“ሚሻላ”
በጋዜጣው ሪፖርተር
ባሕል ለአንድ ማህበረሰብ ማንነቱን የሚገልፅበት እሴት ነው፡፡ ህዝቡ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶቹን÷ በአጠቃላይ የዕድገት ደረጃው በፈቀደ መልኩ የጋራ መግባባትና ምልክት ሆኖት የሚጠቀምበት÷ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የሚሄድ ሀብቱ ነው፡፡
የሀላባ ብሔረሰብ የራሱ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ የአስተዳደር ስርዓት (ሴራ) ያለውና ከጥንት አያቶቹ ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፡- የሚኮራበት ባህል ያለው ነው፡፡
ከእነዚህ መልካም እሴቶች መካካል የሀላባ ሕዝብ የሚመራበት ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት /ሴራ/ አንዱ ነው፡፡ በውስጡ በርካታ ዝርዝር÷ ንዑስ ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡ የሀላባ ሴራ ከንዑሳን የሴራ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሀላባ ብሔረሰብ “ሚሻላ ሴራ” (የመረዳዳት ሥርዓት) ይጠቀሳል፡፡
“ሚሻላ”፡- ከነዚህ ንዑስ የሴራው ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ መነሻ ምክንያቶች የማህበረሰቡ አባላት የሚደርሱባቸውን ችግሮች በተዋረድ ካለው የማህበረሰብ አካላት ቡድኖች ጋር እርስ በእርስ በመቀናጀት ከችግሮቻቸው ለመውጣት የሚፈፅሙት የእርዳታ ባህል ነው፡፡
መረዳዳት ለሰው ልጅ ጠቃሚ ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሰውን ስንረዳ ውስጣችን ሰላም ያገኛል። መርዳት ያለብንን ሰው መርዳት ለኛም ለህብረተሰቡም ጠቃሚ ነው፡፡
በኑሮ ሂደት የሰው ልጅ ከፍና ዝቅ ማለቱ አይቀርም፡፡ ከፍ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ዝቅ ያለውን ክፍል መርዳት ፣መደገፍ፣ ማቋቋምና አለሁ ከጐንህ ማለት ይጠበቅበታል፡፡
“ሚሻላ ሴራ” (የመረዳዳት ሥርዓት)፡- በብሔረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት ህዝቡ በሰላምና በመተሳሰብ እንዲኖር የማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡
በባህል ስርዓቱ (በሴራው) ድንጋጌ መሰረት ባህላዊ ሥርዓቶቹ ለምን እና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸውና በማን ይተገበራሉ የሚል ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ የተቀመጠላቸው ናቸው፡፡
“ሚሻላ ሴራ” (የመረዳዳት ስርዓት) የሚፈፀመው በማህበረሰቡ ዘንድ ባሉ በተለያዩ የእርከን ደረጃዎች ነው፡፡ በዋነኛነትም በቤተሰብ አባላት፣ በንዑሳን ጎሳ አባላትና በጎሳ አባላት ሲሆን በጠቅላላ በሀላባ “ኦገቴ” (በብሔረሰቡ ሸንጎ ጉባኤ) ደረጃ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው የዳኝነት አካላት ይመራል፡፡ የዳኝነት አካሉ የቀረቡለትን አቤቱታዎች ግራ ቀኝ ተመልክቶና የችግሩን ቅለትና ክብደት መርምሮ በሚሰጠው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ጉዳዩ የሚፈፀም ይሆናል፡፡
ይህ መልካም እሴት “ሚሻላ ሴራ” (የመረዳዳት ሥርዓት) በተለያዩ ምክንያቶች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ከፍተኛ የጤና እክል የገጠማቸውን፣በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖቹን ፣ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ክስተቶች ቤት ንብረታቸውን በእሳት አደጋ ያጡ ፣ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ይረዱበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ÷ ለአቅመ ደካሞችና በጤና ችግር ምክንያት ስራ መስራት ላልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የእርሻ ሥራቸውን ከማረስ እስከ መሰብሰብና መውቃት ደረጃ የሚደርስ እርዳታ ይደረግላቸዋል። የመጠለያ ችግር ለገጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎችም ቤት ሰርቶ ከነቁሳቁሱ የማስረከብ ተግባር ይፈፀማል፡፡ ለህፃናት አልባሳትና ምግቦችን ገዝቶ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም የጤና እክል የገጠማቸውን ያሳክማል። በዝርፍያ ምክንያት ንብረታቸውን ያጡትን ይደግፋል፡፡
በሴራው አካሄድና ሥርዓት የማህበረሰቡ ሚና የአንድ ወቅት እርዳታ ብቻ ሳይሆን ውጤቱ በተጨባጭ መሬት ወርዶ እስኪታይ ድረስ በየ 6 ወሩ ክትትል ይደረጋል፡፡
መከራና ችግር ተፈራርቀውባቸው የመኖር ተስፋ የጨለመባቸውን ዜጎች እንባ ያበሰ፣ ከሰው እኩል ብርሀን እንዲያገኙና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሻገሩ ያስቻላቸው ጠብቀው ያቆዩት ማህበራዊ እሴታቸው ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች ማሕበራዊ ፍትህን ለማንገስና የሀገራችንን እድገት ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
የሀላባ ማህበረሰብ ነባር እሴት የሆነውን የመረዳዳት ባህል ከሚሰማው ሰብአዊ ስሜቱ ተነስቶ÷ ለወገኑ ጉልበቱን፣ ገንዘቡን ፣ ጊዜውን ሰውቶ የሚሰጥበት ድንቅ መልካም እሴቱ ጎልብቶ ለሀላባ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ህዝቦች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይ ጎዳና ላይ የወጡትን መርዳት የሚያስችል በመሆኑ ከትውለድ ወደ ትውልድ ጠብቆ ማስተላለፍ ያስፈልጋል÷ ሌሎችም መሰል እሴቶቻቸውን ሊጠቀምባቸው ይገባል እንላለን፡፡
More Stories
ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን
ሀገራዊ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት