ችግር ፈቺ የሆኑ አለም አቀፍ የምርምር ጽሁፎች አሳትሜያለሁ – ወጣት ሱራፌል ሙስጠፋ
በተስፋዬ መኮንን
ትውልድ እና እድገቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፥ በስልጤ ዞን፥ ስልጢ ወረዳ ነው። በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኝ ታታሪ፣ ስራ ወዳድና ሙሉ ጊዜውን በመስጠት የሚተጋ የአላማ ሰው ነው።
ሀገር የምትለወጠው በትምህርት እና በስራ መሆኑን አስቀድሞ በመረዳቱ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጣል። እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጽናት እየተሻገረ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል። የዛሬው የንጋት እንግዳችን ወጣት ሱራፌል ሙስጠፋ ይባላል። ከንጋት ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ። (ውድ አንባቢዎቼ እንግዳችንን አንተ ያልኩት ዕድሜውን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ!)
ንጋት:- የዛሬ የንጋት እንግዳ ለመሆን ላቀረብንልህ ጥሪ በጎ ምላሽ በመስጠትህ በዝግጅት ክፍሉ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ!
ሱራፌል:- እኔም የስራና የህይወት ልምዴን እንዳካፍል እድሉን ስላገኘሁ በጣም አመሰግናለሁ።
ንጋት:- የትምህርት ቤት ቆይታህ እና ስለደረስክበት ስኬት የውይይታችን መነሻ ቢሆን?
ሱራፌል:- ለትምህርት የተለየ ፍላጎት አለኝ፡፡ እንደምታውቀው በወጣትነት ዘመንህ መማር በህይወትህ ላይ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ትርጉም ይኖረዋል። እኔም ያለኝን ጊዜ ለትምህርት ማዋል ችያለሁ።
ንጋት:- የመጀመሪያ ዲግሪህን የትኛው ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርከው? ሌሎች በትምህርት ዘርፍ ያስመዘገብካቸው ውጤቶች ካሉ ብታጫውተኝ?
ሱራፌል:- የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቄያለሁ። ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪዬን ተቀብያለሁ።
የኤራስሙስ ሙንዱስ የአለም አቀፍ የነጻ ትምህርት ዕድል፣ በትምህርት መርሃ ግብሩ ስር በሶስት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በፈረንሳይ Aix-Marseille ዩኒቨርሲቲ፣ ሌላው በፖላንድ Wroclaw Science and Technology ዩኒቨርሲቲ፣ ሶስተኛውም በጣሊያን Tor Vergata ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ናኖ ምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪዬን ማግኘት ችያለሁ።
ንጋት:- መነሻህ በሆነው በጅማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ምን ያህል ጊዜ ሰራህ?
ሱራፌል:- በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለ3 ዓመታት በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ትምህርት አለም ገባሁ።
ንጋት:- አሁን የት ሀገር እና ምን እያጠናህ ነው?
ሱራፌል:- አሁን በአሜሪካን ሀገር በኖርተህስተርን ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የፒኤችዲ ትምህርት እየተከታተልኩ ነው። በዩኒቨርሲቲው ምርምሬንም በ”Sodium ion” ባትሪዎች ላይ ነው የምሰራው። ይህ ምርምር ምርጥ የሆነ የኃይል ማከማቻ ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር የተሻለ መንገድ የሚሆን ሲሆን በምርምሩ ውስጥ አዲስ ውጤት ለማስገኘት ጥረት እያደረኩ ነው።
ንጋት:- ለምርምር ስራህ መነሻ ሀሳብ ምንድነው?
ሱራፌል:- እንደሚታወቀው የምርምር ስራ በዋነኛነት የሚመነጨው ከአካባቢህ አሊያም ከሀገርህ ችግር መነሻነት ነው። የየትኛውም የሀገር እድገት መሰረት ሳይንስና በዘርፉ የሚገኘው እውቀት ነው። የምርምር ስራዎች በስፋት በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙና እውቅና እንዲያገኙ ሲደረግ በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎችን ትኩረት ይስባል።
በኢትዮጵያ የምርምር ታሪክ የእድሜውን ያህል ውጤት ያላስመዘገበ በመሆኑ ሃገራዊ የምርምር ስትራቴጂ በአዲስ እይታ ሊቃኝና የምርምር የትኩረት መስኮችን በልዩ ትኩረት ሊቀረጹ፣ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ተወስደው በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።
የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ችግር ፈቺ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ከማህበረሰቡ የልማት ፍላጎትና ከሃገራችን የትኩረት አቅጣጫ ጋር የተጣጣሙ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ የጤፍ ተረፈ ምርት በቀላሉ በአርሶ አደሩ አካባቢ ይገኛል። ይህንን በመጠቀም የህብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚያስችል ምርምር ማድረግ ይቻላል።
ንጋት:- በአለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የጥናትና ምርምር ጽሁፍ ማሳተም እንደቻልክ ሰምቻለሁ፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ሱራፌል:- እውነት ነው፤ እኔ ከትምህርት በተጨማሪ ምርምር ላይ ነው ጊዜዬን የማሳልፈው። በተለይ በአለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ እኔ ስራ አልፈታሁም። ማንበብ፣ መመራመር እና አዲስ ነገር የመፍጠር ዝንባሌዬን ወደ ውጤት ለመቀየር ጥረት ሳደርግ ነበር።
ንጋት:- የምርምር ስራዎችህ ምን ያህል ችግር ፈቺ ናቸው?
ሱራፌል:- የእኔ ምርምር ሁለት ወሳኝ የሳይንስ መስኮችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህም የአካባቢ ንጽህና ማሻሻያ እና የባትሪ ቴክኖሎጂዎች ናቸው። በአለም አቀፍ ጆርናል የታተሙ የምርምር ስራዎቼ ለውሃ ንጽህና የሚያገለግሉ የባዮ-ቤዝድ አድሶርቤንቶች እና ለተልእኮ ባትሪዎች የሚያገለግሉ አዳዲስ ኤሌክትሮድ ቁሶችን ያካትታል። የምርምሩ ዋና ደረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
በአገራችን ለምግብነት የሚውለው ጤፍ ከዚህ የሚገኘው ተረፈ ምርት ወይንም ገለባ ላይ የተመሰረተ አክቲቬትድ ካርቦን በመጠቀም ሊድ (Pb II) ማስወገድ ነው። በዚህ ጥናት ማክሮዌቭ-አስስተዋል ፓይሮሊሲስ በመጠቀም ከጤፍ ገለባ አክቲቬትድ ካርቦን ማዘጋጀት ነው። ይህ ምርምር አዲስ አድሶርቤንት የሊድ አዮኖችን ከተበከለ ውሃ በብቃት ሊያስወግድ እንደሚችል በጥናቱ ተረጋግጧል። የጥናቱ ዋና ግብ የግብርና ተረፈ ምርትን በመጠቀም ካንሰር አምጪ የሆውን ንጥረ ነገር ከውሃ ማስወገድ ነው።
በሁለተኛው ጥናት ደግሞ የስኳር ባጋስ ላይ የተመሰረተ አክቲቬትድ ካርቦን በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የተበከለ ውሃን ማጽዳት ላይ ያተኩራል። የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የሚፈጥረውን ውሃ ብክለት ለመቋቋም ከስኳር ባጋስ አክቲቬትድ ካርቦን ማዘጋጀት ነው።
ይህ ጥናት ባዮሎጂካል ኦክስጅን ዲማንድ (BOD) እና ኬሚካል ኦክስጅን ዲማንድ (COD) ከተበከለ ውሃ ለማስወገድ የሚያስችል የጥናት ውጤት ነው። ውጤቶቹ የግብርና ተረፈ ምርት ኢንዱስትሪያዊ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል ነው።
3ኛው ጥናት የላንታነሀም ዶብድ ማግኔቲክ ከጤፍ ገለባ ባዮቻር ፍሎራይድ ማስወገድ ነው። በሀገራችን በከርሰ ምድር ውሃ ውስጥ የሚገኘውን ፍሎራይድ ብክለት ለመቋቋም ከጤፍ ገለባ እና ንታኑም-የቀለጠ ማግኔቲክ ባዮቻር እንዲዘጋጅ የሚያስችል ነው።
ይህ ፍሎራይድን በብቃት ማስወገድ እንደሚችል በማሳየት ለውሃ ደህንነት ዝቅተኛ ወጪ ያለው እና ስኬል የሚደረግበት መፍትሔ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል። በ4ኛ ደረጃ የኒኬል ኮምፕሌክስ-ቤዝድ ኤሌክትሮዶች ሊትየም-አዮን ባትሪዎች እና በኢትዮጵያ የኢነርጂ ሽግግር ላይ ያላቸውን ሚና የሚያመላክት የጥናት ውጤት ተጠቃሽ ነው።
የኢነርጂ አከማቸትን ዘርፍ በማስፋት የኒኬል-ቤዝድ ኩይኖን ኮምፕሌክሶችን ለአዲስ ትውልድ ተልእኮ ባትሪዎች ኤሌክትሮድ እንዲሆኑ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህ ጥናት የኤሌክትሮ ኬሚካል እንቅስቃሴያቸውን በመተንተን በሊትየም-አዮን ባትሪዎች ውስጥ አስፈላጊ እና ተግባራዊ እንደሆኑ አረጋግጧል።
በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት ላይ ያለው ጥገኛነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተልእኮ ባትሪዎች ልማት ለኢነርጂ ዋስትና እና ዘላቂነት ወሳኝ መሆኑን የሚያመላክት ነው። የምርምር ስራዎቼ በዋጋ ተመጣጣኝ የኤሌክትሮድ ዕቃዎችን በመለየት የኢነርጂ አከማቸትን ተደራሽነት እና የተሻለ ስነ ምህዳር መፍጠር ላይ የሚያተኩር ነው።
እንደዚህ አይነት ጥናቶች የኢትዮጵያን የኢነርጂ መሠረተ ልማት ለመደገፍ እና ከነዳጅ ጥገኛነት ለመውጣት ይረዳል። የምርምሩ ተጽዕኖ በኢትዮጵያ እና በዓለም ላይ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በተለይ የሀገራችንን ማህበረሰብ የተቀናጀ ችግሮች ለመፍታት ያግዛል።
በነዚህ እና በመሰል የጥናት መስኮች በ“Highly rebuttable journal” ከ16 በላይ የሚሆኑ የምርምር ስራዎቼን ማሳተም ችያለሁ። በጉግል ስኮላር (Google Scholar) መሰረት፣ የምርምር ጽሑፎቹ ከ600 በላይ ሳይቴሽን (ተቀባይነት) አግኝተዋል። ይህም ስራው በዓለም አቀፍ ምርመራ ማህበር ላይ ያሳየውን አስፈላጊ ተፅእኖ ይገልፃል።
ይህ ምርምር ኤክስፐርት እንድሆን አድርጎኛል። በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚገኘውን የጤፍ ገለባ በመጠቀም አክቲቬትድ ካርቦን እና ሌሎች ዋጋ ያላቸው ንብርብሮችን ለማምረት ያግዛል። ምርምሩ፡-
– የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ
– ለአርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ እድሎችን ለመፍጠር
– የውሃ ማጽዳት /ንጽህና መጠበቅ/ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያግዛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሀገራት የሚጋፈጡት የኢንዱስትሪ ብክለት፣ የውሃ ብክለት እና የኢነርጂ አከማቸት ችግሮችን ለመፍታት በዘርፉ ያደረግኩት ምርምር አዳዲስ ዘላቂ አማራጮችን ያቀርባል።
ንጋት:- ቀጣይ ህልምህ ምን እንደሆነ ብታብራራልኝ?
ሱራፌል:- እንደሚታወቀው ትምህርት አለምን የምትለውጥበት መሳሪያ ነው። ይህን መነሻ በማድረግ በትምህርት እና በምርምር ስራዬ ንጹህና የታዳሽ አማራጭ ኢነርጂ መፍጠር፣ ሁለንተናዊ ነጻነት ያለው እና የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅ እፈልጋለሁ።
የምርምር ስራዎቼ በውጤት ላይ የተመሰረቱ እና የማህበረሰቡን ህይወት የሚያቀሉ እንዲሆኑ መስራት የዘወትር ህልሜ ነው። በተለይም የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል። ጀማሪ ተመራማሪዎች እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ በማድረግ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ ሊሆን ይገባል።
ጥናትና ምርምሮች በሚካሄዱበት ወቅት ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ከሳይንስ ጋር አቀናጅቶ ለማህበራዊ ችግር መፍቻ ለመጠቀም መስራት ይገባል። የምርምር ውጤቶች ተግባራዊ ሆነው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት አለባቸው።
ንጋት:- ከሀገር ውጪ ስትማር በሀገሬ በኖረ ብለህ የተመኘኸው ነገር ካለ ብታጫውተኝ?
ሱራፌል:- ወደ ውጭ ሀገር ስትሄድ የሰዎችን የዕለት ተዕለት ህይወት የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎች ምናለ በሀገሬ በኖሩ ብለህ ትመኛለህ። ዘላቂ ልማት እና እድገት የሚገኘው በጥረት ነው። ውጭ ሀገር ያለው የስራ ባህል፣ የጊዜ አጠቃቀም እና መሰል ጉዳዮች በኢትዮጵያም ተግባራዊ ቢደረጉ የሚል ሀሳብ አለኝ። ከራሴ ህይወት ጋር ሳገናኘው ደግሞ በተለይ ለእንደኔ አይነት ተመራማሪ ለምርምር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ለስራዬ ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በመሆኑም የምርምር ቁሳቁሶች እና ተያያዥ ግብአቶች በኖሩ ብዬ ተመኝቻለሁ።
ንጋት፡- ጥያቄዎቼን አጠናቅቄያለሁ ለነበረን መልካም ጊዜ እጅግ ከልብ አመሰግናለሁ።
ሱራፌል፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
አንድ ነገር ቢጎድልህም ሌላ ነገር ተሰጥቶሀል – ወጣት ቢኒያም በሪሶ
የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ
ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን