ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት ካልሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ያስቸግራል – አቶ ቡሪሶ ቡላሾ

ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት ካልሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ያስቸግራል – አቶ ቡሪሶ ቡላሾ

በደረጀ ጥላሁን

የሳምንቱ እንግዳችን አቶ ቡሪሶ ቡላሾ ይባላሉ፡፡ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በህክምና ሞያ እና በኃላፊነት ለ17 አመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

በጤና አገልግሎቶች ግብአቶች ጥራትና ቁጥጥር ላይ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡-

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ቡሪሶ፦  እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ በትውውቅ እንጀምር

አቶ ቡሪሶ፦ ትውልድና እድገቴ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በቀድሞ አጠራሩ ከፍተኛ 2፤ 05 ቀበሌ በአሁኑ ጉዱማሌ ቀበሌ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማርኩት ኮምቦኒ ትምህርት ቤት ነው። በመቀጠል ከሆሳእና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በነርሲንግ በዲፕሎማ ተመረኩ፡፡ ከዚያም በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ከኮሌጅ የወጡ ተማሪዎች ግንባር ሄደው የሞያ ግዳጃቸውን እንዲወጡ በሰጠው መመሪያ መሰረት በ1991 ዓ/ም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከመከላከያ ጎን ተሰልፈን ለሶስት ወራት ያህል የሞያ ግዴታችንን ለመወጣት ወደ ግንባር ዘምተናል፡፡ በትግራይ ክልል ባድሜ አካባቢ ዝባን ገደባ ሆስፒታል አገልግለናል፡፡ በዘመቻ ጸሀይ ግብአት የባድሜ ምሽግ ሲሰበር እዚያው ነበርን፡፡

ንጋት፦ የሥራ አጀማመር እንዴት ነበር?

አቶ ቡሪሶ፦ ሥራ የጀመርኩት ከግዳጅ ከተመለስኩ በኋላ በቀድሞ ደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን ጤና መምሪያ አሮሬሳ ወረዳ ባለሞያ ሆኜ ነበር፡፡ በወረዳው ለአምስት አመታት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያም ቦርቻ ወረዳ ተመድቤ ሁለት አመት ከስድስት ወር በኃላፊነት ከሰራሁ በኋላ በጂማ ጤና ሳይንስ የዲግሪ መርሀ ግብር ተምሬ ተመለስኩኝ፡፡ ከዚያም ቦርቻ ወረዳ በ2000 ዓ/ም በጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ሁኜ ካገለገልኩ በኋላ ከ2003 እስከ 2010 ዓ/ም ድረስ በሸበዲኖ ወረዳ በጽ/ቤት ኃላፊነት እየሰራሁ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪነት ደርቤ እንድሰራ ተደረገ፡፡ ወረዳው በአፈፃፀሙ ግንባር ቀደም በመሆኑ ተሸላሚ ነበር፡፡ በቀድሞ ደቡብ ክልል ካሉ ወረዳዎች ሲወዳደር በተለይ በእናቶችና ህፃናት የተሰራው ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ሀገራችንን ወክለን ኢንዶኔዢያ ጃካርታ ለ28 ቀናት የልምድ ልውውጥ አድርገናል፡፡

ከ2010 ዓ/ም መጨረሻ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ በመሆን እንድሰራ የተመደብኩ ሲሆን በዚህም ኮቪድን ጨምሮ ሌሎች ከበድ ያሉ ሥራዎች የተከናወኑበት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ አስፋልትን በኬሚካል ከማጠብ ጀምሮ በየፌርማታው የመርጨት ሥራ እና ሌሎችም የመከላከል ሥራዎች በመሰራታቸው ጉዳት አልተሰተዋለም፡፡

እዛው እያገለገልኩ በአጠቃላይ ህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ከሀዋሳ ዩንቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል 2ኛ ድግሪዬን ሰርቻለሁ፡፡ በ2013 ዓም ክልሉ ሲደራጅ የሲዳማ ክልል የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆኜ እንዳገለግል ኃላፊነት ተሰጥቶኝ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፦ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ሥልጣንና ኃላፊነት ምንድ ነው?

አቶ ቡሪሶ፦ የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ የምግብ ደህንነትና ጥራትን፣ የመድሀኒት ደህንነት ፈዋሽነት፣ ጥራትና ትክክለኛ አጠቃቀምን የማረጋገጥ፤ የጤና፣ የህክምናና የመድሀኒት ባለሞያዎችን ሞያዊ ብቃትን የመከታተል፡፡ እንዲሁም የጤና ተቋማትን ብቃት እና የጤና አጠባበቅ ለህብረተሰቡ ጤና ተስማሚ መሆኑን የመቆጣጠርና የመከታተል ሥልጣን የተሰጠው አካል ነው፡፡

ከዚህ መነሻ የጤና ባለሞያዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት የሚጠበቅባቸውን ፈተና ካለፉ በኋላ ጤና ሚኒስቴር ድግሪና ከድግሪ በላይ ሲሆን በኦን ላይን ስም ዝርዝር ሲያስተላልፍ እኛም መዝግበን እንቀበላለን፡፡

ንጋት፦ ሕገ ወጥ የመድሐኒት ዝውውር ለመከላከል የተሰራው ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ቡሪሶ፦ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሀኒቶችን ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ቁጥጥር ያደርጋል። በዚህም በክልላችን የተለያዩ ሥራዎች ይሰራሉ። መድሀኒት ፈዋሽነቱና ጥራቱ ተረጋገረጦ ነው ወደ ሀገር የሚገባው፡፡ በሀገር ደረጃ የኢትዮጵያ መድሀኒት ባለሥልጣን መዝግቦ ያስገባቸው ከ 1 ሺህ 100 በላይ የሚሆኑ የተፈቀዱ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በህገ ወጥ መልክ የሚገቡ መድሀኒቶችም አሉ፡፡ እነዚህን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ክትትልና እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ በሀገራችን ያሉ የመግቢያ በሮች ብዙ ናቸው፡፡ በክልላችን በሞያሌ በኩል የሚገቡ መድሀኒቶች አሉ፡፡ እነዚህን ከሚመለከታቸው የፌደራል አካላት ጋር በመቀናጀት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፦ የተወሰዱ እርምጃዎች እንዴት ይገለፃሉ?

አቶ ቡሪሶ፦ እንደ ክልል ተቆጣጣሪ አካላት ህጋዊ ተቋማት እና ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦች መድሀኒት ሲሸጡ እና ሲያዘዋውሩ በተገኙት ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ፡፡ ክልሉ ከተደራጀ በኋላ 15 ግለሰቦች በመድሀኒት፣ ምግብ፣ እና በሌሎች አላስፈላጊ ተግባራት ውስጥ የተሰማሩት ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ከነዚህም 6 በመድሀኒት 9 ደግሞ በምግብ ነው፡፡ ስድስቱ ፈቃድ ሳይኖራቸው በመኖሪያ ቤታቸው ሲሸጡ የተያዙ ሲሆን ሌላው የጤና ባለሞያ ሆነው ፈቃድ ሳይኖራቸው በቤታቸው የሚሰሩ ናቸው፡፡ እንዲሁም መድሀኒት በአያያዝ ችግር በፌስታል ይዘው በመገኘት ወደ ህግ የቀረቡ ናቸው፡፡ እነዚህም በንሳ፣ አርቤጎናና ደራራ ወረዳ የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡

በቅርቡ ሀዋሳ ላይም የታዩ አሉ፡፡ ህግ ይዞታል፡፡ በሀዋሳ ቀደም ሲል የዛሬ አራት አመት አካባቢ በርበሬ ላይ ባእድ ነገር ቀላቅለው እና ኬሚካል ተጠቅመው በህብረተሰቡ ትብብር የተያዙ ነበሩ፡፡ ናሙናው ወደ አዲስ አበባ ተልኮ በውጤቱም ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያመጡ ተረጋግጦ ለፍትህ አካላት ቀርበው ከ3 እስከ 5 አመት እስር የተቀጡ አሉ፡፡ በዳቶ አካባቢም ባእድ ነገር የቀላቀሉ ተይዘው ወደ ህግ ቀርበዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ፈቃድ ሳይኖረው ፎርጅድ አሰርቶ ይሰራ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለህግ የቀረበ አለ፡፡

ከዚህ ሌላ የጤና ባለሞያ በየሶስት አመቱ ፈቃድ የሚያድሰው ሲሆን ይህን ለመቆጣጠር ድንገተኛ ፍተሸ እናደርጋለን፡፡ በአግባቡ መመዝገቡን እናረጋግጣለን፡፡ በዚህ ፍተሻ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች ናቸው፡፡ አንድ አመት ከስድስት ወር እስር እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡ ስራውን ስንሰራ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራን እንገኛለን፡፡

ቁጥጥር ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ሁሉንም የችግሩ ተጠቂ ስለሚያደርገው የመቆጣጠር ሀላፊነት አለበት። በቸልታ የሚታለፍ ከሆነ ችግሩን ለመፍታት የሚያስቸግር ይሆንብናል፡፡

ንጋት፦ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ግንዛቤ ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ቡሪሶ፦ ህገ ወጦችን መንግስት ብቻ ተቆጣጥሮ ችግሩን ማስወገድ አይችልም። ህዝቡን የቁጥጥሩ ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከሚዲያ ጋር በርካታ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህ አመት በተያዘው እቅድ መሰረት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሚዲያ አብዛኛውን ህብረተሰብ ጋር የሚደርስ በመሆኑ እንጠቀምበታለን፡፡ አሁንም ከደቡብ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት እየገባን መረጃ እየሰጠን ሲሆን በሲዳማ ኤስ. ኤም. ኤን /SMN/ እና በበንሳ ኤፍ ኤም ሬዲዮ እንዲሁም በሻሸመኔ ፋና በመጠቀም መረጃ እያደረስን እንገኛለን፡፡ በተለይ ለጤና ጠንቅ በሆኑ ጉዳዮችም እራሱ ህዝቡ መከላከል እንዲችል እየተሰራ ነው፡፡ እናም ህብረተሰቡ እራሱ የቁጥጥሩ ባለቤት ካልሆነ ችግሩን ለመቅረፍ አይችልም፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ መስሪያ ቤቱ መረጃ የሚቀበልበት የነፃ ስልክ መስመር 7732 የጥቆማ መስመር አለው፡፡ ህብረተሰቡ ይህን በመጠቀም ጥቆማ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከአምና ጀምሮ በህብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ አራት ሰዎች ለህግ አቅርበን ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ አሁን ላይ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው የግንዛቤ ችግር እየተቀረፈ መጥቷል፡፡

ንጋት፦ ጊዜ ያለፈባቸው መድሀኒቶች በተለይ በገጠሩ አካባቢ እንደሚስተዋል መረጃዎች ያሳያሉ ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ ቡሪሶ፦ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሐኒቶች ከከተማ ይልቅ ወደ ገጠር አካባቢ ስለሚቀርቡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ይህን ለመቆጣጠር እየተሰራ ሲሆን ቀጣይነት እንዲኖረው እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፈው አመት በተለያዩ አካባቢዎች ከንግድና ገበያ ልማት እና ከፖሊስ ጋር በመተባበር በተደረገው ፍተሸ በርካታ ምርት ማስወገድ ተችሏል፡፡ አሁንም በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል የከተሞች መስፋፋት ለህገ ወጥ ተግባራት መስፋፋት እንደምክንያት ስለሚሆኑ ጥንቃቄ ለማድረግ የግንዛቤ ማስፋት ሥራ መጠናከር አለበት፡፡ እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ህብረተሰቡን በቅርበት የሚያገኙ ስለሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ የማስፋት ሥራ በትኩረት ይሰራል፡፡

በከተሞች አካባቢ በተለይም እንደ ማር፣ ቅቤ፣ ዘይትና ዱቄት የመሳሰሉት ምርቶች ባእድ ነገሮችን ለመቀላቀል አመቺና ተጋላጭ ናቸው። በተለይ በአላት ሲቃረብ ችግሩ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ድርጊት የሚሳተፉ ግለሰቦችን የመጠቆምና የማጋለጥ ሥራ በህብረተሰቡና በሚመለከታቸው አካላት ትብብር የሚሰራ ይሆናል፡፡

ንጋት፦ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰሩ ሥራዎች የተኞቹ ናቸው?

አቶ ቡሪሶ፦ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የምንሰራው በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ በተለይም ድንገተኛ ፍተሻ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በድንገተኛ ፍተሻ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በዚህም በአንድ ወር አካባቢ ተቋማቶች ላይ ቅዳሜ እና እሁድ ምሽትን ጨምሮ ቁጥጥር ተደርጎ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድሀኒቶች በጉሙሩከ የሚያዙ አሉ፡፡ እንዲሁም በግመል፣ በሞተር ይገባሉ፡፡ ይህን ለመግታት ከቁጥጥሩ በተጨማሪ የግንዛቤ ስራው ተጠናክሮ መሰራት ይገባል፡፡ የህግ አካላትም ፈጣን ፍትህ በመስጠታቸውን ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

በጥቅሉ ከኛ ጋር ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ የፍትህ አካላት፣ የህዝብ ክንፍ የምንላቸው የወጣቶችና ሴቶች ፌደሬሽኖች ይገኙበታል፡፡

ንጋት፦ የሞያ ምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት መስፈርቱ ምንድነው?

አቶ ቡሪሶ፦ አንድ ባለሞያ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመጣ እዚሁ ይመዘገባል፡፡ ዲግሪና ከዚያ በላይ ለተማሩት ወደ 11 የሚሆኑ የሞያ ዘርፎች አሉ፡፡ በነዚህ የመውጫ ፈተና ተፈትኖ የብቃት ማረጋጋጫ ፈተና ተፈትኖ በጤና ሚንስቴር በኩል ለኛ በኦን ላይን ይላካል፡፡ በዚህ መሰረት ማለፉን አረጋግጠን ለሞያ ምዝገባ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላ በኋላ የሞያ ምዝገባ ይመዘገባል፡፡

የሞያ ምዝገባ ፈቃድ ከዚህ ቀደም በአምስት አመት ነበር የሚታደሰው አሁን ግን በሶስት አመት ነው እደሳ የሚደረገው። በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሞያ ምዝገባ ሳይወሰድ መስራት አይፈቀድም፡፡ አንድ የጤና ባለሞያ ወደ ሥራ ለመግባት የሞያ ምዝገባ ፈቃድ መያዝ አለበት፡፡ ምክንያቱም በስራቸው ችግር ቢፈጠር መንግስት ከለላ እንዲሆነው ነው፡፡

በክልሉ በርካታ ባለሞያዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር ግን ቋሚ አይደለም፡፡ የሚገቡ እንዳሉ ሁሉ የሚወጡም አሉ፡፡ ባለፈው ስድስት ወር ብቻ አዲስ የሞያ ምዝገባ ፈቃድ የተሰጣቸው ከ 1ሺህ 500 በላይ ናቸው፡፡ እንዲሁም እድሳት የተደረገላቸው ከ 1 ሺህ 200 በላይ ናቸው፡፡

ንጋት፦ መድሀኒትና ሌሎች ግብአቶችን የሚያቀርቡና የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች ፈቃድ አሰጣጥ ምን ይመስላል? 

አቶ ቡሪሶ፦ የህክምና ግብአቶችን አስመጪ ተቋማት ጅምላ አከፋፋዮች ፈቃድ የሚሰጠው የፌደራል የምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ምክንያቱም ድንበር ተሸጋሪ ምርቶችን ፈቃድ ለመስጠት በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን በመሆኑ ነው፡፡

ንጋት፦ ተጨማሪ ሀሳብ ካለዎት

አቶ ቡሪሶ፦ በሀገር ደረጃ የጤና ባለሞያ ሥነ ምግባር መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ በክልሉ ጤና ቢሮ ማናጅመንት ጸድቆ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ይህም የባለሞያ እና የተገልጋይን መብትና ግዴታ ያቀፈ ነው። ይህ ኮሚቴ ከሀያ በላይ አባላት ያቀፈ ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል። ይህም የህክምና ችግር ካለ የሚመረምርና የሚያጣራ፣ እንዲሁም በአግባቡ ያልታከመ ካለ ችግሩ የማን ነው ብሎ ይመረምራል ያጣራል፡፡

ሌላው የጤና ባለሞያዎች የሞያ ምዝገባ ፈቃድ በተገቢው ተመዝግበው ከወሰዱ በኋላ ተወዳድረው ወደ ሥራ መሰማራት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ማንኛውም የጤና ባለሞያ የሞያ ምዝገባ ፈቃድ ሳይወስድ ወደ ሥራ መግባት አይችልም፡፡ ለሥራ እንዲያመችም የሞያ ምዝገባ ፈቃድ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኦን ላይን በማመልከት መውሰድ ይቻላል፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ቡሪሶ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡