ሀገራዊ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል
በቤተልሔም አበበ
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ የህዝቡን አቅምና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ አተገባበር ላይ ከወራት በፊት የነዳጅ ሪፎርም አፈጻጸም እና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
በመግለጫውም በመንግስት ተነድፎ ተግባራዊ የሚደረገው የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ ሁለት መነሻ ምክንያቶች እንዳሉትም ተጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያው የዓለም የነዳጅ ዋጋ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍ እና ዝቅ የሚሉበት ሁኔታ መፈጠር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይም የውጪ ምንዛሬ ተመን ለውጥ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተከሰተው አለመረጋጋት እና ተያያዥ ምክንያቶች መነሻ ከዚህ ቀደም ሰባ ሁለት የነበረው አሁን ላይ ከሰማንያ ዶላር ከፍ ማለቱ እና አለመረጋጋቱ በዚሁ ከቀጠለ የነዳጅ ዋጋው ሊጨምር እንደሚችል በመግለጫው ተነስቷል፡፡
አዲሱ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ በተጠቀሱት ምክንያቶች መነሻ ተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ጥቅል ድጎማ እንዲደረግበት እና አብዛኛውን ሸክም በተለይም ነጭ ናፍጣ ኪሮሲን ላይ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ጭማሪ ልዩነትን መንግስት ይደጉማል። ዝቅተኛውንና ሃያ በመቶ የሚሆነውን ደግሞ በስትራቴጂው መሰረት ተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል እንዲከፍል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ በቤንዚል እና በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ የሰባ አምስት በመቶ በመንግስት ድጎማ የሚደረግ ሲሆን ዝቅተኛውን ሃያ አምስት በመቶ የሚሆነውን ተጠቃሚው እንዲሸፍን የማድረግ ስትራቴጂ እንዳለም ተገልጿል፡፡
ይህ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ እና በነዳጅ አምራች ሀገራት መካከል ያለው አለመረጋጋት በዚሁ ከቀጠለ የነዳጅ ውጤቶች ፣ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ግንባታ ስትራቴጂው ለአንድ አመት ሊዘልቅ እንደሚችል የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በነበረው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
ምንም እንኳን ከነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር እንደ ዓለም ብሎም እንደ ሀገር የተከሰተ እንደሆነ ቢታመንም ኑሯቸው፣ የዕለት ገቢያቸውን እና መተዳደሪያቸውን ተሽከርካሪ ላይ አድርገው የሚመሩ ዜጎች እየደረሰባቸው ያለው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡
አቶ ብርሃኑ አብነት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ረጃጅም የተሸከርካሪ ሰልፎች ተርታ ተሰልፈው ነበር ያገኘናቸው ያለውን የነዳጅ ሁኔታ ተጽዕኖን ሲገልጹ ለሊት ስምንት ሰዓት ቢኒዚን ለመቅዳት ተሰልፈው ውለው አስራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ምንም አይነት አገልግሎት ሳያገኙ ማደያው በመዘጋቱ የእለት ጉርስ ለማግኘት መቸገራቸው እንዳማረራቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪው አስተያየት ከሆነ የኑሮ ሁኔታ ከባድ ፈተና ሆኖ ሳለ ልጆቻችንን ለመመገብ እና የቤት ኪራይ ከፍሎ ለመኖር የቢኒዚን ሁኔታ አስቸጋሪ ሁኔታን በመፍጠሩ መንግስት ችግሮቻችንን በትኩረት ተገንዝቦ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡
በከተማዋ በርካታ የነዳጅ ማደያ ጣቢዎች ቢኖሩም አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ሁለት እና ሶስት በመሆናቸው ከፍላጎት አንጻር እጥረት ስላለ በሁሉም የማደያ ጣቢያዎች ተደራሽ ሊሆን ይገባል ሲሉ ነዋሪው ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪያችን አቶ ወንድማገኝ አባተ በበኩሉ ቤኒዚን ለማግኘት ተሰልፈው ከቆዩ በኋላ ሙሉ እና ጎዶሎ ታርጋ ቁጥር ያላቸው ተብለው እንደገና ወደ ሌላ ማደያ እንደሚላኩና እዛም ሄደው ተሰልፈው ወረፋው ከፍተኛ በመሆኑ ሳይቀዱ ለእንግልት መዳረጉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነበትም ነው የገለጸው፡፡
የፈረቃ አመዳደብ በቴሌግራም መተግባሪያ አንዳንዴ አስራ አንድ ሰዓት ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ የመቀየሩ ሁኔታ ከተማው ላይ ካለው ከተሽከርካሪ ብዛት የተነሳ በሚኖረው መጨናነቅ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ተወስዶ አመዳደቡ ወጥ ሊሆን እንደሚገባ ነው አቶ ወንድማገኝ የተናገረው ፡፡
በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ስራዎች ቀድመው ባለመሰራታቸው የቢኒዚን ሰልፎች ከተጀመሩ በኋላ የመንግስት እና የግል ሞተር ሳይክሎች ተብሎ ልየታ የሚደረግበት አግባብ ተገቢ እንዳልሆነ አንስቶ በዚህ አስቸጋሪ ውጣ ውረድ በተሞላበት ሁኔታ ኑሮን ለማሻሻል እያቃተን ስለመጣ መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል ሲል ወጣቱ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከስርጭት ባሻገር ትልቁ ችግር ማደያዎች ላይ የሚሰጥ ምደባ በመሆኑ ሁሉም ጋር ተደራሽ በማድረግ የሚመለከተው አካል ሊሰራ እንደሚገባ ያሳሰቡት የኪዩት አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ኢያሱ ለጬቦ፥ ከችግሩ ስፋት የተነሳ ከጥቁር ገበያ እንድንገዛ እየተገደድን ነው ብለዋል፡፡
ችግሩ ተያያዥ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ነዳጅ ተጠቃሚ እና ከተማዋ ሰላማዊ በመሆኑ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመመጣጠን መፈጠሩን የተናገሩት የታፍ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ካሱ ናቸው፡፡ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ያስቀመጠው የአሰራር ስርዓትን መነሻ በማድረግ የሚመጣውን ነዳጅ በተገቢ ሁኔታ ለህብረተሰቡ የማዳረስ ስራ እየተሰራ እንዳለም አክለው ገልጻዋል፡፡
ከፖሊስ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር አብሮ የመስራት ሁኔታ እንዳለም ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ክልል እየታየ ያለው የነዳጅ አቅርቦት ችግር መሆኑን ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን በጥናት መረጋገጡን የሲዳማ ክልል ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቡርቃ ቡቱላ ገልጸው በክልሉ ከሰባት ሺህ በላይ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ከሶስት ሺህ በላይ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ኪዩት መኪናዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት ፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ እነኚህን በአንድ ጊዜ ማሰለፍ ስለማይቻል ጎዶሎ፣ሙሉ ታርጋ እና የመንግስት እንዲሁም የግለሰብ በማድረግ የመከፋፈል ስራ ተሰርቶ ህብረተሰቡ በተገቢው እንዲገለገል የማድረግ አሰራር መኖሩን ነው ያነሱት ፡፡
በክልሉ ላሉ ተሸከርካሪዎች በወር 8.84 ሚሊየን ሌትር ነዳጅ የሚያስፈልግ ሲሆን ነገር ግን አሁን ላይ በመንግስት እየቀረበ ያለው በስድስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሌትር ብቻ እንደሆነና ችግሩም እንደ ሀገር የተከሰተ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አቅርቦቱ እንደ ክልል ጫና የፈጠረው ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የትራንስፖርት ፍስት አጎራባች ክልሎችን ጨምሮ በሰፊው የሚሳለጥ እንደሆነም አቶ ቡርቃ አስረድተዋል፡፡ ካለው የነዳጅ አቅርቦትጋር በተገናኘ ሁለት እና ሶስት ማደያዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ የተነሳው ሀሳብ ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ከሃያ በላይ ማደያዎች በነዳጅ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ቤኒዚል እስኪመጣ በመጠባበቅ ላይ ስለሚገኙ ያለውን ችግር ለመፍታት እንዲያስችል በተወሰኑ ማደያዎች ለህብረተሰቡ በተገቢው እንዲዳርስ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንዳለም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ከነዳጅ አቅርቦት ችግር ቀጥሎ ለህብረተሰቡ ማነቆ ሆኖ የዘለቀው ሰው ሰራሽ ችግር በህገወጥ ድርጊት በጥቁር ገበያ ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ህግ የማስከበር ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ነው አቶ ቡርቃ የገለጹት፡፡
ለዚህም ሲባል ዲጂታል መተግበሪያን የማይጠቀሙ ህገ ወጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ ስድስት ማደያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸው ወደ ስራ የተመለሱበት አግባብ መኖሩንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር ጭማሪ ነዳጅ እንዲደረግ ጥያቄ መቅረቡን አንስተው የአቅርቦት ችግር ቢኖር እንኳን ለዳማስ ፣ለከተማ አውቶቢስ እና ለባጃጅ ተሽከርከሪዎች ቅድሚያ የመስጠት ሁኔታ እንዳለም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት ነዳጅ ላይ የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ ችግር ለመፍታት በፓርላማ ውይይት ተደርጎ ተጠያቂነት ላይ ህጉ እንዲጠናከር እና ጫናው እንዲቀንስ የማድረግ ስራ በመስራት ለውጥ ይመጣልም ብለዋል። የአቅርቦት ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ህብረተሰቡ ችግሩን ተገንዝቦ በትዕግስት ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
More Stories
ለቡና ልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን
“ሚሻላ”
የቀቤና ብሔረሰብ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት