የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት በክልሉ የመልማት አቅም ብቻ ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ

የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት በክልሉ የመልማት አቅም ብቻ ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ

የቢሮው ከፍተኛ አመራሮችና ዘርፉን የሚደግፉ ባለድርሻ አካልት በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ በካሌብ እያሱ እርሻ ሥራዎች የምርጥ ዘር ብዜት ማሳን ጎብኝተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በእያንዳንዱ እርሻ ወቅት ከ100 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ የተመላከተ ሲሆን፥ ይህንን ፍላጎት ለመሸፈን ከተለያዩ አካባቢዎች ምርጥ ዘር ሲቀርብ መቆየቱ ተጠቁሟል።

የሚቀርበው ምርጥ ዘር ከጥራትና በወቅቱ ከመድረስ ረገድ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርና ግበዓት ዘርፍ ኋላፊ አቶ ግዳልክ አልክም፥ ችግሩን ለመቅረፍ የየዞኖችን የመልማት አቅም ለይቶ ምርጥ ዘር ብዜት ለማካሄድ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በያዝነው አመት ከ2500 ሄክታር በላይ ማሳ 50 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማግኘት እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፥ እስከ አሁን 2100 ሄክታር መልማቱን ተናግረዋል።

በጎፋ ዞን በስንዴ፣ በበቆሎና በማሾ ከ150 ሄክታር በላይ ማሣ የለማ ሲሆን የምርት አያያዙም የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ግብርና ግበዓት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ትቄ ትላንቴ፥ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ አምራቹ የእርሻ አቅም ባሻገር ከፍተኛ የስነ አዕምሮ ዝግጅት የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጸው በባለሙያ ድጋፍ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረተው ምርጥዘር የሳይንሳዊ ሂደቱን የተከተለ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን አልፎ ጥቅም ላይ የሚውል ነው ብለዋል።

በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ ዶጫ ዳምባላ ቀበሌ የሚገኘው የምርጥ ዘር ብዜት እርሻ ባለቤት ወጣት ካሌብ ኢያሱ በእርሻ ጣቢያው 45 ሄክታር የማሾና 50 ሄክታር የበቆሎ ምርጥ ዘር እየተመረተ እንደሆነ ተናግረው በተለይም የማሾ ምርጥ ዘር ማግኘት በአርሶ አደሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በእርሻው ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ኢንቬስተሮችም ፈታኝ እንደነበር ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን አስተዳደርን በመወከል በሥፍራው የተገኙት የዞኑ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኋላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ በሁለቱም ወረዳዎች የእተከናወነ የሚገኘው የምርጥ ዘር ብዜት በተለይም የማሾ ሠብል አርሷደሩን በአጭር ግዜ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚያደርገው መሆኑን አብራርተዋል።

በጎፋ ዞን ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የምርጥ ዘር እጥረት እንደነበር ያነሱት የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ የዞኑ የተጀመረው ሥራ ችግሩን ከመቅረፍ በዘለለ የአካባቢው አርሷደር የተሻለ ልምድ የቀመረበት መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት የተጀመረውን የምርጥ ዘር ብዜት ጥሩ ተሞክሮ ያገኙበትና ለልጆቻቸው የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያ