የራሷን መልዕክት በወረቀት አስፍራ አንጠንጥላለች። በዚህም ስራዋን የምትሰራው መድረስ ለምትፈልግበት ዓላማ ስኬት እንደሆነ ከአክብሮት ጋር ገልፃለች።
ደንበኞቿም በስራዋ ደስተኛ እንደሆኑ ይነግሯታል። ያበረታቷታል። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶች ያልተገባ ንግግርና ድርጊት ለማድረግ የሚሞክሩ እንዳሉም አጫውታናለች።
ወደፊት ምን መሆን እንደምትፈልግ ጠይቀናት እንዲህ በማለት መልሳልናለች፦
“አሁን የምሰራው ትምህርቴን ለመማርና ወደፊት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ነው። ከተሳካልኝ ወደፊት የራሴን የንግድ ስራ መስራት ነው የምፈልገው። አምላኬ ሃሳቤን እንዲያሳካልኝ ሁሌም እየፀለየኩ ነው። ማለዳ ስነሳ መጀመሪያ ስራዬ በእምነቴ የማመልክበት ቤተክርስቲያን በመሔድ መፀለይ ነው። ከዚያ ተመልሼ ለወንድሞቼ ምግብ በማዘጋጀት ቁርስ በልተን ሁላችንም ወደ ስራ እንሰማራለን። አንድ ቀን አምላኬ የምፈልግበት ደረጃ እንደሚያደርሰኝ አምናለሁ።
“ስሰራ የሚያዩኝ ሁሉ ይባርኩኛል፣ ይመርቁኛል። እኔ የተገኘሁት እግዚአብሔር የሚወደው የስራ ቦታ ላይ ነው። መለመን ወይም መስረቅ ቢሆን አምላክን የሚያሳዝን ስራ ነው። ስለዚህ አምላኬ እንደሚረዳኝ አምናለሁ። ቀን ስራ ውዬ ማታ ትምህርቴን እየተማርኩ ነው። ወንድሞቼን ደግሞ ምግብ በማዘጋጀትና የቻልኩትን በማድረግ አግዛለሁ። በስራዬም በኑሮዬም ደስተኛ ነኝ። ዘንድሮ ዘጠነኛ ክፍል ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ ትምህርቴን እየተማርኩ እገኛለሁ።
“ስለዚህ እንደእኔ ያሉ ሴቶች ስራ ሳይንቁ ቢሰሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ። መቀመጥ እና ቤተሰብን ማስቸገር ተገቢ አይደለም። ሰርተው ቢኖሩ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸውም ይተርፋሉ።”
የስራ ትንሽ እንደሌለው የተማሪ እርቅነሽ ተሞክሮ ማሳያ ነው። በስራዋ በወር እስከ አራት ሺህ ብር ድረስ እንደምታገኝም አጫውታናለች። የምታገኘው ገቢም ከወንድሞቿ ጋር በመተባበር የቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን አስችሏታል። ከእሷ በኋላ ወደ ሃዋሳ የመጡ ታናናሽ ወንድሞቿንም የመንከባከብና የመከታተል ሃላፊነት እየተወጣች ትገኛለች። እንዲሁም ወደፊት መድረስ ለምትፈልግበት ደረጃ የሚያግዛትን መጠነኛ ቁጠባም ጀምራለች።
ከጫማ ስራው ጎን ለጎን ልብስ የማጠብ ስራ ትሰራለች። ደንበኞቿ በፈለጓት ሰዓት ሔዳ በማጠብ ተጨማሪ ገቢ ታገኛለች። በዚህም ደንበኞቿ ማበረታቻ ጉርሻ ይጨምሩላታል። ይህም የበለጠ ትጋትና ተነሳሽነት እንደሚፈጥርላት አጫውታናለች።
ጠንካራ የስራ ባህል ሰርቶ ለመኖር የምናሳየው ጠንካራ ፍላጎትና ልምድ ሲሆን፥ ሰዎች ያላቸውን የመስራት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ማለት ነው፡፡ ስራ የሰው ልጆች ሁሉ የመኖር ዋስትና በመሆኑ ጠንክረው ከሰሩ ከራስ አልፎ የቤተሰብንና የአካባቢን ኑሮ ለመለወጥ ወደሚያስችል ደረጃ ያሸጋግራል፡፡
ስራ ከአካባቢ በሚገኙ ነገሮች ላይ ተመስርቶ ከቀላል ነገር በመጀመር ጠንክሮ ከተሰራ ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማደግ ያስችላል፡፡ ጠንክሮ መስራት ሲባል በተሰማሩበት የስራ መስክ የተሻለ የምርት ውጤትን ማስገኘት ብቻ ሳይሆን የስራ ሰዓትን በማክበር፣ ሙያዊ ስነምግባርን በመላበስና የአገልጋይነት ስሜትን በማሳደግ ጭምር ይገለፃል።
ጠንካራ የስራ ባህል ስራን አለመናቅና ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለራስና ለሀገር የሚኖረውን ጠቀሜታ በተግባር ማሳየት ማለት ነው፡፡ ስራን አለመናቅ ሲባል የትኛውንም የስራ አይነት በእኩል ደረጃ መመልከትና ያገኙትን ስራ ሳይንቁ መስራት ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ የስራ አይነት ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይባል ትኩረት አግኝቶ ከተሰራ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡
ዛሬ ትንሽ ነው የሚባል አንድ ስራ ተገቢውን ትኩረት ካገኘ ነገ የሚሰራውን ሰው ከፍ ወዳለ እና ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ስራን ሳይንቁና ሳያማርጡ በመስራት ለውጤት የበቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ስራን መናቅ አይገባም። ሁሉም ስራ በጥሩ ሁኔታ ሊከናወን የሚችለው በዕቅድ በመመራትና ለወጣው የስራ ዕቅድ ራስን ማስገዛት ሲቻል ነው፡፡ የጊዜን አጠቃቀም በማወቅ ጠንክሮ የሚሰራ ዜጋ በቤተሰቡም ሆነ በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል፡፡
በየከተማው ከስራ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን በማየትና በጊዜያዊ መደለያ በመታለል ህይወታቸውን የሚያጡ ታዳጊ ወጣት ሴቶች በተበራከቱበት በዚህ ወቅት እንደወጣት እርቅነሽ በስራ ማመን ትልቅነት ነው። ሌሎች ከዚህች ጠንካራ ሴት ሊማሩ ይገባል መልዕክታችን ነው!

More Stories
የምርቃት በረከቶች
“ወባ በጣም ቀላል እና መከላከል የምንችለው በሽታ ቢሆንም ዋጋ አስከፍሎናል” – አቶ ፍሰሀ ለመዕንጎ
“ሥራን ማክበርና የሰውን ችግር መረዳት ልዩ ባህሪዬ ነው” – አቶ አወቀ ሲራክ አበጋዝ