የኢትዮጵያ ሚና በአፍሪካ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ልዩ እና ጉልህ ስፍራ አላት። ብዙዎችን የዓለም ሀገራት ባስደመመ ሁኔታ በቅኝ አለመገዛቷ ለአፍሪካውያን የነፃነት እንቅስቃሴ ትልቅ ተነሣሽነት በመፍጠር ረገድ አስተዋፅኦ ነበረው።
ይህ ጠንካራ የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎትን የመቃወም ታሪክ በሀገራችን ማንነት ላይ ጠለቅ ያለ፣ የራሱን ብሔራዊ እና አዎንታዊ ትርክት ከመፍጠሩም ባሻገር፤ የአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ ትግል ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩን የታሪክ ጸሐፊዎች ሰንደውታል፡፡
የኢትዮጵያ ትግል በቴክኖሎጂ የላቀውን የአውሮፓ ኃይሎች ዓድዋ ላይ ድል መንሳቷ፤ የአፍሪካ ኃይሎች በሚገባ በመደራጀት እና በወኔ ከታገሉ አውሮፓውያንን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየ ነው።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ያስጠበቀች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ለሌሎች በቅኝ ግዛት ስር ላሉ ሀገራት የተስፋ ብርሃን እንድትሆን አድርጓታል። በቅኝ ያልተገዛው ታሪኳ ለሰፊው አፍሪካዊ የነፃነት ትግል ኩራት እና መነሣሣትን የፈጠረ ነበር።
ድሉ በፓን አፍሪካኒዝም ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና እንዲጎላ፣ በአፍሪካ መንግሥታት መካከል አንድነትን የሚያበረታታ የፖለቲካ እና የባህል ንቅናቄ ለመፍጠት ባለፈ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው።
በዚህም ድሉ ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) እና የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሰረት በማድረግ የአህጉሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። እንዲሁም ከቅኝ አገዛዝ ጋር ለሚዋጉ ሀገራት የሞራል እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ለአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴዎች መድረክ ሆኖ አገልግሏል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ መውጣት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ ፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ረገድ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች። ለብዙ የአፍሪካ ሃገራት የነፃነት ንቅናቄዎች፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች። የኢትዮጵያ ጥረት የበርካታ አፍሪካ ሀገራትን ነፃነት እንዲጎናፀፉ አግዟል።
ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ላይ የነበራት ተቃውሞ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ረገድ የተጫወተችው ሚና ለዘመናዊው አፍሪካዊ ማንነት መሠረት ሆኗል። የፓን አፍሪካኒዝም መፍለቂያ እንደመሆኗ፣ ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ያደረገችው አስተዋፅኦ በአህጉሪቱ ላይ የማይጠፋ አሻራ አሳርፏል።
ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦርነት ታሪካዊ ድል ድረስ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢ ኃይሎች ላይ ያደረገችው ተቃውሞ እና ትግል፣ ትሩፋቱ ለአፍሪካ ሀገሮች የተስፋ ብርሃን እንደሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፉ የተለያዩ ጸሀፍት አመላክተዋል፡፡
እንደሚታወቀው በየጊዜው የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት ለአፍሪካ ህዝቦች ነጻነት ጽኑ አቋም ነበራቸው፡፡- አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነጻ እንዲወጡ ኢትዮጵያ የበኩሏን ስትወጣ ቆይታለች፡፡ በዚህም ሌሎች የአፍሪካ የነፃነት አርበኞችን በማስተባበር ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተምሳሌት መሆኗን በተግባር ጭምር ያስመሰከረች ሀገር መሆኗን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያመላክታሉ።
ከሰሞኑ ታዲያ 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ መቀመጫና በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶቿን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ ይገኝበታል።
በዚህም ኢትዮጵያ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ድምጽ መመረጧን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በየጊዜው በተለይም በቀጣናው የራሷን ሰላም አስከባሪ በተለያዩ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በመላክ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው፤ አባል ሆና መመረጧ የነዚህ ድምር ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል። በቆይታዋም ይህንኑ አጀንዳ ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ጋር በመሆን የበለጠ የምታስፈጽም እና አተኩራ የምትሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የሚመክርባቸው አጀንዳዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ዘላቂ ሰላም እና መፍትሄ በሚያገኙበት ጉዳይ ላይ መምከር እና የመፍትሄ አቅጣጫ መስጠት መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአህጉሪቷ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ እነኝህን ግጭቶች ከአባል ሀገራት ጋር በጋራ በመሆን ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻልበት መንገድ በቀጣይ የሚሰራበት አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
More Stories
አንድ ነገር ቢጎድልህም ሌላ ነገር ተሰጥቶሀል – ወጣት ቢኒያም በሪሶ
ችግር ፈቺ የሆኑ አለም አቀፍ የምርምር ጽሁፎች አሳትሜያለሁ – ወጣት ሱራፌል ሙስጠፋ
የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ