ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አሃድ ጥምረት ለጥራት ንቅናቄና የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዳይሬክትሬት የ2017 የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም መድረክ አካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት እንደገለጹት፤ መጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ጥምረት ለጥራት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ተግባር ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ስትተገብር የቆየች ስትሆን ከለውጡ መንግሥት ወዲህ አክሞ ማዳን እና ከመካከል ሥራ አጣምሮ እየተስራ እንዳለ አቶ አስራት ገልጸዋል።
የጤና ዘርፍ ውጤታማነት እንዲረጋገጥ በሽታን በመከላከል ረገድ የጤና ተቋማት የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚፈልግ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ እና የመንገድ ልማት እና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አስፋው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ጥምረት ለጥራት ዓላማው የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አሃድ እና የወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አገልግሎት በሽታ ሽፋን ለማሻሻል በጋራ መማርን ለማጎልበት እንደሚጠቅም በዞኑ ጤና መምሪያ በሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስዩም ከበደ ተናግረዋል።
የ2017 ዓ.ም ግማሽ ዓመት የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ የ6 ወር የበሽታ መከላከል ዕቅድ አፈፃፀም በመምሪያው በሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ስዩም ከበደ ለመድረክ ቀርቦ ውይይት ተደረጎበታል፡፡
በሥራ አፈጻጸም ግምገማው ታመው የመጡ ተገልጋዮች አገልግሎት አሰጣጥ እርካታ ላይ የተመሰረተ፣ ተቋሙን ማራኪ ከማድረግ አኳያ፣ መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ከመፍታት አኳያ ተገምግሟል።
የወባ በሽታ መካከል በተመለከት ከሰኔ 19/2016 ዓ.ም እስከ ጥር 18/2017 ዓ.ም ድረስ ያለው አፈጻጸም የዞኑ 67 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ በረከት ባቡሎ እና ወ/ሮ ብርሃነ ብሩ በጋራ በሰጡት አሰተያየት፤ ጥምረት ለጥራት ጤና ክብካቤ አጠቃላይ የተሻለ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ የባለሙያዎች ስነ-ምግባር እንደሆነ ጠቁመው በህገ-ወጥ ህክምና ባለሙያዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የህግ እርምጃ አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
መምሪያው ከየወረዳዎቹ እና ከተማ አሰተዳደሮች ጋር በቀጣይም ስለሚከናወኑት ተግባራትና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መፈጸምና ማስፈጸም በሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ የግብ ስምምነት ተፈራርሟል።
በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊዎች በደም እጦት የሚሞቱትን ወገኖች ለማዳን ደም ልገሳ በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ አንዱዓለም ኡማ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም…
“ፓራ ቡላቻ”÷ ቀደምቱ የጋብቻ ስርዓት
ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ