የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሠሰ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በየም ዞን ፎፋ ወረዳ በአዝጊ ዘምዳ ቀበሌ ተጀመረ

የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሠሰ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በየም ዞን ፎፋ ወረዳ በአዝጊ ዘምዳ ቀበሌ ተጀመረ

በወረዳው የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወን ከተጀመረ ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱም ተመላክቷል።

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የፎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋሽ ጀበል፤ በወረዳው የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወን ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ ቦታዎች አረንጓዴ መልበሳቸውን ተከትሎ የተለያዩ የውሃ አማራጮች በመፈጠራቸው ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በወረዳው በዛሬው ዕለት የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ ዘመቻ ለ15 ቀናት እንደሚቆይ የገለፁት አቶ ነጋሽ፤ ባጠረ ቀናት ሥራው አልቆ ወደ ሌሎች የግብርና ተግባራት መሻገር ያስፈልጋል ብለዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዮት ሲሳይ በበኩላቸው፤ የተቀናጀ ግብርና ሥራ ማለት ከተፋሰስ ባሻገር የመስኖ እና የበልግ ሥራዎችን አቀናጅቶ መስራት መሆኑን በመጥቀስ በተያዘው በጀት ዓመት በወረዳው በተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራ በ16 ንዑስ ተፋሠሶች 953 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ነው የጠቆሙት።

አቶ ፍቃዱ ያዲ በወረዳው የአዝጊ ዘምዳ ቀበሌ አስተዳዳሪ ሲሆኑ ህብረተሰቡ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ጠቃሚ መሆኑን ከተረዳ ወዲህ የማስተባበሩ ሥራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

የአዝጊ ዘምዳ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ዘገየ፤ የተፋሰስ ልማት ሥራ እየተለመደ በመምጣቱ ከአሁኑ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ አድርጓል ብለዋል።

ከተፋሠስ ልማት ሥራው ተሳታፊዎች መካከል ወ/ሮ መሠረት ደፋር፣ ወ/መስቀል ካሣዬ እና ወ/ሮ ውቢት ገ/ጻድቅ በሰጡት አስተያየት፤ በዘርፉ እስካሁን በተሰራው ሥራ በርካታ ለውጦች በመምጣታቸው ተግባሩን በደስታ እያከናወንን ነው ብለዋል።

ከተፋሰስ ልማት ስራው ጎን ለጎንም ሌሎች የግብርና ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ እስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን