የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚረዱ ዘመናዊ ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
በተያዘው የምርት ዘመን ከ160 ሄክታር በላይ መሬት የቡና ጉንደላ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በወረዳው ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ቡና ለአገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ በመሆኑ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት ረገድ ትልቁን ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተመላክቷል።
አቶ ክፍሌ ደምሴ እና አቶ ደምሴ ደስታ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በአቹራ ማዘጋጃ የመብራት ኃይል መንደር ነዋሪዎች ሲሆኑ፥ ለበርካታ ዓመታት የተሻለ ምርት ይሰጥ የነበረ ቡና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርት እየቀነሰ በመምጣቱ የቡና ጉንደላ እንዲከናወን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና እገዛ እንዳልተለያቸው የገለጹት አርሶ አደሮቹ፥ የተጎነደሉ ቡናዎች አቆጥቁጠው ፍሬ እስከሚሰጡ ድረስ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ እንደሚያደርጉና ከዚህም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል።
ምርት የማይሰጡ እና ረዥም ዓመት ያስቆጠሩ የቡና ተክሎችን በመለየትና ለምርታማነቱ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን በአቹራ ማዘጋጃ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወጋየሁ አስረድተዋል።
አርሶ አደሩ ያለውን አነስተኛ መሬት በአግባቡ በመጠቀም የወቅቱን የኑሮ ጫናን ለመቋቋም እንዲችል የማስተባበርና የማስተማር ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን የአቹራ ማዘጋጃ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ገልፃዋል።
በተያዘው የምርት ዘመን ከ160 ሄክታር በላይ መሬት የቡና ጉንደላ ሥራ ለማከናወን ከታቀደው እስካሁን 95 በመቶ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን በወረዳው ቡና እና ቅመማቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አግዴ አሽኮ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ፍቃዱ ማቴዎስ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የሰንበት ገበያ ማዕከል ሸማቹና አምራቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና እንዳለው ተገለጸ
በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ከ36 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተሰራው የኡማ ባኬ መንገድ ተጠናቆ ተመረቀ
የ2017 የክረምት ወራት የገቢ አሰባሰብና የ2018 ዓ.ም የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ስራ በአግባቡ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በጋሞ ዞን ባለድርሻ አካላት ገለጹ