በጎፋ ዞን ከ950 ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ከ950 ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩን የጎፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የዞኑ ማዕድን ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምና የቀሪ ወራት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።
የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሚያስችሉ ዘርፎች አንዱ ማዕድን መሆኑን ጠቁመው፥ እስከአሁን በሚፈለገው ልክ ያልተጠቀምንበት ዘርፍ በመሆኑ ያስቆጫል ብለዋል።
በቀጣይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፉን ማልማት፣ መደገፍና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ዞኑ ከ50 ሄክታር በላይ በብረት ማዕድን የበለጸገ ሲሆን ከ950 ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ በጥናት መረጋገጡን አንስተዋል።
በዞኑ የከሰል ድንጋይ፣ የብረት፣ የግንባታና ሌሎች ማዕድናት በአብዛኛው አካባቢ ስለሚገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በጥናት የተደገፈ ልማት ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።
የጎፋ ዞን ማዕድን ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዝታ አብርሃም የማዕድን ዘርፍ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን አመላክተው፥ ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ዕድገት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በዞኑ ሰባት ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የማዕድን ልየታ መደረጉን ጠቁመው፥ ዘርፉ በሀገራችን የኢኮኖሚ ምሰሶ በመሆኑ ራሱን ችሎ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በጽ/ቤት እንዲደራጅ ተደርጓል ብለዋል።
አክለውም የዞን ማዕድን ጽ/ቤት በየወረዳና በከተማ አስተዳደር ያሉ ሀብቶችን በመለየት ጥናቶች እያደረገ ሲሆን በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ስለመገኘታቸው አብራርተዋል።
የጽ/ቤት የስድስት ወራት አፈጻጸምና የማዕድን ህጎች ላይ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በክረምቱ ወቅት የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ዝግጅት ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ ትምህርት እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ገለፁ
የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ እና የግብርና ቴክኖሎጂን በተገቢ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን በከምባታ ዞን የዶዮገና ወረዳ አንዳንድ አርሶ አደሮች ተናገሩ
የኦዲት አገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራት በማሣደግ የተገልጋይና የባለድርሻ አካላት ርካታን ለማሣደግ እየተከናወነ በሚገኘው ተግባር ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የክልሉ ዋና ኦዲተር አስታወቀ