“የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋል” – አቶ ታሪኩ ዶንቃ

“የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋል” – አቶ ታሪኩ ዶንቃ

በደረጀ ጥላሁን

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ታሪኩ ዶንቃ ይባላሉ፡፡ ለአስራ ስድስት አመታት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በባለሞያነትና በአመራርነት አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት እና በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!!

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ታሪኩ፦  እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ በትውውቅ እንጀምር

አቶ ታሪኩ፦ ትውልዴ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በንሳ ወረዳ ጎንጆቤ ቀበሌ ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 6ተኛ ክፍል በተወለድኩበት አካባቢ በሚገኘው ጎንጆቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ከ 7ኛ እስከ 10ኛ ክፍል በንሳ ዳዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩኝ፡፡ የመሰናዶ ትምህርት የመማር ፍላጎቱ ቢኖረኝም በወቅቱ ከ10ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በግብርና፣ በጤና እና በመምህርነት ስለሚቀጠሩ ተወዳድሬ በማለፍ በወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ በዲፕሎማ መርሀ ግብር ተምሬ ተመረቅኩ፡፡ ከዚያም በቢዝነስ ማናጅመንት የመጀመሪያ ድግሪ ያዝኩኝ፡፡

ንጋት፦ የሥራ አጀማመርዎ እንዴት ነበር?

አቶ ታሪኩ፦ ሥራ የጀመርኩት በንሳ ወረዳ በሚገኙ ሶስት ቀበሌያት የግብርና ባለሞያ በመሆን ነበር፡፡ ከሶስት አመታት ሥራ በኋላ እዚያው ሱፐርቫይዘር ሆኜ የሰራሁ ሲሆን አጠቃላይ ለሰባት አመታት በግብርና ሞያ ሰርቻለሁ፡፡ በመቀጠል በወረዳው በተለያዩ ሰባት በሚሆኑ መስሪያ ቤቶች በአመራርነትና በባለሞያነት አገልግያለሁ፡፡

ከ2011 ጀምሮ ለሁለት አመታት የበንሳ ወረዳ አስተዳዳሪ በመሆንም ሰርቻለሁ፡፡ አስተዳዳሪ እያለሁ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ከሪፍት ቫሊ ዩንቨርስቲ ሁለተኛ ድግሪ ሰርቻለሁኝ፡፡ በተጨማሪም ሀዋሳ ከመጣሁ በኋላ በማርኬቲንግ ማናጅመንት ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ድግሪዬን ሰራሁ፡፡ ከ2012 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ ስራና ክህሎት ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ምክትል ኃላፊና በከተማ ሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ ሆኜ ለሶስት አመታት አገልግያለሁኝ፡፡ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ኃላፊ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፦ የሥራ ኃላፊነትን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ታሪኩ፦ የሥራ ኃላፊነት ከበድ ይላል፡፡ ኃላፊ ነኝ ብለህ ብቻ የምትሰራ ከሆነ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡን አገለግላለሁ ካልክ በጥንቃቄ ልትመራ ይገባል፡፡ ኃላፊነት ተሰምቶህ የምትሰራ ከሆነ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። በሰራሁባቸው ጊዜያት የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ በተለይ የስራ እድል ፈጠራ ላይ በሰራሁበት ወቅት ለወጣቱ ተዘዋዋሪ ፈንድ ተብሎ የሚመጣ ገንዝብ ነበር፡፡ ይህን ገንዘብ ለሚመለከታቸው ለማድረስ በምንሰራው ሥራ መሀል ለመቀራመት የሚፈልጉ አንዳንድ ስግብግቦች ያጋጥማሉ፡፡ እንደዚህ አይነቱ ለሥራህ እንቅፋት ይሆናሉ። ከዩራፕ መንገድ ጋር በተገናኘም ብዙ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ መንገዶችን ሰርተናል፡፡ ያልሰሩትን ሰርተናል ብለው ገንዘብ ለመውሰድ የሚሞክሩ ነበሩ፡፡ የነዚህ መንገዶች መሰራት ለሁሉም ጥቅም ነውና አለአግባብ የሚፈጸሙ ክፍያዎች ሀገርን የሚጎዱ በመሆናቸው ጥንቃቄን ይፈልጋሉ፡፡ አስተዳዳሪ እያለሁም በአንድ ወቅት በተፈጠረው ችግር አካባቢያችን ሰላም እንዲሆን በተሰራው ቅንጅታዊ ሥራ እውቅና ተሰጥቶናል፡፡ ችግሮችን በብልሀት እና ህብረተሰቡን አስተባብረህ ካልሰራህ ትቸገራለህ፡፡ የያዝከው ወንበር የህዝብ ነው ብለህ ለህዝብ ከሰራህ ኃላፊነትን መወጣት ይቻላል፡፡

ንጋት፦ ልማታዊ ሴፍትኔት አላማው ምንድነው?

አቶ ታሪኩ፦ ሴፍትኔት በገጠርና በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሀ ግብር ነው፡፡ በተለይ የድሀ ድሀ ተብለው የተለዩ አቅም የሌላቸው አረጋዊያን፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በልተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው የፕሮግራሙ አላማ፡፡

ፕሮጀክቱ የሚተገበረው አለም ባንክ ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት ሲሆን ተጠቃሚ የሚሆኑት ሰዎች በመስፈርቱ እንደተቀመጠው ተረጋግጦ ምንም የሌላቸው የድሀ ድሀ የሚባሉት እንዲጠቀሙበት ይደረጋል፡፡ የሚመደበው ገንዘብ ለሶስት አመት የሚከፈል ሲሆን 20 በመቶ ይቆጥባሉ። በዚህ ገንዘብ የራሳቸውን ህይወት እንዲያሻሽሉና እንዲመሩ የተቀረጸ መርሀ ግብር ነው፡፡

ንጋት፦ ፕሮግራሙ መቼ ተጀመረ?

አቶ ታሪኩ፦ ፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም እንደ ሀገርና ክልል የተጀመረ ሲሆን በሲዳማ ክልልም ሀዋሳ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በ2014 ዓ.ም ይርጋለም ከተማን በመጨመር በክልሉ በሁለት ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ሌሎች ከተሞችን ለመጨመር ፌዴራሉንና የአለም ባንክ እየተጠየቀ ሲሆን አሁን ላይ እንደሀገርም ስላልተጨመረ በሚጨመር ወቅት እኛጋም ይጨመራል የሚል መረጃ ነው ያለው፡፡

ንጋት፦ በሁለቱ ከተሞች የታቀፉ ተጠቃሚዎች ምን ያህል ናቸው?

አቶ ታሪኩ፦ በሀዋሳ እና ይርጋለም ከተሞች 22 ሺህ ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 14 ሺህ ተመርቀው ወጥተዋል። አሁን ላይ 6ሺህ የሚሆኑት ቀጥታ ተረጂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተረጂዎች አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያን ናቸው፡፡ ተመርቀው የሚወጡት በተለያየ ሥራ የሚሳተፉ ናቸው። በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ አረንጓዴ ሥፍራን የመንከባከብ፣ ችግኝ የመትከል፣ የተፋሰስ ሥራ እና በሌሎች የአካባቢ ልማት ሥራዎች ሰርተው የሚከፈላቸው ናቸው፡፡

ሁለቱ ከተሞች ተጨማሪ 18 ሺህ 994 ኮታ ተሰጥቶናል፡፡ አሁን ላይ ምልመላው አልቆ ወደ ትግበራ ልንገባ ነው፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ የሚከፈላቸው ተለይተዋል፡፡

ንጋት፦ ቀደም ሲል ለተመረቁት የሚደረግላቸው ድጋፍ ምንድ ነው?

አቶ ታሪኩ፦ ቀደም ሲል ተመርቀው የወጡትን ለሚመለከተው አካል ማለትም ለሥራ እድል ፈጠራ ጽ/ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በማፈራረም እንሰጣለን፡፡ ስልጠና ሰጥተን አስመርቀን ስራ ማስኬጃ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ 600 ዶላር ይሰጣቸዋል፡፡ ሶስት አመት ጨርሰው ሲመረቁ በየወሩ ግዴታ 20 በመቶ ይቆጥባሉ። ባጠቃላይ ለ3 ሺህ 663 አባወራ 137 ሚሊዮን ብር ተሰጥቷል፡፡ እነዚህም ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በአነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ሥራ፣ ሽመና፣ ሱቅ፣ ዳቦ ጋገራ የእንጀራ እና ከብት ማደለብ በመሳሰሉት እንደ ቢዝነስ ፕላናቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ይህንንም እየተከታተልን ሲሆን ሥራ እድል ፈጠራ በየመዋቅሩ ያሉት እንዲከታተሉ አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ እነሱም  ሼድ፣ ኮንቴነር እንዲሁም ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ከገንዘብ ተቋማት ጋር እንዲገናኙ እየተደረገ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም የአለም ባንክ ተወካዮች ከፌዴራል ጋር ሆነው በመመልከት ምስጋና በማቅረብ ነው የተመለሱት፡፡ እኛም ለሌሎች ተሞክሮ እንዲሆን በደቡብ ቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ተዘጋጅቶ እንዲታይ አድርገናል፡፡

ንጋት፦ በከተሞች የአረንጓዴ ልማት ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ታሪኩ፦ በከተማ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በየከተሞች አረንጓዴ አካባቢ መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ እየተሰራበት ነው፡፡ ኮሪደር ልማትም በዚሁ አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ በከተሞች ፕላን ላይ ያለ መሬት 40 በመቶ ለመሰረተ ልማት፣ 30 በመቶው ለመንገድ እንዲሁም 30 በመቶው ለአረንጓዴ ልማት መሆኑን መመሪያው ላይ ተካቷል፡፡ በከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ሲደረግም ይህን መሰረት አድርገው ነው የሚሰሩት፡፡ አሁን ላይ ፕላን ሲዘጋጅም በዚህ መሰረት ነው፡፡ ይህን ተቀናጅተን ነው የምንሰራው፡፡ ከዚህ አኳያ አረንጓዴ ልማት ለመስራት በተለይ በየከተማው ከሶስተኛ ወገን ነፃ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ መጀመሪያ ግን ፕላን ላይ መቀመጥ አለበት፡

በየከተሞቹ የሚገኙ አረንጓዴ ሥፍራዎችን የሥራ እድል ፈጠራ ጽ/ቤት ወጣቶችን በማደራጀት ውሀ የማጠጣትና የመንከባከብ ሥራ ይሰራል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የማናጅመንት ክፍተት እንዲስተካከል ደንብና አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመስተዳድር ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ በቢሮ የወጣ መመሪያም ወደ ታች ወርዷል፡፡ ይህም የአረንጓዴ አካባቢ ልማት የሚመራበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

በከተሞች የአረንጓዴ ልማት ሽፋን ምን ያህል እንደሆነ ስለማይታወቅ ጥናት አስፈልጓል፡፡ ሀዋሳ ብቻ 27 በመቶ እንደሆነ የቆየ ጥናት ያመለክታል፡፡አሁን እንደ አዲስ አራት ከተሞች ላይ ጥናት አድርገናል። በይርጋለም፣ ለኩ፣ ዳዬ እና አለታ ወንዶ ከተሞች ላይ የአረንጓዴ ልማት ሽፋን ተጠንቶ አልቋል፡፡ በቀጣይ ይህ ጸድቆ ወደ ተግባር ይገባል፡፡

ንጋት፦ በአሰራር ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተፈቱበት መንገድ እንዴት ነበር?

አቶ ታሪኩ፦ ሴፍትኔት ላይ ከምልመላ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ በፕሮግራሙ መታቀፍ የሌለባቸው ሰዎች እየገቡ ነበር፡፡ ይህንን ማጣራት ብዙ ድካም አለው፡፡ በመልማይ ኮሚቴ ክፍተት ምክንያት በርካቶችን ቀንሰናል፡፡ ለምሳሌ ሀዋሳ ላይ 34 ሺህ ያህል ከተመለመለው ወደ 13 ሺህ ተጠቃሚ ነው የለየነው፡፡ ይርጋለም ላይም 12 ሺህ ተመዝግቦ 5 ሺህ የሚሆኑት ናቸው መስፈርቱን ያሟሉት፡፡ ይህን እየገመገምን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል፡፡

በአረንጓዴ ልማት የሚስተዋለው ችግር ከማናጅመንት ችግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለአረንጓዴ ልማት የታጠሩ ቦታዎች ሲበላሹ ይታያል፡፡ እየቆሸሹ እንዲሁም የሰዎችና የመኪና ማደሪያ ሲሆኑም ይስተዋላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የጥበቃ ሥራ እንዲደረግ እየተሰራ ሲሆን በቀጣይም በህግ ማእቀፍ ተበጅቶ የመቅጣት ሥራ ይሰራል፡፡

በአረንጓዴ ልማት ሥፍራዎች የሚገኙ ችግኞች በውድ ዋጋ ተገዝተው የተተከሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ለመቆጣጠር መመሪያ በማውረድ እየተሰራበት ነው። ሌላው ሥፍራውን ከሶስተኛ ወገን ነፃ ያለማድረግ ችግር ነው፡፡ ችግሩ በተለይ ትንንሽ ከተሞች ላይ በስፋት ይስተዋላል፡፡ እንዲሁም አረንጓዴ ሥፍራዎቹ ላይ ለተለያየ አገልግሎቶች ለመስጠት አዝማሚያዎች አሉ። ይህ የአስተዳደራዊ ችግር ስለሆነ የሚፈታ ይሆናል፡፡

ሌላው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ያለው ችግር ነው፡፡ በቀን ምን ያህል ቆሻሻ ይመነጫል የሚለውን በጥናት ተመስርቶ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ በአራት ከተሞች ተጠንቷል፡፡ ይሁን እንጂ መወገድ ያለበት ቆሻሻ በሚፈለገው መጠን እየተወገደ አይደለም፡፡ ዘንድሮም በሌሎች አራት ከተሞች ላይ እየተጠና ይገኛል፡፡ ብዙ ችግር የሚታይበት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ ቦታ አለመኖር በአስተዳደራዊ ሥራዎች የሚስተካከል ይሆናል፡፡

ንጋት፦ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ሀሳብ ካለ!

አቶ ታሪኩ፦ በምግብ ዋስትና መርሀ ግብር መጠቀም ያለበት የሚመለከተው አካል ብቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ በቅንጅትና በመግባባት መሰራት አለበት፡፡ ለዚህም የህዝብ አደራ ስለወሰድን አደራውን በአግባቡ መወጣት አለብን፡፡ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው መዋቅር ኃላፊነት ተሰምቶት መስራት አለበት የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

በሌላ በኩል በከተሞች የሚሰሩ የልማት ሥራዎች የተሻለ ጽዱና አረንጓዴ ከተማ እንዲኖረንና በዚህም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ክልሉን ማልማትና መቀየር እንችላለን፡፡ አሁን ላይ አለም በከፍተኛ ደረጃ ያደገበት ዘመን ላይ ስላለን እኛም የሥራ ባህላችን ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ አለም ከደረሰችበት ለመድረስ መትጋት ይኖርብናል።

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ታሪኩ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡