የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት
በአስፋው አማረ
ሀገራችን የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ እንደመሆኗ መጠን የበርካታ ውብ ቱባ ባህሎች ባለቤትም ናት፡፡ ከነዚህ ባህሎች መካከል አንዱ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ ነው፡፡
በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ ብንጓዝ የማይጠገብ ውብ የሆነ ባህላዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓት የሚገኝባት ሀገር ናት ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡
የጋብቻ ሥነ-ስርዓት ወይም ሠርግ ሠዎች በጋብቻ ለመተሳሰር ቃል የሚገቡበት ዝግጅት ነው። ይህ ደግሞ ከቦታ ቦታ የሚለያይና የሚከወን ነው፡፡
በዛሬው የባህል ዓምዳችን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነውን የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ ጋብቻ ሥነ ስርዓት ልናስቃኛችሁ ወደናል መልካም ንባብ፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የቀቤና ብሔረሰብ፤ ካሉት በርካታ ሀገር በቀል ባህሎች አንዱ የሆነው ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ተጠቃሽ ነው፡፡
በቀቤና ብሔረሰብ ባህል መሰረት ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ወጣቶች ለጋብቻ ብቁ መሆናቸውን የሚገልፁባቸው የተለያዩ መንገዶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዲት ልጃ አገረድ ለአቅመ ሔዋን መድረሷን ለማመልከት “ናኑት” ወይም “ጨራራ” የተሰኘውን ባህላዊ የፀጉር አሰራር ትሠራለች፡፡
የግል ቤትና ንብረት እንዲኖረው መፈለግና ይህም እንዲሟላለት ለወላጆቹ ጥያቄ ማቅረብ ደግሞ ወንዱ ልጅ ለአቅመ አዳም መድረሱን የሚገልፅበት መንገድ ነው፡፡
በቀቤና ብሔረሰብ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ፤ እነሱም፡-
አንደኛው “አጩቁ” የሚባል ሲሆን ይህ አይነቱ ጋብቻ በወላጆች መልካም ፈቃደኝነት የሚፈፀም ነው፡፡ ሁለተኛው “ጣጦቄን አዩ” የሚባል ሲሆን ድንገት የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ “ረገዑ” የሚሰኝ ሲሆን ይህ የጋብቻ አይነት የውርስ ጋብቻ ነው፡፡ አራተኛ “ዶረቱት” ይባላል፡፡ ይህ ጋብቻ ደግሞ “የምትክ ጋብቻ” ነው። አምስተኛ “ወጌቱታ” የፈት ጋብቻ ሲሆን ስድስተኛው “ሙሪታ ባዬን አሱ” የሚባል ሲሆን የሴቷ ወላጆች ለልጃቸው የመረጡላትን ወንድ ጠርተው የሚድሩበት ጋብቻ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በብሔረሰቡ ዘንድ በይበልጥ የሚዘወተሩት “ኡጩቁ” አና “ጣጧቄን አዩን” የተሰኙት ሁለት የጋብቻ ዓይነቶች ናቸው፡፡ የ “አጩቁ” ጋብቻ በወላጆች መልካም ፍቃድ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ሲሆን በዚህ የጋብቻ ሂደት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው የወንዱ ወላጅ አባት አንደሆነ ይነገራል፡፡
አባት ለልጁ የወደፊት ሚስት ትሆንለት ዘንድ ወደመረጣት ልጃገረድ ቤተሰብ አብረውት የሚሄዱትን ሽማግሌዎችን የሚመርጠው ራሱ ነው፡፡ ከመረጣቸው ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ከልጅቷ ወላጅ አባት ቤት እንደደረሱ “ልጅህን ለልጄ ስጠኝ” የሚል የጋብቻ ጥያቄ የልጁ አባት ለልጅቷ አባት ያቀርባል፡፡
በቀጥታ አይሁን እንጂ ለሽማግሌዎች አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ በተዘዋዋሪ የሚሰጥባቸው ሲሆን በብሔረሰቡ የተለመዱ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ ይህም አጭር ወይም ረዥም ቀጠሮ መስጠት ዋነኛው በብሔረሰቡ ዘንድ የተለመደ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የልጅቷ አባት በጉዳዩ ላይ ተማክሮ መልስ ለመስጠት ለሽማግሌዎቹ አጭር (ከሁለት ሣምንት ያልበለጠ) ቀጠሮ ከሰጠ ጋብቻውን የፈቀደ ወይም በጋብቻው የተስማማ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ረዥም ማለትም እስከ ሦስት ወር የሚቆይ ቀጠሮ ከሰጠ ደግሞ ጋብቻውን ያልፈቀደ መሆኑ ይገመታል፡፡
ከቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በብሔረሰቡ ዘንድ አንዲት የቀቤና ልጃገረድ “ኒካ” ከታሠረላት በኋላ ሌላ ወንድ አይጠጋትም፣ ትከበራለች፤ እንደዚሁም ወንዶች በሙሉ አይናቸው በድፍረት አያይዋትም፡፡
ሌላው በብሔረሰቡ ዘንድ የሚዘወተረው የጋብቻ ዓይነት “ጣጦቄን አዩ” የሚሰኘው የድንገቴ ጋብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጋብቻ አንዳንዴ “ተጠምጥሞ ገባ” በሚል ስያሜውም ይታወቃል፡፡
አግቢው ወጣት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሣይታሰብ በድንገት ከወደዳት ልጅ ወላጆች ቤት ገብቶ “አልወጣም” በማለቱ ምክንያት የሚፈፀም ጋብቻ በመሆኑ ነው “ተጠምጥሞ ገባ” የሚል ስያሜ የተሰጠው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጋብቻ ለልጅቱ ወላጆች ዱብዳ (ድንገተኛ) ይሁን አንጂ ለተጋቢዎቹ ግን ድንገተኛ አይደለም፡፡
ሁለቱ ተጋቢዎች (እጮኞች) ቀደም ብለው በሚስጢር የተስማሙበት ጉዳይ ቢሆንም ፤ በዚህ ዓይነት ከነጓደኞቹ የገባው ወጣት ከየት አንደመጣ? ምን እንደሚፈልግ? ቤታቸውንም ለቆ እንዲወጣ በልጅቷ ወላጆች ቢጠየቅም አይወጣም ፤ ቤታቸውን የሙጥኝ ይላል፡፡
ከልጅቱ ወላጆች የይሁንታን ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከገባበት ቤት ንቅንቅ አይልም፡፡ ልጅቷም ፍቅረኛዋ “ተጠምጥሞ መግባቱን” ስታውቅ ወዲያው በቅርብ ጓደኞቹ ትታጀባለች፣ አፍታም ሣይቆዩ የልጁ ወላጆች ልጃቸው ካለበት ከልጅቷ ወላጆች ቤት ሽማግሌ ይልካሉ፡፡
በዚህ መልኩ ጉዳዩ በሽምግልና ያልቅና ልጅቷ ትሞሸራለች፡፡ በተሞሸረች በአንድ አሊያም ሁለት ቀናት ውስጥም የጋብቻው ሥነ ስርዓት ይፈፀማል፡፡ የጥሎሽ ሥርዓትም በዚሁ ዕለት ይከናወናል፡፡
More Stories
ችግር ፈቺ የሆኑ አለም አቀፍ የምርምር ጽሁፎች አሳትሜያለሁ – ወጣት ሱራፌል ሙስጠፋ
የክልሉ ስኬት ሌላው ማሳያ
ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን