የሆሳዕና ከተማ የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለሌሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መብቃታቸውን ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ጥር 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሆሳዕና ከተማ የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች በፕሮጀክቱ ከታቀፉ ወዲህ በጽዳትና ውበት፣ አረንጓዴ አሻራና በተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመሰማራት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለሌሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት አማካኝነት ከተረጂነት ወደ ምርታማነትና ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የተሸጋገሩ የመጀመሪያ ዙር ተጠቃሚዎች ምረቃና የአዲስ ጀማሪዎች ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ጨምር ሀይሌ፤ መንግስት በከተሞች ፈጣን ዕድገት ምክንያት የሚፈጠረውን ሥራ አጥነትንና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ በመቅረጽ ወደ ተግባር ከገባ ወዲህ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ በነበሩ ዜጎች ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አንስተዋል።
መንግስት የዜጎች ኑሮ በዘላቂነት እንዲሻሻል የነደፈው ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ግብ የሚመታው ተጠቃሚዎቹ ለመለወጥ የሚያደርጉት ቁርጠኛ ትጋት እንደሆነ የገለጹት ሀላፊው፤ የባለድርሻ ተቋማት ድጋፍና ክትትልም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አመላክተዋል።
የሀድያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ተሾመ አነሞ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦሥት ዓመታት በፕሮጀክቱ የታቀፉ 10 ሺ የሚጠጉ ዜጎች በጽዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና መሠረተ ልማት ላይ ተሰማርተው በኑሮአቸውና በከተማው ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻላቸው በነዋሪው ላይ መነሳሳት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
በአዲስ መልክ በፕሮጀክቱ የታቀፉ የከተማው ነዋሪዎች የተሰጣቸውን ዕድል በመጠቀም ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ አሳስበዋል።
አስተያየት የሰጡት አንዳንድ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ በፕሮግራሙ ከመታቀፈቸው በፊት የሰው እጅ በማየት ሲተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለሌሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱም ላለፉት ሦስት ዓመታት በፕሮጀክቱ ታቅፈው በመጠቀም ኑሯቸውን እንዳሻሻሉ በመገመት የተመረቁ ተጠቃሚዎች ከዕለቱ የክብር እንግዳ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል።
ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችኝ
More Stories
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ማሻሻልና ማዘመን እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ጥራት ያለው ኮረሪማ ለገበያ ለማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትኩረት መደረጉን የአሪ ዞን ቡናና ቅመማቅመም ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ