አንድ ነገር ቢጎድልህም ሌላ ነገር ተሰጥቶሀል – ወጣት ቢኒያም በሪሶ
በደረሰ አስፋው
ለዓላማው ትኩረት ይሰጣል፡፡ ይህንኑ ለማሳካት የሚጋደል ነው፡፡ ስራን ይወዳል፡፡ ካለስራ መቀመጥ፤ ውሎ ማደርም ለእሱ ትርጉም የለሽ ህይወት አድርጎ ይመለከታል፡፡ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችም ፀንቶ የማለፍ ልምድ አለው፡፡ እነዚህም የአሸናፊነት ስነ ልቦናን አላብሰውታል፡፡ በአካል ጉዳቱ እራሱን ደካማ አድርጎ አይመለከትም፤ ከዚህ ይልቅ እችላለሁ የሚለውን አስተሳሰብ ያነገበ ነው፡፡
በምህንድስናው ዘርፍ ከሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ለ5 ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ በተመረቀ ማግስት በተማረበት የትምህርት ዘርፍ መንግስትንና ህዝብን ለማገልገል በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ ተቋማትን ደጅ ጠንቷል፡፡ ይሁን እንጂ ምኞቱ አልተሳካም፡፡ ተቋማት የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጡት ከደጃቸው ይመልሱት ነበር፡፡
በዚህ ውጣ ውረድ ተቀጣሪ ለመሆን የነበረውን ምኞት ገታ፡፡ “ዕድሜና ጤና ለወላጆቼ ይስጥልኝ” እንዳለውም ቀደም ሲል ወላጅ እናቱ ይሰሩበት የነበረውን የፎቶ ኮፒ ማሽን ሰጥተውት በዚሁ ስራ ተሰማራ፡፡ ይህ የስራ ጅማሬው ከቤት ወጥቶ ለመግባት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ራዕዩንም የሚያደላድልበት ሆኖ ተመለከተው፡፡ ከፎቶ ኮፒ ባሻገር ተጨማሪ የስራ ዕድሎችንም እንዲመለከት ዕድል ፈጠረለት፡፡ የዛሬ አምስት አመት የጀመረው የፎቶ ኮፒ ማሽን ስራም ዛሬ ለደረሰበት ስራ መነሻና መሰረት እንደሆነው ገለጸልን፡፡
ወጣቱ አካል ጉዳተኛ በሀዋሳ ከተማ አሮጌው መናኸሪያ ፊት ለፊት የስራ ቦታው ነው፡፡ በዚህ የስራ ቦታው ቀደም ሲል ከጀመረው የፎቶ ኮፒ ስራ በተጨማሪ በሌሎች ተጨማሪ ስራዎች ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ያገኘነውም በስራ ላይ እያለ ነው፡፡ ከፎቶ ኮፒ ስራው በተጨማሪ ሌሎች ግብአቶችን ገዝቶ ጽህፈት አገልግሎት፣ የመጠረዝ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በሞባይል እና ኮምፒውተር ጥገና ላይ መሰማራቱን በስራ ቦታው ካሉ ቁሳቁሶች መረዳት ችለናል፡፡ አጭር የሆነ ጊዜውን እንዲያጋራን ጠይቀን ቆይታ አደረግን፡፡ በመተዋወቅም ጀመርን፡፡
ወጣት ቢኒያም በሪሶ ይባላል፡፡ የተወለደው ይርጋለም ከተማ ቢሆንም ዕድገቱ ግን ሀዋሳ ከተማ ቴሶ ቀበሌ ነው፡፡ ትምህርቱንም በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ቀደም ሲል ከላዕድ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሮ እስከ 1ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ከ2ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ፊሊጶስና ቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ አካዳሚ መከታተሉን ተናግሯል፡፡
የ12ኛ ክፍል ፈተናን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የመግባት ዕድል አገኘ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በምህንድስና ዘርፍ በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ተምሮ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2013 ዓ.ም ይዟል፡፡ ከዚህ በኋላ በነበረው ህይወትም እንደማንኛውም ሰው ተቀጣሪ ለመሆን የትምህርት ማስረጃዎቹን ጨብጦ የበርካታ የመንግስትና የግል ተቋማትን ደጅ መጥናቱን ያስታውሳል፡፡ የቀድሞ የደቡብ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮንም በተደጋጋሚ እንደጎበኘው በመጥቀስ፡፡
የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም በማህበረሰቡ አካል ጉዳተኞች አይችሉም የሚለው የአመለካከት ችግር ነጸብራቅ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አለው፡፡ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁትን ሲኦሲ የማይመለከት ሆኖ ሳለ ሲኦሲ ይጠየቅ ነበር፡፡ በሌላ ቦታ ደግሞ ሌሎች ምክንያቶች ይሰጡት ነበር፡፡ እነዚህ ምክንያቶች አሁን ለተሰማራበት የስራ መስክ በር ከፈቱለት፡፡
በወቅቱ የፎቶ ኮፒ ስራ የሚሰሩት ወላጅ እናቱ ነበሩ፡፡ ታዲያ በቁጭት ውስጥ የነበሩት እናት ይህን ስራ ለልጃቸው ሲሰጡት በደስታ እንደነበርም ነው የገለጸው፡፡ የልጃቸውን ቢኒያም የወደፊት ተስፋ ለማለምለም ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡ በዚህም ወላጆቹ ያደረጉለትን ድጋፍ ለማመስገን እንኳ ቃላት ያጥረኛል ሲል ነው የገለጸው፡፡ በርካታ አካል ጉዳተኞች ከቤት እንዳይወጡ ታፍነው በሚቀመጡበት ጊዜ እሱ ግን በተደላደለ ሁኔታ ይኖር ነበር፡፡ ተምሮ ለቁም ነገር እስኪደርስ በቤተሰቡ የሚደረገው ድጋፍ የተለየ እንደነበር ዛሬም ከህሊናው የጠፋ አይደለም፡፡
በስራው የጽህፈት አገልግሎት፣ የፎቶ ኮፒ አገልግሎት፣ የመጠረዝና ሌሎች አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ በስራው ለመለወጥ ራዕይ ያለው ቢኒያም በሌላም ተጨማሪ ስራ ለመሰማራት አቀደ። ለዚህም ይረዳው ዘንድ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ስልጠና ወሰደ፡፡ በዚህ አጭር ስልጠናም በሞባይል እና ኮምፒውተር ጥገና በቂ ክህሎት አግኝቶ ወደ ስራው ተሰማርቷል፡፡ የሞባይል አክሰሰሪዎችንም ይሸጣል፡፡ የጥገና ስራውን እሱ ሲያከናውን የኮፒ፣ የጽህፈትና የጥረዛ ስራውን ደግሞ አንድ ሰው ቀጥሮ እያሰራ ነው የሚገኘው፡፡ ስራው ከቤት ከመቀመጥ አውጥቶ ተጠቃሚም ስላደረገው ለስራው ክብር አለው፡፡ ለሌላ ሰው የስራ ዕድል በመፍጠሩም ደስተኛ ነው፡፡
በአንድ ፎቶ ኮፒ ማሽን የተጀመረው ስራው በተለያዩ ግብአቶች የተደራጀ ሆኗል፡፡ ለጥገናም ይሁን ለጽህፈትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግብአቶችን አሟልቷል፡፡ እሱ በስራው ከተሰማራ በኋላ ለደንበኞቹ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳው ዘንድ በርካታ ግብአቶችን ገዝቷል፡፡ በተለይ በሞባይል እና ኮምፒውተር ጥገና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማሟላት በርካታ ገንዘብ ለግዥ ማውጣቱን ነው የገለጸልን፡፡ በስራውም ቢሆን በንግድ ስራ ከተሰማሩ ቤተሰቦቹ ጋር በሀሳብ ይደጋገፋሉ፡፡ ይህም ለውጤቱ አጋዥ እንደሆነ ይናገራል፡፡
“ዛሬ ላይ በርካታ አካል ጉዳተኞች በብዙ ተጽእኖ ውስጥ እንዳሉ እመለከታለሁ፡፡ በቤት ውስጥ ታፍነው እንዳይማሩ ይደረጋል፡፡ ይህም አምራች ዜጎች እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ ችግሩ ደግሞ የሚጎላው የራሴ በሚሉት ቤተሰብ ነው፡፡ ማህበረሰቡም አካል ጉዳተኞች አይችሉም የሚል አመለካከት አለው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተደማምረው የአካል ጉዳተኛውን ህይወት ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ እኔ እንደመታደል ሆኖ እነዚህ ችግሮች አላጋጠሙኝም፡፡ ለስራ ፍለጋ ስንቀሳቀስ ካጋጠመኝ መጠነኛ ችግር ውጪ፡፡ ወላጆቼ ከሌሎች ልጆች በላይ እንክብካቤ እያደረጉልኝ ነው ያደኩት፡፡ ጊዜያቸውን ቅድሚያ ለኔ በመስጠት ነው ያሳደጉኝ፡፡ በዚህም እድለኛ ነኝ እላለሁ”
ለወጣት ቢኒያም በዚህ ስራ መሰማራቱ በርካታ ጥቅሞች አስገኝተውለታል፡፡ ስራ አለኝ ብሎ መውጣት መግባቱ አንዱ ጥቅም እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የራሱ የሚለውን ሀብት መፍጠሩም ሌላው ጥቅሙ እንደሆነ ነው የሚገልጸው፡፡ በዩኒቨርስቲ ለአምስት አመት ቆይቶ በተመረቀበት የሙያ ዘርፍ ተቀጣሪ መሆን ባይችልም የራሴ የሚለው የስራ ዘርፍ ላይ በመሰማራቱ ደግሞ የአእምሮ እርካታ በማግኘቱም ደስተኛ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ በተለይ ለአካል ጉዳተኛው ሰው ልዩ ትርጉም ያለው እንደሆነም ነው የተናገረው፡፡
በተፈጥሮ በሁለት እግሮቹ ላይ ባጋጠመው የአካል ጉዳት ክራንች እየተጠቀመ ነው ስራውን የሚሰራው፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎትም ቤተሰቦቹ የለገሱትን የሶስት እግር ሞተር ሳይክል ይጠቀማል፡፡ በስራው ላይ ደረሰብኝ የሚለው ችግር እንደሌለ ያነሳል፡፡
“አካል ጉዳተኛ ሲኮን ብዙ ነገሮችን ታገኛለህ እንዲሁም ታጣለህ። አንዳንድ ጊዜ ቅድሚያ ለአካል ጉዳተኛው የሚል እንዳለ ሁሉ አካል ጉዳተኝነትህም የሚዘነጋበት ጊዜ አለ፡፡ በከተማዋ ካለው የነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ የተወሰነ ጊዜ ችግር የደረሰብኝ ቢሆንም በቅርቡ ግን የሚመለከተው አካል ችግሬን አይቶ እልባት ሰጥቶኛል፡፡ ከዚህ መጠነኛ ችግር ውጪ የደረሰብኝ ችግር የለም” ሲል ነው የገለጸው፡፡
“በአሁን ወቅት በርካታ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ በርካታ አካል ጉዳተኞች ከራሳቸው የአመለካከት ችግር በጎዳና ላይ ወጥተው ይለምናሉ፡፡ ለአልባሌ ሱስም ተጋልጠው እመለከታለሁ፡፡ ስለዚህ አካል ጉዳተኛ መሆን ለልመና የተፈጠረ አለያም አለመቻል አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ለዚህም አካል ጉዳተኞች እግር ቢጎዳ በእጅ መስራት ይችላሉና ከዚህ አይነት የአመለካከት ችግር መውጣት ይገባቸዋል፡፡ አንድ ነገር ቢጎልህም ሌላ ነገር እንደተሰጠህም ማሰብ ይገባል፡፡ አካል ጉዳት ተፈልጎ የመጣ ባይሆንም ከሆነ ግን አስተሳሰብን መለወጥ ይገባል፡፡ በዙሪያችን ያለውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል፡፡
“አንዳንዴ ሞባይል ሊያስጠግኑ መጥተው አይተው ይህ ለአንተ አይሆንም በማለት መልሰው የሚወስዱ አሉ፡፡ ይህ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ አትችልም የሚል መገለጫ ነው፡፡ ወደ ሙያው ስገባ ተጨባጭ ክህሎት ጨብጬ እንጂ እንዲሁ አይደለም፡፡ ግን የማህበረሰቡ አመለካከት የተለወጠ ባለመሆኑ አካሌን አይቶ አትችልም ይላል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ለውጥ ባለመሆኑ ተስፋ ሳይቆረጥ በመስራት ችግሩን ማሸነፍ ይቻላል፡፡ መለመን ግን የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞች ከመለመን ይልቅ እንዲሰሩና እንዲለወጡ እመክራለሁ” ሲልም አስተያየቱን ይሰጣል፡፡
ወጣት ቢኒያም አሁን የተሰማራበትን የስራ መስክ የማስፋፋት ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህም ብድር የሚያገኝበት እድል ቢመቻች በስራው ከዚህ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆንና ለሌሎችም የስራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እንዳለው ነው የተናገረው፡፡ የዚህ አይነት ድጋፍና ማበረታቻ አካል ጉዳተኞችን የሚያነሳሳና ለብዙዎች ምሳሌ መሆን እንደሚቻል ነው የተናገረው፡፡
የአካል ጉዳተኞች ማህበር አባል እንደሆነ ያነሳል፡፡ የማህበሩ አባል መሆኑ በአንዳንድ ውይይቶች ላይ እንዲሳተፍ ዕድል ቢፈጥርለትም ማህበሩ የተጠናከረ ባለመሆኑ ግን የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም እያስከበረ አይደለም፡፡ ይህ መጠናከር አለበት ሲልም ነው አስተያየቱን የሰጠው፡፡
ወጣት ቢኒያም ወደ ስራ የገባበት ጊዜ አጭር ቢሆንም በየእለቱ ከሚያገኘው ግን ይቆጥባል፡፡ ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች በማሟላትም ተጨማሪ ሀብት ፈጥሮበታል፡፡ ለጽህፈት አገልግሎት የሚውሉ ኮምፒውተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽን፣ የመጠረዣ ማሽኖችንና ሌሎች ንብረቶችን አፍርቷል፡፡ ለዚህም ካፒታልህ ምን ያህል ደርሷል ብለን ላነሳንለት ጥያቄም ይህን ያህል ነው ለማለት ድፍረቱ ባይኖረኝም አሁንም የተሻለ ሀብት ለመፍጠር እተጋለሁ ሲል ተናግሯል፡፡
የስራ ቦታውን ተከራይቶ ነው የሚሰራው፡፡ አከራዩም ቢሆን እሱን ለማገዝ በኪራይ ዋጋ ጫና ስላላደረጉበት ምስጋናውን ነው የቸራቸው፡፡
“በመጨረሻም አካል ጉዳተኞች መስራት እንችላለን፡፡ ጎዳና ላይ ወጥተን አንለምን። በልመና ህይወት አይመራም፡፡ ዛሬ ተለምኖ ቢገኝም ነገ ላይደገም ይችላል፡፡ በተሰጠን ችሎታ ተጠቅመን እራሳችንን በበጎ ጎን በማህበረሰቡ ውስጥ መግለጽ አለብን፡፡ ያለንበት ዘመን የግሎባላይዜሽን ዘመን በመሆኑ ከዘመኑ ጋር መራመድ አለብን፤ እሱም በስራ በመትጋት ህይወታችንን መለወጥ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
More Stories
ችግር ፈቺ የሆኑ አለም አቀፍ የምርምር ጽሁፎች አሳትሜያለሁ – ወጣት ሱራፌል ሙስጠፋ
የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ
ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን