‎በደቡብ ኦሞ ዞን በሣላማጎ ወረዳ በሌማት ትሩፋት በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ድጋፍ በዶሮ እርባታ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

‎በደቡብ ኦሞ ዞን በሣላማጎ ወረዳ በሌማት ትሩፋት በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ድጋፍ በዶሮ እርባታ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ
‎
‎በሣላማጎ ወረዳ በጽጽማ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከሌማት ትርፋት ተግባር አንዱ በሆነው በዶሮ እርባታና እንቁላል ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
‎
‎በወረዳው በጽጽማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አሸቴ ኩስዬ በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ድጋፍ 24 ዶሮዎችን በማርባት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
‎
‎ወ/ሮ አሸቴ ጨምረው እንደገለፁት፤ ባገኙት ድጋፍ ሰርተው በ6 ወር ውስጥ በእንቁላል ሽያጭ ብቻ 23,800 ብር መቆጠብ መቻላቸውን ገልፀው በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል።
‎
‎የቀበሌው ስራ አስኪያጅ አቶ ካሣዬ ገንድሻ፤ የወረዳው መንግስትና የቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ብሎም ግብርና ጽህፈት ቤት ላደረጉት ድጋፍና ክትትል አመስግነዋል።
‎
‎በቀጣይም ሥራውን በቀበሌው በማስፋት እንደሚሰሩ ገልፀው፥ ምርቱን በፈለግነው ልክ እንዳናሳድግ በሽታ መከላከሉ ላይ በቅንጅት እንዲሰራ ሥራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።
‎
‎የሣላማጎ ወረዳ ግርብርና ጽህፈት ቤት እንስሳትና አሳ ሀብት ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ከተማ ካሳሁን እንደገለጹት፤ በወረዳው የተለያዩ የሌማት ትሩፋት መንደሮችን በማደራጀት እየተሰራ ሲሆን በዶሮ መንደር 3 ታቅዶ 11፣ በማር መንደር 5 ታቅዶ 6፣ በሥጋ መንደር 4 ታቅዶ 5 ማከናወን ተችሏል።
‎
‎በተመሳሳይ መንግስት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው የቤተሰብ ብልፅግና ሲረጋገጥ እንደሆነ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባሩን በተለየ ሁኔታ በመደገፍ በሌሎችም ዘርፎች ድጋፍና ክትትሉን በቀጣይነት በማጠናከር እየተሰራ እንዳለ ቡድን መሪው ገልፀዋል።
‎
‎የሣላማጎ ወረዳ ግርብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቶማስ አስካም በበኩላቸው፤ በወረዳው በሁሉም ቀበሌ በሌማት ትሩፋት አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
‎
‎በዚህም የቁጠባ ባህልን እንዲያሳድጉ በማስገንዘብ እና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት እየተሰራ ሲሆን ሁሉም የቀበሌው ነዋሪ ተግባሩን በማጠናከር የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
‎
‎
‎ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን
‎