ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን በማሸነፍ የሊጉ መሪ ሆነ

ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን በማሸነፍ የሊጉ መሪ ሆነ

በ8ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኤቨርተንን 2 ለ 0 በማሸነፍ በግዚያዊነት የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

ለማንቸስተር ሲቲ ሁለቱንም የማሸነፊያ ግቦች ኤርሊንግ ሀላንድ ከዕረፍት መልስ አስቆጥሯል።

ኤርሊንግ ሀላንድ 11ኛ የፕሪሚዬር ሊግ ጎሉን ነው ማስቆጠር ችሏል።

ኖርዌያዊው አጥቂ ለክለቡ እና ለብሔራዊ ቡድን ባለፉት 11 ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ማንቸስተር ሲቲ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 16 በማድረስ ከአርሰናል በግብ ክፍያ ተሽሎ የሊጉን መሪነት ጨብጧል።

በሌሎች ጨዋታዎች ብራይተን በሜዳው ኒውካስልን አስተናግዶ 2 ለ 1 ረቷል።

ለብራይተን ሁለቱንም ግቦች ዳኒ ዌልቤክ ከመረብ ሲያሳርፍ ኒክ ቮልትማደ ደግሞ ኒውካስልን ከሽንፈት ያልታደገችውን ጎል አስቆጥሯል።

ሰንደርላንድ ዎልቭስን እንዲሁም በርንሌይ ሊድስን በተመሳሳይ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ክርስቲያል ፓላስ ከቦርንማውዝ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 3 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ፕሪሚዬር ሊጉ ምሽት ላይ መካሄዱን ሲቀጥል አርሰናል   መሪነቱን መልሶ ለመያዝ በለንደን ደርቢ ከፉልሃም ጋር ከ1 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በክራቨን ኮቴጅ ይፋለማል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ