የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ

የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ

በምንተስኖት ብርሃኑ

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ እና ዋነኛዉ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ነው፡፡፡ ሃገሪቱ በ2015 ዓ.ም በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ እና በአቮካዶ ልማት ያስመዘገበችውን ውጤታማ ስራ መሰረት ያደረገ ለአራት አመታት የሚተገበር “የሌማት ቱሩፋት” የተሰኘ ሃገር አቀፍ ፕሮግራም ቀርጻ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮና ማር ምርቶች ላይ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ እንደ ሃገር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ህልም የሰነቀ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ፕሮግራሙ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ድህነትን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም የኑሮ ዉድነትን ለማቃለልና ለዜጎች የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ሚናው የጎላ በመሆኑ በሃገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ከሆኑ አካባቢዎች መካከል የሲዳማ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡

ለዚህም ማሳያው በሥራው እየተሳተፉ ካሉ ዜጎች ተጠቃሚነት ባሻገር፤ የእነሱን ተሞክሮ ለማየት የሚመጡ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምስክርነት ነው፡፡ ክልሉን ከጎበኙ የሥራ ኃላፊዎች መካከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ባለፈው ዓመት ያደረገው ምልከታ አንዱ ነው፡፡ በጉብኝቱ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ካስጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተከናወኑ የንብ ማነብ፣ የወተትና የዶሮ መንደር ምስረታ ክልሎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል፡፡

የሲዳማ ክልልም በመርሃ-ግብሩ እንደ ክልል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ስምንት ኢኒሼቲቮችና 68 ፓኬጆች አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን በማንሳት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ናቸው፡፡ ሚንስትሯ ከሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር በመሆን በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ከጎበኙ በኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክልሉ በዋናነት በሌማት ትሩፋት ላይ በማተኮሩ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን በማንሳት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን በመስክ ቆይታቸው መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ በወተት ሀብት ልማት፣ በዶሮ እርባታና መሰል ልማቶች ለሌሎችም አካባቢዎች ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢ ጥበቃ እና ከዚህ በፊት ወደ ልማት ያልገቡ አካባቢዎች ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግ ብዙ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመረውን በምግብ እራስን የመቻል ውጥን ለማሳካት የክልሉ መንግስት የወል መሬቶች ወደ ልማት ማስገባት መቻሉን አድንቀዋል። በዚህ ረገድ ጦም ሲያድር የነበረን መሬት በኩታ ገጠም ጤፍ በማልማት የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን በማንሳት የክልሉ አጠቃላይ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን መስክረዋል፡፡

የክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆንባ ለኢፕድ እንዳሉት፤ በክልሉ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ በመጠቀም የእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡ በስራው የቤተሰብ ብልፅግናን ከማረጋገጥ ጀምሮ ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር፤ ገበያን ማረጋጋት እና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሰፊ ግብ ይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

በዚህም ቢሮው 7 ፓከጆችን በመቅረጽ በወተት፣ በዶሮ፣ በዓሣና በሐር ትል ልማት የማህበረሰቡን ኑሮ ለመቀየርና በሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት ለበርካታ ሥራ አጥ ዜጎች ሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ለእንስሳት እርባታ ካለው ምቹነት አንጻር፤ በተለይ በወተት ምርት፤ በዶሮ እርባታና በዓሣ ልማት ላይ በትኩረት መስራት በመቻሉ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

የሌማት ቱሩፋት ፕሮግራም በ2015 ዓ.ም እንደ ሃገር ከተጀመረ በኋላ በክልል ደረጃ በ22 ወረዳዎች 669 መንደሮች 38 ሺህ አርሶ አደሮች በወተት ልማት ፓኬጅ ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የእንስሳትን ዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ በቀን ሲያገኝ የነበረው ወተት ከአንድ ሊትር ያነሰ የነበረ ሲሆን ዝርያቸው በተሻሻሉ ከብቶች በቀን 40 ሊትር ወተት እያገኙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ሶስት የወተት ዩኒየኖችን እና 14 የወተት ህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት ለ225 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ሰባት ማህበራት ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንደስትሪ ፓርክ ወተት እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ክልሉ አሁን ላይ በየሁለት ቀኑ አስከ ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሊትር ወተት ወደ አዲስ አበባ እየላከ ይገኛል ያሉት አቶ ተክሌ፤ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ህብረተሰብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በዚህም አርሶ አደሮቹ ከራሳቸው አልፈው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የዶሮ ልማት በ37 ወረዳዎች፣ የንብ ሃብት ልማት በ17 ወረዳዎች፣ የሐር ልማት በ10 ወረዳዎች፣ የበግ ልማት በ14 ወረዳዎች፣ የዓሣና የሥጋ ልማት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ የሌማት ትሩፋት መንደሮችን በማደረጃት በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው፤ መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ምርታማነትን በቀጣይነት ማሳደግ ከተቻለ በምግብ ራስን የመቻል እቅዱ የሚሳካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኋላቀር የአመራረትና የአሰራር ዘይቤን ከመቀየር ጀምሮ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ወደልማቱ በማስገባት በዘርፎቹ ስኬት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ የቤተሰብ ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አውስተው፤ እየተተገበረ ለሚገኘው ሃገራዊ የሌማት ቱሩፋት እቅድ ስኬት ክልሉ የድርሻውን እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡