የብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቻለሁ – አቶ አብደላ ላራጎ

የብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቻለሁ – አቶ አብደላ ላራጎ

በጋዜጣው ሪፖርተር

“በሰላም አውለህ በሰላም አሳድረኝ” ይላል ያገሬ ሰው ቀኑን ለአምላኩ አደራ ሲሰጥ፡፡ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን በሰላም ውሎ ማደር ትልቅ ነገር በመሆኑ የዘወትር ተግባሩን ለመፈፀም ማልዶ ተነስቶ፥ ከብቶቹን ለማገድ በተሰማራበት አጋጣሚ ያልታሰበ አደጋ ደረሰበት።

ዛሬ ስኬት ላይ ቆሞ ታሪኩን ሲያጋራን ያለፈበት መንገድ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በደረሰበት አደጋ ህይወቱን እስከ ማጣት ደርሶ ነበር። ሥራ ለማግኘትም ብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቷል። የውሃ አጣጪን ለማግኘት ባደረገው ሙከራም ልቡ ተሰብሮ ነበር፡፡

የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ልቡን የሚያቆስሉ በርካታ ፈተናዎች ሊያጋጥመው ይችላል፤ በተለይም አካል ጉዳተኞች ላይ ችግሩ ይበልጥ ይበረታል፡፡

የዛሬው ችያለሁ አምድ ባለታሪካችን አቶ አብደላ ላራጎ ይባላል፡፡ በ1988 ዓ.ም በማረቆ ወረዳ ሺሪንቶ በምትባል ገጠራማ ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በማረቆ ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት የሰው ሀብት ባለሙያ ሆኖ ለ6 ዓመታት አገልግሏል፡፡ አሁንም እያገለገለ ይገኛል።

አካል ጉዳት እንዴት እንደገጠመው ሲያነሳ፡-
“የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ከብቶችን ለማገድ ወደ ሜዳ ስሄድ አጎቴ እንጨት እየቆረጠ ነበር፡፡ የራሳችንን እና የአጎቴን ከብቶች ነበር የማግደው፡፡ ‘ይህቺን እንጨት እስክቆርጥ ጠብቀኝ እሸኝሀለሁ’ አለኝ፡፡ የእኛ ከብቶቹ ሰው የረገጠውን ሳር አይበሉም፤ ቀድሜ ልሂድ አልኩት፡፡ አጎቴ ግን ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ልጅ ስለነበርኩ ብዙ መከራከር አልፈለኩም፡፡ እሺ ብዬ ጠበኩት” ሲል ነበር በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የገለጸልን፡፡

አጎቱ የሚቆርጠው እንጨት ለመውደቅ ልክ ጫፍ ሲደርስ፣ ከወዲያ ማዶ ደግሞ የአጎቱ በሬ አዲስ የተተከለ የሰው ባህር ዛፍ ማሳ ላይ ሲገባ አጎቱ ተመለከተ፡፡ ቶሎ እንዲያስወጣ ሲያጣድፈው ወደ በሬው ሮጠ፡፡ ይሁን እንጂ የእንጨቱ ቅርንጫፍ ወድቆበት ቀኝ እግሩ ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡

በሰዓቱ ቤተሰቦቹ ከማልቀስ ባለፈ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም፡፡ ወደ ህክምና ቦታ እንኳን ለማድረስ አልተረጋጉም ነበር፡፡ ከቀናት በኃላ ለማጅ ወጌሻ አመጡ፡፡ ያልተሰበረ ቦታ እያሰረ ጭራሽ እግሩን ከጥቅም ውጪ አደረገው፡፡ አብደላም ራሱን እስከ መሳት ደረሰ፡፡

ዘመድ አዝማድ ሞቷል ብሎ ተስፋ ቆረጠ፡፡ እናትና አባቱ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ህክምና መሄድ ፈለጉ፡፡ አጎቶቹ (የአባቱ ወንድሞች) ደግሞ “በቃ ሞቷል ሬሳ እንዴት እንወስዳለን፡፡ ነፍሱ ስትወጣ ጠብቀን ብንቀብረው ይሻላል፡፡” የሚል ሃሳብ ሰጡ፡፡

በሌላ በኩል ሌሎቹ አጎቶቹ (የእናቱ ወንድሞች) እዛ ወስዳችሁ ገደላችሁት ብለው ከቀዬአችን ያፈናቅሉናል በሚል በሁለት ጎራ ተከፈሉ፡- እርስ በእርስ መጣላትም ጀመሩ፡፡ ይባስ ብለው ወላጆቹ ወደ ህክምና እንዳይወስዱት መጠበቅ ጀመሩ፡፡

“ታዲያ አንድ ቀን ማምሻ ወደ የቤታቸው ሲሄዱ የታላቅ ወንድሜ አማቾች በምሽት ይዘውኝ ጠፉ፡፡ ቆሼ የምትባል ከተማ አሳድረውኝ በለሊት ሻሸመኔ ኩየራ ሆስፒታል ወሰዱኝ፡፡ ሀኪሞቹ እንደ ነገሯቸው ትንሽ ብዘገይ ኖሮ ህይወቴ ያልፍ ነበር። እግሬ ከመበስበሱና ከመትላቱ የተነሳ ትሉ ወደ ሽንት ቧንቧ እየተሰራጨ ነበር፡፡ ስለዚህ መቆረጥ አለበት ብለው እግሬ ተቆረጠ፡፡” ሲል ወላጆቹ የነገሩትን በማስታወስ ነበር ያወጋን፡፡

ህክምና አግኝቶ መከታተል ከጀመረ ልክ አራተኛ ወር ላይ ነበር ራሱን ያወቀው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሆነውን ሁሉ አያውቅም ነበር፡፡

“ልክ ስነቃ የማላውቀው ቦታ ራሴን አገኘሁት። አባቴን የት ነው የመጣነው? ወደ ሰፈር እንሂድ? ብዬ አለቀስኩኝ፡፡ አባቴም አብሮኝ ያለቅስ ነበር። በሶስተኛው ቀን አካባቢ በጣም እያለቀስኩ ሳስቸግረው፥ ‘በምን እግርህ ነው የምትሄደው’ እያለ እንደ ህፃን ልጅ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ከተረጋጋ በኋላ ለምንድ ነው የምታለቅሰው ብዬ በተደጋጋሚ ጠየኩት፡፡

“የተከሰተውን ነገር ሁሉ በዝርዝር አስረዳኝ። በመጨረሻ ግን ‘እግርህ ተቆርጧል’ ሲለኝ በጣም አለቀስኩኝ” ሲል ፍፁም በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ገለጸልን፡፡

ከስድስት ወር በኋላ ህክምናውን ጨረሰ፡፡ በክራንች መራመድም ጀመረ፡፡ ከዚያም ለሁለት ዓመታት ያህል ቤት ከቆየ በኋላ፥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ይህ ጊዜ በጣም ፈታኝ ነበር ይላል አብደላ፡፡ ከሻሸመኔ ያመጣው ክራንች ተሰበረ፡፡ ወደ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት በዱላ እየተንጠለጠለ እየሄደ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ሺሪንቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ አጠናቀቀ፡፡

“9ኛ ክፍልን ቆሼ መጥቼ ስመዘገብ፥ የታሪክ መምህሬ ከተመዘገብኩበት ቀን ጀምሮ በዱላ መንጠልጠሌን አይቶ ልቡ ያዝን ነበር፡፡ አዝኖ ከንፈር መጦ ዝም አላለም። አርቴፊሻል እግር እንዲሰራልኝ እየተደዋወለ ብዙ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ከዚያ ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ተሳካልኝ። አርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ሄጄ የእግር ድጋፍ ተሰራልኝ፡፡

በመምህሩ ጥረት እንደማንኛውም ተማሪ በሁለት እግሩ እየተራመደ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ቆሼ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዚህም መምህሩንም ሳያመሰግን አላለፈም፡፡
ከዚያም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አምጥቶ “ጎንደር ዩኒቨርስቲ” በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ለመማር በቃ።

ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ አየሩ ስላልተስማማው ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተዘዋወረ፡፡ ከዚያም ለ2 ዓመታት ተከታትሎ በ2011 ዓ.ም መመረቅ ችሏል፡፡

ወደሥራ ዓለም የገባበትን አጋጣሚ ሲያጫውተን፡-
“ሥራ ለማግኘት ያስተናገድኳቸው ፈተኛዎች ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ። ወረዳው እየደገፈኝ አስተምሮኝ ሲያበቃ፤ ዩኒቨርስቲውም እየደገፈኝ ተምሬ ብመረቅም፤ ቅጥር ላይ ግን ትልቅ ፈተና ገጠመኝ፡፡ ወቅቱ ቅጥር የታገደበት ጊዜ ነበረ። ባለፍኩባቸው መንገዶች አካል ጉዳተኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር፡፡ አትቀጠርም ስባል ግን በጣም ተማረርኩኝ፤ መፈጠሬንም ጠላሁት” ሲልም ነበር ስሜቱን የገለፀልን፡፡

“በየመስሪያ ቤቱና በየአካባቢው ስራ ሳፈላልግ ቅጥር ታግዷል ያለኝ መስሪያ ቤት በሙሉ ጉዳት አልባ ሰዎች መቀጠራቸውን ሰማሁ፡፡ በጣም እልህ ውስጥ ገባሁ፤ በዛ ጊዜ ደግሞ ሌላ ፈተና የሆነብኝ የተሰራው አርቴፊሻል እግሬ ተሰብሮብኝ ስለነበር እንደልብ ለመንቀሳቀስ አልችልም ነበር።

“ለሚመለከተው አካል የተሰበረውንና ሰው ሰራሽ እግሬን እያሳየሁ መኳተኔን ቀጠልኩ። አልቅሼም ለመንኳቸው፤ ሊረዱኝ ግን አልፈለጉም። በመጨረሻ ምርር ብሎኝ የወረዳውን አስተዳደሪ ‘ለእኔ የመንግስት ሥራ የማይፈቀድልኝ ከሆነ የግቢህ ሠራተኛ አድርገህ ቅጠረኝ’ አልኩት። እስከ ክልል ድረስ ጠየኩ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ተሳካ፡፡ በ2011 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ በሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ቅጥር ተፈፀመልኝ” ሲልም አብደላ ሁኔታውን አጫውቶናል፡፡

“በመስሪያ ቤቱ ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ ሥራዬን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ የተቋሙ የሰው ሀብት ሠራተኛ ነኝ፡፡ ሠራተኞች በአግባቡ በሰዓታቸው እንዲገቡ ሰዓት የማስከበር እና ሠራተኞች ተቋሙ ላይ እንዲቆዩ የማድረግ ሥራ ላይ ውጤታማ ነኝ፡፡ እና ደስ የሚል ህይወት እየኖርኩኝ ነው፡፡

“ሆኖም ግን ፍፁም ነው ማለት አይቻልም። አጠቃላይ ነገሮችን ስታዘብ፥ አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ጭምር ስለአካል ጉዳት የግንዘቤ ችግር አለባቸው፡፡ ቢሮ አካባቢ ግልፅ ሆኖ ባይወጣም አሉታዊ የአመለካከት እሳቤዎች ይንፀባረቃሉ። አካል ጉዳተኞችን ከሰው በታች አድርገው የሚያዩበት እይታ አለ” ሲልትዝብቱን አካፍሎናል።

እነዚህን አመለካከቶች ያስተናገደበትን መንገድ ሲያስረዳም፡-
“እኔ ግን ምንም አይመስለኝም፡፡ ከማንም በላይ መስራት እና ማንም የደረሰበትን ቦታ እደርሳለሁ የሚል ህልም አለኝ፡፡ አልሀምዱሊላ አላህ ያሳካልኝ፡፡” ሲል ተስፋ በሰነቀ ስሜት ይናገራል፡፡

ወደ ትዳር ህይወት እንዴት እንደገባ ላነሳንለት ጥያቄ፡-
“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ትንሽ ያሳስበኝ የነበረው እንዴት ትዳር እመሰርታለሁ በሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ አንዳንዴ ጓደኞቼ ሲያገቡ እኔ ብቻ ሳላገባ ልኖር ነው ብዬ እሰጋ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ነበር፥ ከቤተሰብ ይመስለኛል ስልኬን ያገኘች አንዲት ሴት ደውላ እወድሀለሁ አለችኝ፡፡

“ያችን ቀን እንደ ታሪክ ነው የምቆጥራት፡፡ እና ልጅቷ እወድሀለሁ ስትለኝ መጀመሪያ ጀርባዬን አጥኚ፡፡ አካል ጉዳተኛ ነኝ ግን በጉዳቴ ምክንያት ተሸማቅቄ አላውቅም፡፡ ባንቺ ምክንያት መጎዳት አልፈልግም አልኳት፡፡

“ሞቼ እገኛለሁ ብላ አሻፈረኝ አለች፡፡ እኔም ብዙ ችግር ሊደርስብሽ ይችላል፤ ቤተሰቦችሽም ፈቃደኛ ላይሆኑ ስለሚችሉ በደንብ አስቢበት አልኳት፡፡ እንደፈራሁትም ቤተሰቦቿ ‘እንዴት እንደዚህ ትላለህ? ምን አይነት ድፍረት ቢኖር ነው’ ብለው ቅስሜን ሰበሩት፡፡ ልጅቷንም ለሌላሰው ዳሯት” በማለት ማህበረሰቡ ላይ ያለውን አመለካከት ያወግዛል፡፡

“ከዚያ ጊዜ በኋላ ስለ ትዳር አስቤ ኣላውቅም ነበር፡፡ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተዘዋውሬ ከመጣሁ በኋላ ግን የተለየ ስሜት ይሰማኝ ጀመር፡፡ አደጋ ላይ መውደቄ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ቶሎ ማግባት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

“ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር አንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው እነሱ ቤት ነበር፡፡ እሱን አማከርኩት፡፡ ‘የተቀደሰ ሀሳብ ነው አግባ አለኝ’ አጋጣሚ ሆኖ የእሱን እህት ነበር ማግባት የፈለኩት፡፡ ግን በምን አግባብ ማናገር እንዳለብኝ ግራ ገባኝ፤ በጣም ፈራሁ። ለጓደኛዬ እህቱን እንደምፈልግ አልነገርኩትም ነበር፡፡

“አንድ ቀን ግን በድፍረት ማናገር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ለእረፍት መጥቼ በፍላሽ ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን አስጭኜ እንድታዳምጥ ሰጠኋት። እረፍት አለቀና ተመለስኩኝ፡፡ እዛ ሆኜ ስልክ ቁጥሯን ከሰው አፈላልጌ ደወልኩላት፡፡ ‘ፍላሽ ጥያለሁ እንዴ?’ አልኳት፡፡ ‘አይ ሰጥተኸኝ እኮ ነው የሄድከው’ አለችኝ፡፡

“ከዛ በፊት ቤታቸው እየበላሁ፣ እየጠጣሁ ከመተያየት ውጪ ተነጋግረን አናውቅም ነበር። ስታናግረኝም መድፈር አልቻልኩም፡፡ ከዚያም በአካል ከመጠየቅ፥ በስልክ ይሻላል ብዬ፤ በስልክ መልዕክት ፃፍኩላት፡፡ እሷም ታስብ ስለነበር እሺ ብላ ምላሽ ሰጠችኝ፡፡

“ወንድሟም በበኩሉ የዛች ልጅ ቤተሰብ ከከለከሉኝ በኋላ ተናድዶ በውስጡ ‘ለምን እህቴን አያገባም ብዬ አስብ ነበር፡፡ ግን እህቴን አግባ ማለቱ ማስገደድ ይሆናል ብዬ ፈራሁ’ ብሎ ነገረኝ፡፡ ከዚያም ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ሽማግሌ ልኬ ኒካ(ቀለበት) አሰርኩኝ” በማለት ሁኔታውን አጫውቶናል፡፡ አሁን ላይ የ3 ልጆች አባትም ሆኗል፡፡

“አካል ጉዳተኞች ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ከተማም ሆነ ገጠር አካባቢ የሚሸማቀቁበት ሁኔታ አለ፡፡ ሰው የሚያደርገውን ነገር ማድረግ አልችልም ብለው ራሳቸውን የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋሉ፡፡ አካል ጉዳተኞች ከማንም የሚያንስ ስብዕናም ሆነ ችሎታ የላቸውም፡፡

“የበታችነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም፡፡ መበርታት አለባቸው፡፡ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም፡፡ እንደ ሀገራችን ብሎም እንደ ዓለማችን ትላልቅ ቦታ የደረሱ ታዋቂ አካል ጉዳተኞች አሉ። ከማንኛውም ሰው የበለጠ መሥራት እንችላላን፡፡ አካል ጉዳተኞች ተስፋ ቆርጠው አንችልም ብለው ቤት መቀመጥን አስወግደው፤ እችላለሁ የሚለውን ተስፋ አንግበው መንቀሳቀስ አለባቸው” ሲልም መልክቱን አስተላልፏል፡፡