ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን
በጋዜጣው ሪፖርተር
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሃገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በዓለም-አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ሃገራችን ከምትታወቅበት ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎቿ መካከል ቡና ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ የሚታወቅና በእጅጉ የሚወደድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘው የኢትዮጵያ ቡና ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆንም ይታወቃል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከመሆኑም በላይ ተፈላጊነቱ በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል፡፡
በዚህም ቡና አብቃይ በሆኑ የሃገሪቱ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ካለፈው ጊዜ በተሻለ ደረጃ እያመረቱ የሚገኙ ሲሆን በምርቱም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ቡና በግብርና ሚኒስቴር እንደ አንድ ዘርፍ ገብቶ ተደብቆ ቆይቷል ሲሉ ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን በአሁን ወቅት ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያለው ቡና በተሰጠው ትኩረት ልክ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ለዚህም በዘርፉ የተሰሩና አሁንም በስራ ላይ ያሉ በርካታ ተግባራት ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ በመቀጠል ዘርፉን ማሳደግና ሃገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተሰራ ያለው ሥራ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በክልሉ ለዘንድሮ ቡና ልማት ሥራ የሚውል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ በቀጣይ ሚያዚያ ወር ላይ የሚተከሉ ከ31 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከሰሞኑ ዲላ ላይ ባደረገው የ6 ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በተያዘው ዓመት ከ15 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በአዲስና በእድሳት የቡና ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ደረጃውን የጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለቡና ጥራትና ምርታማነት ሚናው የጎላ በመሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ላይ ለአርሶ አደሩ ተግባር ተኮር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል። በዚህም በተያዘው ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስከሁን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በተጨማሪ ለቀጣይ ሚያዝያ ወር የሚተከሉ የተሻሻለ የቡና ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል። ችግኞቹ በመንግስትና በማህበራት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እንዲሁም በአርሶ አደሮች ጓሮ የተዘጋጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
አቶ አማኑኤል አያዘውም በክልሉ ባለፉት ዓመታት የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተደረገ ጥረት በአሁኑ ወቅት በቡና የተሸፈነ መሬት 228 ሺህ ሄክታር መድረሱን ገልጸው፣ ሽፋኑን የማሳዳግ ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በበኩላቸው፤ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ የኩታ ገጠም የቡና እድሳት እየተከናወነ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ ያረጀ ቡናን በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች ለመተካት የነቀላና ጉንደላ ስራ በንቅናቄ እየተከናወነ ነው፡፡ በተለይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ያረጀ ቡና የማንሳት ስራን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቡና እድሳት የሚስተዋለውን የአመለካከትና የግብዓት በተለይም የተፈጥሮ ማዳበሪያና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች አቅርቦት በማመቻቸት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርቡ መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።
በክልሉ ቡናን በስፋት ከሚያመርቱ አካባቢዎች መካከል የጌዴኦ ዞን አንዱ ነው። በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የቡና እድሳት ስራዎች ውጤት ማምጣቱን የገለጹት የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ጫካ ናቸው፡፡
በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ4 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች ለመተካት ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም 342 ሄክታር የቡና ማሳ በኩታ ገጠም እየለማ ነው፡፡
በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ አልማሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት እሳቸውን ጨምሮ 54 አርሶአደሮች ከ27 ሄክታር መሬት ያረጀ ቡናን በማንሳት የተሻሸሉ ዝሪያዎችን በኩታ ገጠም ማልማታቸውን አንስተዋል፡፡
አርሶአደሩ አክለውም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀምና የአረም ቁጥጥር ጨምሮ የተለያዩ እንክብካቤዎችን በማከናወን ቡናው በአጭር ጊዜ ምርት እንዲሰጥ እየሰራን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዘንድሮም ተጨማሪ በ36 ሄክታር መሬት ላይ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን በብዛትና ጥራት ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ ክልሉ በግማሽ ዓመቱ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የበኩሉን ሚና መጫውቱ ተዘግቧል፡፡
ባለስልጣኑ የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በዲላ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሪክተር አቶ አማኑኤል ብሩ እንዳሉት፤ በክልሉ በግማሽ ዓመት ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡
በክልሉ ከ134 ሺህ ቶን በላይ እሸት ቡና ተሰብስቦ የደረቅ ቡና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምርት ዘመኑ ተሰብስቦ የተከማቸ ቡናን በቀጣይ ሶስት ወራት አሟጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ህገ-ወጥ የቡና ዝውውርን ከመቆጣጠር በተጓዳኝ አቅራቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ በየደረጃው ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑ አንሰተዋል፡፡
በዞኑ በግማሽ አመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ጫካ ናቸው፡፡ በምርት ዘመኑም ከ200 በላይ ቡና አምራቾች ከ17 ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ቡና ማዘጋጀት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ይህንንም በቀጣይ ወራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የተሰሩ ሥራዎች የቡና መገኛ እንደሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ቡና ለማምረት ሰፊ እምቅ አቅም ቢኖራትም እስካሁን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ አርሶ አደሩም ሆነ ሃገሪቱ ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደለም የሚለውን ሃሳብ መቀየር እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በመሆኑም እንደ ችግር የሚነሱ በዘመናዊ መንገድ አለማምረት እና የገበያ ሰንሰለቱ ረዥም መሆን እና እሴት መጨመር አለመቻል በመቅረፍ ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም መሥራት ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል እያልን የዛሬን አበቃን፡፡ ሠላም፡፡
More Stories
“ሚሻላ”
ሀገራዊ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት