ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን በየደረጃው ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ።

“ተሳትፏችንን እናሳድጋለን ምሁር አክሊልን እናለማለን ” በሚል መሪ ቃል የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት በሃዋርያት ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለፁት በጉራጌ ዞን በየደረጃው ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በምሁር አክሊል ወረዳ ካለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ በልማት ዘርፍ ላይ በርካታ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የማህበረሰቡ ባህል፣ ቋንቋ ሌሎችም የማንነት መገለጫ የሆኑት እሴቶችን ከማስተዋወቅና ጠብቆ ለማቆየት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስረድተዋል ።

በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የመማር ማስተማሪያ ግብዓቶችን ከማሟላት አኳያ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ላጫ፥ ወጣቱ ጊዜና ጉልበት ከሚያባክኑ ከመጠጥና ከተለያዩ ሱሶች በመላቀቅ ስራ ፈጥሮ መስራት ይኖርበታል ሲሉም አስገንዝበዋል ።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በበኩላቸው በወረዳው አመራሩና ማህበረሰቡ በመቀናጀት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፥ ማህበረሰቡ ከመንግስትና ከፓርቲ ጎን በመቆም በወረዳው ያሉ እምቅ ጸጋዎችን በተገቢው በመጠቀም የተጀማመሩ የልማት ስራዎችን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡ እሴቱን ከመጤ ባህል በመጠበቅ ባህልና እሴቶቹን ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ በወረዳው ባለፉት አመታት ማህበረሰቡን በማሳተፍ በሁሉም ዘርፍ በተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አበረታች ስራዎች መሰራታቸውንና ማህበረሰቡንም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ተግባሩ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎአቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በወረዳው በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች ከዚህ ቀደም ያነሷቸው የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆኑንም አንስተዋል።

አክለውም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ወረዳዋ ይበልጥ እንድትለማ ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክተዋል ።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን