የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸዉ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የኣሪ ዞን አስተዳደር ገለፀ፡፡
“ትምህርት ለትዉልድ” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ትምህርት መምርያ የ2018 ዓ/ም ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና በኣራፍ ቋንቋ የትምህርት አሰጣጥ ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሳይንስ፣ የመረጃና የቴክኖሎጂ አብዮት ባለበት በዚህ ዘመን ያለትምህርት እውቀትን ማሰብ እንደማይቻል አመላክተው፥ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ስብራቶችን በመቅረፍ ጊዜው የሚፈልገውን ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ዜጋ በማፍራትና በትምህርት ጥራት ላይ በተሰሩ ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ቋንቋ በአከባቢ ያሉ ነገሮችን በቀላሉ ለማወቅና ለመረዳት ስለሚያግዙ በዞኑ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲማሩ በአከባቢያቸዉ ያሉ እውቀቶችንና ባህሎች በቀላሉ እንዲያውቁትና እንዲረዱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የተጀመረውን የኣራፍ ቋንቋ የትምህርት አሰጣጥ ማልማትና ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የኣሪ ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ አቶ እልፊዮስ ባድመ በበኩላቸው፥ የትምህርት ስብራትን በመጠገን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን አቅም ማጎልበት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የተማሪዎችን መጠነ መቅረትና ማቋረጥ ማስቀረት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የምገባ ፕሮግራም የማስጀመር ስራዎ እየተሰሩ ቢሆንም፥ አሁንም ያሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በቀሪ የስራ ጊዜያት ውጤታማ ተግባራትን ለመከወን የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮ የኦን ላይን ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ቲቶርያል ሆነ ተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን ማብቃት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የባካ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ጋንማይ፥ የሰሜን ኣሪ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብራጊ ታደለና የደቡብ ኣሪ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም አይከስ በጋራ በሰጡት አስተያየት፥ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ በቀሪ ወራቶች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣብያችን

More Stories
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ በጋራ በመሆን ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረጉ
ዞኑ በግማሽ ዓመቱ 1 ሺህ 3 መቶ 25 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቀረበ
የማህበረሰቡን የፍትህ ጥማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ