በከተማው የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማት ዕጥረት በመቅረፍ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በምዕራብ ኦሞ ዞን የባቹማ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

በከተማው የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማት ዕጥረት በመቅረፍ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በምዕራብ ኦሞ ዞን የባቹማ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

የከተማ ነዋሪዎችም የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ልማት አጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ቡጳይ፤ ከተማው በከተማ አስተዳደር የተዋቀረው ለሕዝቡ ቅርብ በመሆን ሕዝብን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ከተማው በከተማ አስተዳደር ከተዋቀረ 4 ዓመት የሆነው የባቹማ ከተማ ሰፊ የመሠረተ ልማት ችግር ስላለበት ይህንን ለመቅረፍ የከተማውን ማህበረሰብ፣ አጎራባች ወረዳዎችንና አልሚ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ሰፊ ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ከንቲባው።

በ12 ሚሊየን ብር በዋን ዋሽ ፕሮጀክት የተጀመረ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ መኖሩን፣ በከተማው በቅርብ ጊዜ በአምስት አቅጣጫ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ተካሂዶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን እንዲሁም ሌሎች በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዳሉም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ መነሻ በማድረግ በከተማው የመንገድ መብራት ለመዘርጋት 8.8 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት ከከተማውና ከአጎራባች ወረዳዎች እየመጡ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ አልሚ ባለሀብቶችና የመንግስት ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የሀገር ሽማግሌና በንግድ ስራ የሚተዳደሩ አቶ ባደገ ተስፋዬ፣ የሀይማኖት አባት አቶ ኮራዬ ሌማች፣ ወጣት ጽዮን አለማየሁና ወጣት አብርሃም ታደሰ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት ለከተሞች ዕድገት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ዕውን ለማድረግ ቃልን በተግባር በመግለጽ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ንግድና ባዛር ላይ በመሳተፍ ለገቢው ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን