በሆሣዕና ከተማ የሚገነቡ ሆቴሎች የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ከተማው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ገለፁ
በሆሳዕና ከተማ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በወጣት ባለሀብት ኤርክቦ ባቾሬ የተገነባው ሆቴል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።
በሆቴሉ የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የተገነባው ሆቴል የአንድ ባለሀብት ብቻ ሳይሆን የህዝቡ መሆኑን በመጥቀስ በከተማው እየተገነቡ ያሉ ሆቴሎችም የከተማውን ገጽታ የሚቀይሩ ብቻ ሳይሆኑ ከተማው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለማንኛውም ልማት ሰላም ወሳኝ ነዉ ያሉት ዶ/ር ዲላሞ፤ የሆሣዕና ከተማም የሰላም አምባሳደርነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የሆሳዕና ከተማ ከፍተኛ የገንዘብ ዝዉዉር ያለው እንደመሆኑ የገንዘብ ዝውውር ስርዓቱን በጥበብ እና በብቃት መምራትና በኢንቨስትመንት ላይ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ በበኩላቸው፤ የሆቴሉ መገንባት ከተሞችን ለዜጎች ኑሮ ምቹና ማራኪ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ የተቋማት ግንባታ እንዲጠናቀቅ የዞኑ አስተዳደር ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ የፋይናንስ ተቋማትም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በወጣቱ ባለሀብት የተገነባዉ ሆቴል ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጠር መሆኑን የተናገሩት አቶ ማቲዎስ፤ በእለቱ ከተመረቀው ሆቴል በተጨማሪ ለወጣቱ ባላሀብት በሆመቾ ከተማ አስተዳደርና በሆሳዕና ከተማ ተጨማሪ በሆቴል እና በማምረቻው ዘርፍ እንዲሰማራ ቦታ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እንደገለጹት፤ የተመረቀው ሆቴል ለከተማው ኢኮኖሚ፣ ውበትና ባህላዊ ጉዞ ተጨማሪ መሆኑን በመጥቀስ በከተማው ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ የሚያስቀምጡ ወጣቶች በብዛት እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማውን የኮንፍራንስ ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ክልላዊና ሀገራዊ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ አቅም የሚፈጠር መሆኑንም አክለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አሁንም ከተማውን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፤ በእለቱ የተመረቀው ሆቴልም የሀዲያን ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን ጨምሮ ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል።
የሆቴሉ ባለቤት የሆነው ወጣት ኤርክቦ ባቾሬ በበኩሉ፤ ከወላጆቹ የወረሰውን ጠንክሮ የመስራት ባህልን በመጠቀም ከልጅነቱ ጀምሮ ባፈራው ጥሪት በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር የሚሆን ቅርስ መስራቱን ተናግሯል።
ሆቴሉም ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ለግንባታውም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ወጣት ኤርክቦ ገልጿል።
ሆቴሉ ለምርቃት እንዲበቃ በሀሳብ እና ሙያዊ ድጋፍ ያደረጉ ቤተሰቦቹን፣ ጓደኞቹንና የመንግስት አካላትን አመስግኗል።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የጂንካ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የተጠርጣሪ ማቆያና የቢሮ ህንጻ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በተገኙበት በደማቅ ሥነ ስርዓት በይፋ ተመረቀ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ቢሊዮን 4 መቶ 21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ
በትራንስፕርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ባለው ከታሪፍ በላይ ጭማሪ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች እየተጋለጥን ነው ሲሉ በወልቂጤ ከተማ መናኽሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች ተናገሩ