የሸማቹ መብት በማስከበር የተረጋጋ የንግድ ስራ መፍጠር ይገባል – የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን

የሸማቹ መብት በማስከበር የተረጋጋ የንግድ ስራ መፍጠር ይገባል – የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን

ሀዋሳ: ጥቅምት 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአዋጅ የተቀመጠለትን የሸማቹ መብት በማስከበር የተረጋጋ የንግድ ስራ መፍጠር ይገባል ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ገለጹ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የ2017 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት አመት እቅድ ላይ ያተኮረ ሴክቶሪያል ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ በ2017 በጀት አመት በንግዱ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት መምሪያው በክልል ደረጃ ግንባር ቀደም ከመሆኑም ባለፈ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ የተቀመረባቸውና እውቅና የተሰጣቸው ስራዎችን ሰርቷል።

በ2018 በጀት አመትም ይህንኑ ውጤታማነትን በማጠናከር በተለይም በአዋጅ የተቀመጠለትን የሸማቹ ማህበረሰብ መብትን በማስከበር የተረጋጋ የንግድ ስራ እንዲኖር ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ቤተልሄም ታደሰ በበኩላቸው በባለፈው በጀት አመት በንግድ ስርአቱ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል ።

የሰንበት ገበያዎችን ከማጠናከር ባሻገር ከ20 ሺህ 594 በላይ ያህል ለሚሆኑ ሸማቾችና የንግዱ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የንግዱ ዘርፍ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ስለመሰራቱም ገልጸዋል።

ሴክቶሪያል ጉበኤው ”ሞጋች ሸማችና ሀላፊነት የሚሰማው ነጋዴ መፍጠር ለፍትሐዊ የንግድ ስርዓት ውጤታማነት”፣ ”ከሰንበት እስከ ሰንበት የግብይት ማዕከላትን በሁሉም መዋቅሮቻችን በማስፋት ሸማቹ ማህበረሰብ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኝ ተግተን እንሰራለን!” የሚሉ መሪ ቃሎችን ይዞ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በጉባኤው የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ እንዳልካቸው ጌታቸው፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሰለ ጫካ፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳን አቶ ሁሴን ሽፋን ጨምሮ የዞን ፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በ2017 በጀት አመት ጥሩ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮችና ፈጻሚዎች እውቅና እንደሚሰጥም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ: አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን