“አትችይም የሚለውን አመለካከት አሸንፌያለሁ”
የ2017 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀዋሳ ከተማ መከበሩ የሚታወስ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልእክት፡- ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞችን ቀን በዓል ስናከብር በሀገራችን እና በመላው አለም አካል ጉዳተኞች ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ ያስመዘገቡትን አስደናቂ ስኬቶች በኩራት ማንሳት ይገባናል ብለዋል፡፡
ይህን ያሉት አካል ጉዳተኞች ለማህበረሰቡ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ እውቅና መስጠትም ተገቢ በመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥም ተግባራቸው የገዘፈ አካል ጉዳተኞች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው አይቻልም ሳይሆን ይቻላል የሚል አመለካከትን የሰነቁ በርካቶች ናቸው፡፡
ተግዳሮቶችን በጽናት አልፈው ወደ አመራርነት ከመጡት መካከል አንዷ ስለሆኑት ብርቱ ሴት በዛሬው የችያለሁ አምድ ለማቅረብ ወደድን፡፡ እችላለሁ የሚለውን መንፈስ አጎልብተው የወጡ ብርቅዬ እንስት አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ትልቁ ጉዳይ የቤተሰብ እገዛ ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ በቤተሰብ ትኩረት የተቸራቸው አካል ጉዳተኞች ወደፊት ያለመውጣት ምክንያት የላቸውም ሲሉም አበክረው ይናገራሉ፡፡ ማህበረሰቡ አትችልም ቢልም ቤተሰብ ትችላለች በማለቱ ለዛሬው ህይወታቸው መሰረት መጣሉን ያነሳሉ፡፡
ኮሚሽነር እርግበ ገብረ ሃዋሪያ ሐጎስ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከቱ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡
በአሜሪካ ኤምባሲ በሰብአዊ መብት ሪሶርስ አድቫይዘር፣ ዲስኤቢሊቲ አድቫይዘር፣ እና የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብት ጉዳዮችን በማማከር እና በሰው ኃይል አስተዳደር ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በግላቸውም ኮንሰልታንሲ በመፍጠር አካል ጉዳተኞችን የማማከር እና ኣካል ጉዳተኞች ማካተት ላይ የሚመለከቱ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች መብቶች ዙሪያ በሴቶች መብቶች ላይ ከሚሰሩ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ጋር ሰርተዋል፡፡ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ያለ ድርጅት ውስጥ በቦርድ አባልነትና በአመራርነት እንዳገለገሉም ነው የጠቆሙን፡፡ አሁንም በሴቶች መብቶች ዙሪያ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካ በኮምሽን ደረጃ የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች አረጋውያን መብቶች ወርኪነግ ግሩፕ በሚባል ድርጅት ውስጥ ኤክስፐርት አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መስራታቸውንም አክለዋል፡፡ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰራ እስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭ ፎር ሒዩማን ኢን ዘ ሆርኖፍ አፍሪካ በሚባል ድርጅት ውስጥ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቭሎፕመነት የሚባል በኣካል ጉዳተኞች ማካተት ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ በአስተባባሪነት አገልግለዋል፡፡
ኮሚሽነር እርግበ ገብረሃዋሪያ የተወለዱት በትግራይ ክልል እደጋ ሀሙስ በምትባል ከተማ ሲሆን እድገታቸው ደግሞ አዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ልደታ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ሲሆን የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በህግ፣ 2ኛ ዲግሪያቸውን (ማስተርሳቸውን) በሶሻል ወርክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡
ኮሚሽነር እርግበ ገብረሃዋሪያ ባለትዳር እና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው፡፡ አካል ጉዳት የገጠማቸው ከውልደት ጀምሮ በፖሊዮ ምክንያት ሁለት እግራቸው ላይ ጉዳት መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡ የእግር ድጋፍ እንዲሁም ክራንች ተጠቅመው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ለቤተሰቡ ከስድስት ወንድና ሴት ልጆች መሀል ሶስተኛ ልጅ ናቸው፡፡ “ቤተሰቦቼ በትምህርት መለወጥ እንደሚቻል የሚያምኑ ናቸው፡፡ ትልቅ ቦታ እንደምደርስ፣ በኃላፊነት ህዝብን እንደማገለግል ውስጤን እያነሳሱ ነው ያሳደጉኝ” ሲሉም ነው የተናገሩት። ያም ዛሬ ላይ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታ ላይ ሆነው ማህበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ አቅም እንደሆናቸው በመግለጽ፡፡
በሀገራችን አካል ጉዳተኞች ላይ ጫናው ከቤተሰብ እንደሚጀምር ስለመታዘባቸው ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም ለኣካል ጉዳተኞች ቤተሰብ መሰረት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ባለቤታቸው አካል ጉዳተኛ አለመሆናቸውን ይሁን እንጂ ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ንቃተ ህሊና ጥሩ በመሆኑ ሌላ አቅም እንደሆናቸውም ነው የገለጹት፡፡ “ወላጅ ቤተሰቦቼ ብሎም በትዳሬ ውስጥ በእኩልነት የምናምን ሰዎች ነን” በማለትም ነው የገለጹት። ባለቤታቸው የሚሰሩት በኣካል ጉዳተኞች ዙሪያ በመሆኑም ተመሳሳይ ዓላማን አንግበው ነው የሚሰሩት። እንደ መታደል ሆኖ ከቤተሰብ ጋር ተያይዞ የገጠማቸው ችግር የለም፡፡ የትዳር አጋራቸውም በአስተሳሰብ የተሻለ በመሆኑ አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡
ኮሚሽነር እርግበ አካል ጉዳተኞች ላይ ትልቅ ተግዳሮት ነው ብለው የሚያነሱት፡- በየትኛውም ዘርፍ ሙሉ ተሳታፊ ያለማድረግ፣ የተግባቦትና ተቋማዊ እንቅፋቶች ያሉ ሲሆን ማህበረሰቡም ለኣካል ጉዳተኞች ያለው ስር የሰደደ እንደ ተረጂ የማየት ችግር በሁለንተናዊ ዘርፍ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ተጭኗቸው እንደቆየ ነው የተናገሩት፡፡
“የቤተሰብ ድጋፍ ስለነበረኝ ተቋቁሜ አለፍኩት እንጂ እንደ ማህበረሰቡ አመለካከት ቢሆንማ ወድቄ በቀረሁ ነበር፡፡ ተግዳሮቱ ከንፈር ከመምጠጥ ይጀምራል፡፡ ከዛም የመቻል አቅም እያለኝ አትችይም ብሎ ይፈርጀኛል፡፡ እኔ ግን ከቤተሰብ ያዳበርኩት በራስ መተማመን አለ፡፡ ይህንንም በህይወቴ ስለገለጥኩት ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ላይ ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ለውጥ ስላለ አካል ጉዳተኞችም በህገ- መንግስቱ የተረጋገጡላቸውን መብቶች ማስጠበቅ አለባቸው፡፡”
አካል ጉዳተኛ በመሆንዎ ምን ትውስታ አለዎ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም፡- ተማሪ እያሉ ይደርስባቸው የነበረውን ገጠመኝ አብነት አድርገው ያነሳሉ፡፡ ይህም ተጽእኖ ይፈጥርባቸው እንደነበር በማስታወስ፡፡ እንደሚችሉ ሳይሆን እንደማይችሉ አድርጎ ማሰብ ቀዳሚ ተግዳሮት ነበር፡፡ ይህም ሁልጊዜ ራሳቸውን እንዲጠይቁ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ አልፎ አልፎም የስነ-ልቦና ተጽእኖም ይፈጥርባቸው ነበር፡፡
“ያዝኑልኛል የሚታዘንልኝ ሰው እንዳልሆንኩ ግን አውቅ ነበር፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ሰዎች ሲያዝኑልኝ፣ አንዳንድ ነገሮችን ስሰራ እንደ ብርቅ ነው የሚያዩኝ፡፡ ከተለየ ዓለም የመጣሁ ልዩ ፍጡር አድርገው ሲመለከቱኝ ግራ ይገባኝ ነበር” በማለት ነው በትዝብት የተናገሩት፡፡
ይሁን እንጂ በራስ መተማመን እያዳበሩ በማደጋቸው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ የፈጠረባቸው ችግር እንደሌለ ነው የተናገሩት። ዛሬ ላይ ወደ ኋላ ሊያስቀራቸው ነበረውን የአመለካከት ችግር አሸንፈው ወጥተዋል። በአደባባዮች ላይም አቁሟቸዋል፡፡ ይቻላል በማለት ለአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ሆነዋል፡፡ በዚህም ደስተኛ ናቸው፡፡
ወደ አመራር ቦታ ሲመጡም የቀደመው የማህበረሰቡ የአመለካከት ችግር አልተላቀቃቸውም ነበር፡፡ “አካል ጉዳተኛ እንዴት የሚሉ አልታጡም፡፡ አመራር መሆን ለኔ እንደማይመለከተኝ አድርገው የሚያስቡ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ እኔ ግን ችያለሁ” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
“ተግዳሮቱ የተማረው አመራርም ጋር አለ፡፡ አንዳንዶች ሱፍ ለብሰው የተዛባ አመለካከታቸውን ነው የሚያንፀባርቁት። ያንን አመለካከት ቢሮ ውስጥ ያመጡታል፡፡ እኔም እንደ አመራር ይህ የኔ ቦታ ነው እችለዋለሁ ብዬ ሞገትኩ፡፡ እወጣዋለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡ በሴትነቴም አድልኦ ነበር፡፡ በነሱ መነፅር ድርብ ጎዶሎ ነኝ፡፡ እሱን ለመሙላት የማደርገው ጥረት በእኔ ላይ ጫና ቢፈጥርም አሸንፌዋለሁ። ወደ መሪነት ስመጣ ያለ ቦታዬ እንደመጣሁ ስለሚታሰብ ጫናው ይበረታል።”
የሚያሳዝኑ ገጠመኞች እንዳሉ ሁሉ ያስደሰትዎ ገጠመኝ ካለዎት ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም፡-
“ስወልድ የተሰማኝ ስሜት ደስ የሚል ነበር፡፡ ልጆቼ በጣም ያስደስቱኛል፡፡ የእናትነት ስሜት እንዲሁም ከጓደኞቼ ጋር ተሰብስቦ መጫወትና ማውራት እወዳለሁ፣ እስቃለሁ፣ በጣም ተግባቢ ሰው ነኝ፡፡ ከሰዎች ጋር በተለያ ሀሳቦች ዙሪያ መነጋገር ያስደስተኛል” ብለዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች መብት በተገቢው እንዲከበር መስራት ያስፈልጋል የሚል አመለካከት እንዳላቸው ገልጸው እሳቸውም ባላቸው ኃላፊነትና የመብት ተሟጋችነታቸው ይህ እንዲረጋገጥ እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡
ኮሚሽነር እርግበ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደፊት እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ላይ የመሰማራት ውጥን አላቸው። አገልጋይነታቸውም እያደገ እንዲሄድ እንጂ እንዲቆም አይፈልጉም፡፡ “ለአካል ጉዳተኞች፣ በተለይም እንደኔ ላሉ ሴት ኣካል ጉዳተኞች ምሳሌ ወይም አርአያ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ሞዴል መሆን ብቻ ሳይሆን እድሎች መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡ መንገድ መክፈት፤ መንገዱን ማሳየት እፈልጋለሁ” ነው ያሉት፡፡
የሚያዩዋቸውን ነገሮች በብዕራቸው መግለጽ፣ ሀሳባቸውን መፃፍ፣ የተለያዩ መጻህፍትን ማንበብ ልዩ ተሰጥኦዋቸው እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ለአካል ጉዳተኞች ምን ይመክራሉ? መልዕክትዎስ ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“ራሴን ስገልጽ አካል ጉዳተኝነቴ ማንነቴ ነው፡፡ ልክ እንደ ሴትነቴ እንደሌሎች ማንነቴን እወደዋለሁ፡፡ ኣካል ጉዳተኝነቴን አውጥቼ ሳይሆን ከነ አካል ጉዳቴ እወደዋለሁ፡፡ ልክ እንደኔ ሌሎችም አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን መውደድ አለባቸው፡፡ የበታችነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋል” – አቶ ታሪኩ ዶንቃ
ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም…
ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተገለፀ