12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በተቋማት የድርጊት መርሐ-ግብርና በፀደቀላቸው በጀት መሠረት ማሰራጨቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ
ሀዋሳ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉን ፋይናንስ ቢሮ ለ2018 በጀት ዓመት ከፀደቀለት 53.9 ቢሊየን ብር በ6 ወራት አፈፃፀም ከ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰራጨት መቻሉን፥ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት አመላክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ፋይናንስ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል።
የበጀት ድልድሉ ፍትሀዊ፣ ግልጽ፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የነበረበት፣ የወንድማማችነትን መንፈስ በማጉላት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መከናወኑን የገለፁት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፥ የክልሉ አንዳንድ መዋቅሮች በቀመር ድርሻቸው የበጀት ጉድለት እንዳይገጥማቸው በተደረገ እሳቤ ለደ/ኦሞ፣ ለኮሬ እና ለጋርዱ ዞኖች ከክልል ማዕከል ጥቅል በጀት በመቀነስ ማስተካከያ መደረጉ ክልሉ ለፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ስርዓት መሳለጥ ቁርጠኛ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።
ከአጠቃላይ በጀት የክልል ማዕከል 20 በመቶ እና የአስተዳደር እርከኖች 80 በመቶ የበጀት ድርሻ እንደነበራቸው የገለፁት አቶ ተፈሪ፥ ለታቸኛው ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመላክተው፥ የክልሉ የገቢ ፖቴንሻል በማስጠናት ከሰባት ሴክተር መ/ቤቶች፣ ከወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ፣ ከአቅም ግንባታና ፖሊስ ጥናት፣ ከገቢዎች፣ ከፕላንና ልማት ቢሮ፣ ከርዕስ መስተዳደር ጽ/ቤት፣ ከአንድ ማዕከል/መሶብ/ ፕሮጀክት እና ከፋይናንስ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የክልሉን የገቢ አቅም ለመለየት የሚያስችል ጥናት ተጀምሮ 50% መድረሱን አንስተዋል፡፡
በካፒታልና መደበኛ በጀት የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው የተለያዩ የክልል ሴክተር መ/ቤቶች ከ53 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ለደመወዝ እጥረት 16 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ከመጠባበቂያ ብር 54,043,470 ጠቅላላ ድምር ብር 124 ሚሊየን 487ሺህ 974 ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በ2018 ዓ.ም ከመስከረም ወር ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ የታወጀውና ከፌዴራል ፐብሊክ ሰርቭስ ኮሚሽን በኩል ለክልሉ የተላለፈው በጀት ብር 7 ቢሊየን 128 ሚሊየን 401ሺህ 651 ብር በቂ አለመሆኑን፥ ይልቁንም ለክልሉ ለ10 ወራት መያዝ የነበረበት የአዲሱና የነባሩ ደመወዝ በጀት ትክክለኛ ልዩነት መረጃ የማጥራት ስራ ሰርተን ብር 13 ቢሊየን 469 ሚሊየን 697 ሺህ 152.90 ብር ዝርዝር መረጃና ጥያቄ ለገንዘብ ሚኒስቴር በመላክ የጋረ መግባባትና መተማመን ተፈጥሮ ልዩነቱን ለማስለቀቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከፌዴራል መንግሥት የተገኘውን ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ለደመወዝ ጭማሪ የተመደበ በጀት ለክልል ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ለዞን አስተዳደሮች በማስተላለፍ አዲሱ የደመወዝ ክፍያ በወቅቱ መፈፀሙን ገልፀዋል።
የግዥና የክፍያ ሥርዓትን ከማዘመን አኳያ የተከናወኑ ተግባራትን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ፥ ለክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡ የክልላዊ ህትመቶችን ለማሳተም ጨረታ ካሸነፈ ድርጅት ጋር በተገባው ውል መሠረት ርክክብ ተፈጽሞ አሠራርን የጠበቀ የክፍያ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
ዘመናዊ የሪፖርት አቀራረብን ለማጠናከርም በዌብ ቤዝድ ግዥ ቁልፍ የአፈፃፀም አመላካች (KPI) ምዝገባ ሥርዓት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በቀረበው የግማሽ አመት እቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ሊብራሩና ምላሽ ያስፈልጋል ባሉት ጉዳይ ላይ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፥ የ2017 የቻናል ሁለት ፕሮግራሞች የአጋማሽ በጀት አፈጻጸም የጋራ የግምገማ መረጃ አለመኖር፣ የገንዘብ ትልልፍና የአስተዳደር ሥርዓት ጋር ተያይዞ ያለውን የአፈጻጸም ግብረ-መልስ መስጠት ያለመቻሉ እንደድክመት አንስተዋል።
በየወሩ ከክልል መ/ቤቶች እና ከዞን የቀረበ የኦዲት ሪፖርቶችን በመገምገም ግብረ- መልስ መስጠትና አፈጻጸሙን መከታተል የዓመቱ ዕቅድ 720 ሲሆን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም 361 ሲሆን አፈጻጸሙ 51.1% በመቶ መሆኑን በጉለት ያመላከቱት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፥ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች በሚታዩ የአሰራር ክፍተቶች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው አፈፃፀሙ እንዲሻሻል በበጀት ዓመት ውስጥ ለተገልጋዮች የሙያዊ የምክር አገልግሎት ለመስጠት የተያዘው እቅድ ክንውን ሊሻሻል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሐንስ የክልሉ ፋይናስ ቢሮ በበጀት አመቱ 6 ወራት የነበረው አፈፃፀም ጠንካራ እንደነበር ጠቁመው፥ ክፍተት ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበዋል።
የቢሮው ኃላፊና የዘርፍ ኃላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ዓባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ

More Stories
የግል እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን በተገቢው በመጠቀም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘውን ብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ጎበኙ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የሚገነቡት የኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል እና የፈትሁዲን ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ተገለፀ