በንፅሁ መጠጥ ውሃ እጥረት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን የስልጢ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

በንፅሁ መጠጥ ውሃ እጥረት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን የስልጢ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ጥር 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በንፅሁ መጠጥ ውሃ እጥረት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን በስልጤ ዞን አንዳንድ የስልጢ ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ጋር በተያያዘ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለሆሳዕና ጣቢያችን ቅሬታቸውን ያቀረቡ በስልጤ ዞን የዳኔቾ ሙከሬ ቀበሌ ነዋሪዎች፤ በአካባቢው ለረጅም አመታት የቆየ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር መኖሩን ነው የገለፁት።

በዚህም ሳቢያ በአካባቢያቸው ያለውን ወራጅ ወንዝ እንደሚጠቀሙ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በጋ በመጣ ቁጥር ወንዙ እየደረቀ ስለሚሄድ ችግሩ እንደሚከፋ ገልፀዋል።

በአሁን ወቅት ከዚህ ወንዝ በቀን ለመቅዳት የውሃው ንፅህና በእንሰሳት ስለሚበከል የተሻለ የተጣራ ውሃ ለመቅዳት በሌሊት ከዱር እንስሳት ጋር መጋፋት ግዴታቸው መሆኑን አንስተዋል።

ተማሪዎች በሌሊት ለውሃ ፍለጋ ስለሚሄዱ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ማህበረሰቡ ለተለያየ በሽታ እየተጋለጠ ነውም ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች ተገቢነት ያላቸው መሆኑን በመጠቆም በወረዳው ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን የስልጢ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙህዲን ከድር ገልፀዋል።

በበጀት አመቱ የተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችንና የግል ባለሀብቶችን በማስተባበር በወረዳው ባሉ ቀበሌያት አስር የእጅ ጉድጓድና አራት ምንጭ በማስገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ይህም ካለው የውኃ አቅርቦት ችግር አንጻር በቂ ባለመሆኑ መካከለኛ የእጅ ጉድጓድ ቁፋሮ የተደረገ ሲሆን አብዛኛው ስራው ስላለቀ በቅርብ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይውላል ነው ያሉት አቶ ሙህዲን።

በተመሳሳይም በወረዳው ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር ያለበትን የሰደበረንጎ ቀበሌ ችግር ለመፍታትም ከአጎራባች ቀበሌያት ውሃ በማዳረስ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተሰርቷል ያሉት ኃላፊው አሁንም የህዝቡን የውሃ ችግር መቅራፍ ባለመቻሉ ቀጣይ የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን