“በመምህርነቴ የሚሰማኝ እርካታ ከፍተኛ ነው” – መምህር ቆስቲ ስማ
በአብርሃም ማጋ
የዛሬው ባለታሪካችን መምህር ቆስቲ ስማ ሃሳባቸውን ያጠናከሩት የትልቅ ሥራ ባለሙያና አባት መሆናቸውን በመግለፅ ነው።
መምህርነት ታላቅ ሙያ መሆኑን ሲገልፁ በአጠቃላይ የዓለም ሚስጥር የሚፈተሸው በዋናነት በመምህሩ አማካይነት እንደሆነ በመናገር ነው፡፡
የዶክተሩ፣ የፈላስፋው፣ የፖይለቱ፣ የሳይንቲስቱ፣ የኢኮኖሚስቱ፣ የአስትሮኖሚስቱ፣ የሐኪሙ… ወዘተ ፈጣሪ መምህር ብቻ እንደሆነም ከመግለፅ ወደ ኋላ አላሉም፡፡
መምህሩ የእውቀት ፈንጣቂ ብርሃን መሆኑንም ከመግለፅ አልሸሸጉም፡፡ መምህር የትውልድ ትልቅ አሻራ በመሆኑ የስልጣኔ በር ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡ መምህር አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ለተማሪዎቹ የቀለም አባት መሆኑንም የተናገሩት በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተማሪዎቻቸው በሚያገኟቸው ቦታ ሁሉ የሚሰጧቸውን ክብር በመግለፅ ነው፡፡
በመሆኑም ነው “በመምህርነቴ የሚሰማኝ እርካታ ከፍተኛ ነው” ሲሉም የተደመጠው። ለመግቢያነት ይህንን ካልን ዘንዳ የመምህር ቆስቲ ምርጥ ተመክሯቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን መልካም ንባብ፡፡
መምህር ቆስቲ ስማ በቀድሞው መንግስታዊ አወቃቀር በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ በወላይታ አውራጃ በሶዶ ከተማ፥ በጊዮርጊስ ልዩ ሰፈር በ1944 ዓ.ም ተወልደው የ74 ዓመት እድሜ ይዘዋል፡፡
የልጅነት ህይወታቸው ሲዳሰስ በጊዮርጊስ ቄስ ትምህርት ቤት አባባሻ በሚባሉ ቄስ እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል፡፡
በ1951 ዓ.ም በሰባት ዓመታቸው በሊጋባ በየነ አባ ሰብሳብ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በአርባ ምንጭ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቀዋል፡፡
በ1964 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው በሰርተፊኬት የሚያበቃ ውጤት በማምጣት ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው ለአንድ ዓመት ሰልጥነው በመምህርነት ሙያ በሰርተፊኬት ተመርቀዋል፡፡
በወቅቱ ተመራቂዎች በቀጥታ ስለሚመደቡ እጣ ተጥሎ ወሎ ጠ/ግዛት፣ ዋድላ አውራጃ ደርሷቸው በፀሐይ መውጫ ት/ቤት ተመድበው ለአንድ ዓመት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
በ1967 ዓ.ም ወላይታ አውራጃ ተዘዋውረው በወላይታ ሀባ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድበው በመምህርነት ለሁለት ዓመት ሠርተዋል፡፡
በመቀጠልም በአውራጃው ሥር ወደሚገኘው አባላ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው በርዕሰ መምህርነት ለሁለት ዓመት ያህል አገልግለዋል፡፡
ከዚያም በ1971 ዓ.ም ወደ ወላይታ ሶዶ ሊጋባ በየነ አባሰብስብ 1ኛ ደረጃ /ወደ ተማሩበት/ ት/ቤት ተዛውረው የሳይንስ /የባዮሎጂ/ መምህር ሆነው እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ አስተምረዋል፡፡
ከዚያም በ1976 ዓ.ም ተወዳድረው የትምህርት እድል አግኝተው ኖሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ ገብተው ለሁለት ዓመታት ተከታትለው በትምህርት አስተዳደር በዲኘሎማ ተመርቀዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ዲላ የሙያ ትምህርት ቤት ተመድበው በሱፐርቫይዘርነት ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፡፡
ከዚያም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በ1980 ዓ.ም ወደ ሃዋሣ ታቦር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው በዋና ርዕሰ መምህርነት ተመድበው እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
በወቅቱ የታቦር ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ጥበት ስለነበረው የኮምቦኒ ትምህርት ቤትን ጠይቀው ከሰዓት በኋላ መምህራንን መድበው ተማሪዎቻቸውን ያስተምሩ ነበር፡፡
በመሆኑም በወቅቱ 106 መምህራንንና 6 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ያስተዳድሩና ይመሩ ነበር፡፡
በወቅቱ በሃላፊነት በሠሩባቸው ጊዜያት የመማሪያ ክፍሎች ጥበት በመኖሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር 1ዐ የመማሪያ ክፍሎችን አሠርተው ችግሩን ለማቃለል ችለዋል፡፡
የአጥሩን ዙሪያንም በብረትና በሽቦ አሳጥረው በግቢው ውስጥ የውሃ ጉድጓድና የቧንቧ ውሃ በማዘርጋት የግቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
ከዚህ ውጭም ተጨማሪ የማብራት ሃይል በማስጨመር የማታ ትምህርት ኘሮግራም በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
የቴሌቪዥን ትምህርትም በጥሩ ሁኔታ እንዲሰጥ ከማድረግ አኳያ ሚናቸው ከፍተኛ ነበር፡፡
በትምህርት ቤቱ ዕድር፣ የገንዘብ ቁጠባና ብድር በተጠናከረ መልኩ ተቋቁሞ አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
ከመምህራንና ከተማሪዎች ጋር በመተባበር በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ዙሪያ የተለያዩ የጥላ ዛፎችን አስተክለዋል፡፡
መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች የመማሪያ ክፍልንና መምህራንን በማዘጋጀት የተጠናከረ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
በ1984 ዓ.ም ላይ የመንግስት ለውጥን ተከትሎ በመጣው ሃላፊነት ቅድሚያ ለአካባቢው ልጆች ይሰጥ በሚለው መመሪያ መሠረት ዋና ስልጠናቸው ለሌላ ሰው ተሰጥቶ እሳቸው በምክትል ር/መምህርነትና በመምህርነት በት/ቤቱ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
ከዚያም በ2000 ዓ.ም ላይ ገበያ ዳር መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ዓመታት ያህል በርዕሰ መምህርነት ካገለገሉ በኋላ የጡረታ መብታቸውን አስከብረዋል፡፡
በገበያ ዳር ት/ቤት በርዕሰ መምህርነት በሠሩባቸው ጊዜያትም በርካታ ነገሮችን አሳክተዋል፡፡
ለአብነት ያህል የጀርመን ተራድኦ ድርጅትን በማስተባበር አንድ ትልቅ ቤተ መፃህፍትን ከነሙሉ መጽሐፍትና መቀመጫዎች ጋር አቋቁመዋል፡፡
የዩኒየን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ለትምህርት ቤቱ መምህራን ስልጠና እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም የደቡብ ኢትዮጰያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲኘሎማ ላላቸው ለትምህርት ቤቱ መምህራን ነፃ የትምህርት እድል እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ወላጅ አጥ ለሆኑ ተማሪዎች እየሩሳሌም የህፃናት መርጃ ድርጅት የዩኒፎርምና የደብተር እገዛ እንዲያደርግላቸው በመፃፃፍ እንዲታገዙ አድርገዋል፡፡
የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር ለመምህራን ሃገር አወቅ ኘሮግራም አዘጋጅተው ኮንሶ፣ ቤንሻንጉል…ወዘተ ጉዞ ተደርጐ ሁሉም መምህራኖች ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በሥራ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችም ነበሩ ይላሉ መምህር ቆስቲ ስማ፡፡
ለአብነት ያህል የተማሪዎች መብዛትና የክፍሎች እጥረት፣ የወላጅ አጥ ተማሪዎች ቁጥር መብዛት፣ በሙያው የሰለጠኑ መምህራን በበቂ ሁኔታ ያለመኖር፣ ትምህርት ቤቱን ለማሻሻል በቂ በጀት ያለመኖር፣ የትምህርት ሥራ የአእምሮ ሥራ ሲሆን የመምህራን ኑሮ አለመሻሻል /የደመወዝ ማነስ/ የመማሪያ መፅሐፍትና ቁሳቁስ ያለመሟላት ዋንኞቹ ችግሮች እንደነበሩ መምህሩ ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
መምህር ቆስቲ ስማ በ2004 ዓ.ም በሁለት የግል ት/ቤቶች በርዕሰ መምህርነትና በምክትል ርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡
ለአብነት ያህል በአቡነ ጎርጎሪዮስ ት/ቤት በርዕሰ መምህርነት በኮንትራት ተቀጥረው ለ3 ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡
በመቀጠልም ሌክሳይድ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነት ተቀጥረው ለሁለት ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡
በተጠቀሱት የግል ትምህርት ቤቶች ለ5 ዓመታት ያህል ከሠሩ በኋላ ሥራውን በመልቀቅ በእድሮች፣ በገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበር እንዲሁም በተለያዩ ሽምግልና ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
በሠሩባቸው ጊዜያት ጥሩ ተግባራትን በመፈፀማቸው እውቅናና የማበረታቻ ሽልማቶችን ማግኘታቸውን መምህር ቆስቲ ያብራራሉ፡፡
ለአብነት ያህል የታቦር መምህራንና ሠራተኞች የገንዘብና ቁጠባ ማህበር መሥራች ሆነው ግልፅና ታማኝነት ያለውን ሥራ በመሥራታቸው ማህበሩ ሠርተፊኬተና ሜዳሊያ ሸልሟቸዋል፡፡
ታቦርና ገበያ ዳር ት/ቤቶች በትምህርት ቤቱ ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የምስጋና ወረቀትና መጽሐፍት ተሸልመዋል፡፡
የትምህርት ሥራን እንዴት ያዩታል ተብለውም ተጠይቀው የሰጡን ምላሽ “የትምህርት ሥራ ውጤቱ ከብዙ ዓመታት በኋላ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ያስተማሯቸውና በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ መ/ቤቶች ለአብነት ያህል በሆስፒታሎች፣ በፍ/ቤቶች፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማትና በባለሙያነትና በሹመት ላይ የሚሠሩ ተማሪዎች መንገድ ላይ ሲያገኙኝ ‘መምህር አስተምረውኛል’ ሲሉኝ የሚሰማኝ እርካታ ከፍተኛ ነው፡፡
ለዚህም ይመስላል “እኔ መሠረቱን በመጣሌ የሀገሪቱ ብቁ ዜጋ በመሆናቸው እጅግ በጣም ያስደስተኛል” በማለት የተናገሩት፡፡
“ርዕሰ መምህር በመሆንም በርካታ ወላጆች እና ተማሪዎች ሰላምታ ሲያቀርቡልኝ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል” በማለትም ደስታቸውን ሲገልፁ የዚህ ሁሉ ውጤት መሠረቱ የትምህርት ሥራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ቀጣዩ ትውልድም የሀገር ተረካቢ በመሆኑ መምህራንና ሠራተኞች ችግሩንም ደስታውንም ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር በመሳተፍ፣ ፍቅርን በመስጠት እና ሰላምን በማስፈን ጥሩ ሥራ እንዲሠሩ ይመኛሉ፡፡
አስፈላጊ ቦታ ላይ እሳቸውን እገዛ ለሚሹ ትምህርት ቤቶችም ሆነ ድርጅቶች በነፃ ሊያገለግሉ ፈቃደኛ መሆናቸውን በደሰታ ያበስራሉ፡፡
የሥራ ሰዓት አክባሪነት፣ ከሠራተኞቻቸው ጋር በፍቅርና በመቻቻል ማሳለፍ፣ ሰው አክባሪነት፣ ሐቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ሚዛናዊነት፣ እውነተኛነት ልዩ ባህሪያቸው እንደሆነ ከመግለፅ አልሸሸጉም፡፡
የሥራ ሰዓት አክባሪነትን የገለፁት ማርፈድና ከሥራ መቅረት ችግር ካላጋጠማቸው በፍፁም ያልለመዱት ድርጊት መሆኑን በመግለፅ ነው፡፡ ጠዋት ተኩል ሰዓት አስቀድመው በሥራ ቦታቸው ይገኛሉ፡፡
ከሰዓት የሥራ ሰዓት ተጠናቅቆ ከተኩል ሰዓት በላይ ዘግይተው ነው ወደ ቤታቸው የሚሄዱት፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ሥራን ያስቀድማሉ፡፡ ሁሌ ትጉህና ውጤታማም ናቸው፡፡
መምህራንና፣ ሠራተኞችንና ተማሪዎችን አባታዊ መርህ ተከትለው ነው የሚመሩት፡፡ ሰውን ማበላለጥና ማሳነስ የማይወዱ ሁሉንም በእኩል አይን የማያዩ ከአድሎአዊነት የነፁ ሐላፊ ናቸው፡፡
ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በ1981 ዓ.ም ሲሆን የ1 ወንድ እና የ2 ሴት በድምር የ3 ልጆች አባት ናቸው፡፡
አንዲት ሴት ልጃቸው ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ በዓይን ህክምና ተመርቃ በሀዋሣ ውስጥ ብርሃን የዓይን ህክምና ማእከል ተቀጥራ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ወንድ ልጃቸው ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ታናሹዋ ሴት ልጃቸው ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነች፡፡
ይህ የመምህሩ ምርጥ ተሞክሮ አስተማሪ በመሆኑ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምኩኝ ዝግጅቴን በዚሁ ቋጨሁ፡፡ ሰላም፡፡
More Stories
“አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው” – ወጣት ታምራት አማረ
ትንሽ ዕድሜ፤ ትልቅ ዓላማ
አትሌቲክሱ ምን ነካው?