በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ መሃል የሚገኘው የአስፓልት መንገድ በመበላሸቱ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ

በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ መሃል የሚገኘው የአስፓልት መንገድ በመበላሸቱ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ

የመንገዱ መበላሸት ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው ላይም ተፅዕኖ መፍጠሩን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጣቢያችን ካነጋገራቸው የአካባቢ ነዋሪዎቹ መካከል አቶ አበበ አደቆ፣ አቶ ተሾመ ታደሰ፣ አቶ ሰለሞን ተስፋዬና ወ/ሮ ዘለቃሽ ወዳጆ በስፍራው ረጅም ዓመታትን በኖሩበት ጊዜያት ውስጥ በአካባቢው ምንም የመሬት ናዳም ሆነ የመንገድ ችግር ሳይገጥማቸው መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከ2005 ዓ/ም የአስፓልት መንገድ ከተሰራ በኋላ የመንገድ መሰነጣጠቅ፣ የፈሳሽ መውረጃዎች መሰባበርና በአቅራቢያው የሚገኘው መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ተቋማት መፍረሱን አስረድተዋል፡፡

ከመንገዱ መበላሸት የተነሳ በተለያዩ ሥራዎች የሚተዳዳሩ ወጣቶች ንብረታቸው መውደሙን፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት መቋረጥ ለከፋ ችግር እንዳጋለጣቸውም ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም ለረጅም ዓመታት ከኖሩበት፣ ቤት ንብረታቸው ፈርሶ ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት አልተቻለም።

አሁንም የችግሩ ስፋት እየጨመረ ስለሆነ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ችግሩን አስመልክቶ ጣቢያችን ጉዳዩ የሚመለከተውን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጅማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ የእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ባለመሣካቱ የዚሁ ዜና አካል ልናደርገው አልቻልንም።

ምላሻቸውን እንዳገኘን የምናሣውቅ መሆናችንን ከወዲሁ እንገልፃለን።

ዘጋቢ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን