“የአልማዝ ቦርሳ …”

“የአልማዝ ቦርሳ …”

“የአልማዝ ቦርሳ ትልቅ ነው

ሲበረብሩት ባዶ ነው …”

ይበልጣል ጫኔ

የጎረቤት ልጆች ናቸው። እርሜን ሰፈር ብውል÷ መስኮቴ ስር መጥተው “የአልማዝ ቦርሳ …” እያሉ ይጫወታሉ። ትንሽ እረፍት ማድረግ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም÷ ሁኔታቸው ስላስገረመኝ መጋረጃዬን ገልጬ እነሱን ማየት ጀመርኩ።

ከአፋቸው ከሚወጣው ሙዚቃዊ ጨዋታ እኩል እጃቸውን እያጋጩ÷ ያጋጩትን እጃቸውን ወደ ደረታቸው እየመለሱ÷ ደረታቸው ጋ የደረሰውን እጅ መልሰው እያጋጩ÷ ተመስጠው ይጫወታሉ። ሙዚቃው፣ እጃቸው የፈጠረው ጥምረት እና ስልተ- ምት አጠባበቅ እንደ አዲስ ገረመኝ።

“ይኼ’ኮ የድሮ ጨዋታ ነው” አልኩ ለራሴ። እውነትም የድሮ ጨዋታ ነው። ያኔ አልማዝ የሚባል ስም ብርቅ ነበር። ጨዋታው ምን ያህል የድሮ መሆኑን ለማወቅ ከፈለጋችሁ÷ ዛሬ ላይ አልማዝ ተብላ የምትጠራ ትንሽ ልጅ ፈልጉ። በፍፁም አታገኙም።

አልማዝ የተሰኘው የድሮ ስም ግን “የአልማዝ ቦርሳ” በተሰኘ የልጆች ጨዋታ ጀርባ ላይ ተፈናጦ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። በእርግጥ የልጆች ጨዋታ በስነ ቃላዊ ተፈጥሮው ከትውልድ ትውልድ መሸጋገሩ እሙን ቢሆንም÷ ብዙዎቹ ጨዋታዎች ከዘመን ጋር ቀርተዋል። ለምሳሌ የድሮ ህፃናት የጦርነት እና የዘመቻ ወሬ በየዕለቱ ስለሚሰሙ÷ እንዲህ የሚል ጨዋታ ነበራቸው፦

“ውርዬ … ወዬ

ባልሽ የት ሄደ … ዘመቻ

ምን ለብሶ …. ነጠላ

ምን ዓይነት ቀይ ጥለት”

እያለ ይቀጥል ነበር÷ የአሁኖቹ ልጆች ምናልባትም “ዘመቻ” የሚባል ቃል በውል የሚረዱ ላይሆኑ ይችላሉ። በእርግጥ “የአልማዝ ቦርሳም” ድንገት ተንከባሎ ደርሶባቸው እንጂ÷ የዘንድሮዎቹ ጨዋታቸውም ዜማቸውም ሌላ ነው።

በነገራችን ላይ “የአልማዝ ቦርሳ ባዶ ነው” የሚል ጨዋታ÷ የጨዋታውን አሮጌነት ብቻ ሳይሆን የተፈጠረበትንም ዘመን ያሳያል። ለምሳሌ በዚህ ጨዋታ ዘመን ቦርሳ ይይዙ የነበሩት እና በአልማዝ የተወከሉት ሴቶች÷ በሳምንት ወይም በአስራ አምስት ቀን ቅቤያቸውን ግጥም አድርገው የሚቀቡ ነበሩ።

ቅቤያቸውን ተቀብተው ውለው ያድሩና በቢ- 29 ወይም በፋኖስ ሳሙና ይታጠባሉ። እነዚህ ሳሙናዎች መደበኛ አገልግሎታቸው ለልብስ ማጠቢያነት ቢሆንም÷ በዚያ ዘመን በነበረው እሳቤ አገልግሎታቸው ሁለገብ ነበር። ለፊትም፣ ለልብስም፣ ለገላም … እንደተገኘው መታጠብ ነው÷ የዘመኑ ፋሽን። በእርግጥ ቁጥራቸው ያን ያክል ትልቅ ባይሆንም÷ በሉክስ፣ በሬክሶና፣ በካሜይ … እና መሰል የገላ ሳሙናዎች የሚታጠቡ ዘናጮች አልነበሩም ማለት አይቻልም።

ቅቤ ከመቀባት ሻገር ያሉት ደግሞ÷ እንደ ኮኮናት፣ ሳምራ፣ ዜኒት እና መሰል ቅባቶች ለጸጉራቸው÷ እንደ ቫዝሊን ጄሊ እና አስቴር ክሬም የመሳሰሉትን ቅባቶች ደግሞ ለፊት እና ቆዳቸው ማለስለሻ ይጠቀሙ ነበር። እነዚህን እና መሰል የዘመናቸውን መዋቢዎች በአመዛኙ በቤት ውስጥ የሚጠቀሟቸው ስለሆኑ÷ ቦርሳዎቻቸው ባዶ ነበሩ።

የአሁኖቹ “አልማዞች” ግን ከድሮዎቹ ይለያሉ። እየበሉ፣ እየጠጡ፣ እየሄዱ … በብዙ ተግባሮቻቸው ውስጥ መኳኳል አያጣቸውም። በዚህም ምክንያት ትላልቅ ቦርሳዎቻቸው ተንቀሳቃሽ የኮስሞቲክስ መደርደሪያ ናቸው።

ስልክ፣ ቻርጀር እና የጆሮ ማዳመጫዎች ተጠባቂ ነገሮች ናቸው። ከበዛ ጓዛቸው ጋር ተቀላቅሎ በቀላሉ አልለይ ስለሚላቸው÷ መታወቂያ፣ የባንክ ካርዶች፣ ጥሬ ገንዘብ እና መሰል ነገሮች ከቦርሳቸው ውስጥ አትጠፋም።

ከዚያ ውጪ ያለው ግን ውበት እና ንፅህና መጠበቂያ ነው። ከንፈር ማለስለሻ፣ ሊፒስቲክ፣ መስታወት እና ማበጠሪያ ሁሌም ዝግጁ ናቸው። ለድንገተኛ ጊዜ የሚሆን ፓድ÷ ተአምር ካልተፈጠረ በቀር አይረሱም። እዚህ ላይ ሽቶ፣ የጸሃይ መነጽር፣ ማስታገሻ መድሃኒት … በአንድ ጎን ይኖራል።

የፀሐይ መከላከያ ክሬም፣ የእጅ ክሬም፣ ሴረም (እንደ ቫይታሚን ሲ ያሉ ለፊት ጥራት የሚጠቅሙ ፈሳሾች)፣ ኮንሲለር እና ፋውንዴሽን፣ ብረሽ እና ብሌንደር፣ የዓይን መኳኳያ፣ የጥፍር ቀለም … ቦርሳቸው ውስጥ ከሚይዟቸው ነገሮች  ጥቂቶቹ ናቸው።

የሆነ ጊዜ አንድ ወዳጄ ሚስቱ ተሸክማ የምትዞረውን ጉድ አይቶ÷ በመገረም ነበር የነገረኝ። በዚህ የተነሳ “ሆድ ካገር ይሰፋል” የሚለውን ተረትና ምሳሌ ሲሰማ÷ “ሆድ ከሀገር ሊሰፋ ይችላል÷ ከሴቶች ቦርሳ ግን አይሰፋም” ያለኝ ቀን÷ ሳቄን መቆጣጠር አልቻልኩም።

የሆነ ቀን እንደ አጋጣሚ ከአንዲት ሴት ጓደኛዬ ጋር ምሳ በላን። ወደ መታጠቢያ ክፍል ስታመራ÷ ቦርሳዋን አንግታ በመሄዷ ቅሬታ አደረብኝ። “ስንት እና ስንት የጋራ ጉዳይ ያለን ሰዎች÷ እንዴት ነው ለቦርሳ የማንተማመነው?” የሚል ስሜት ተሰማኝ።

ስትመለስ ጠብቄ የተሰማኝን ነገርኳት። ደንግጣ ወይም ተቅለስልሳ ምክንያት ትደረድራለች ብዬ ስጠብቅ÷ እንባዋ ጠብ እስኪል ድረስ ሳቀችብኝ። እንደምንም ብላ በሳቅ የተበታተነ ስሜቷን ሰብስባ፦

“ምን ዓይነት ሰው ነህ?÷ይኸው ያለፕሮግራሜ አስለቅሰኸኝ ሜካፔን አበላሸህብኝ። ካንተ ጋር እየተሻማሁ ስበላ የተበላሸውን ሜካፔን ላስተካክል ነው÷ ቦርሳዬን ይዤ የሄድኩት” አለችኝ።

በዚህ የተነሳ ስንነጋገር፦

“እንዲህ ውብ ሆናችሁ ተፈጥራችሁ ስታበቁ÷ ይኼንን ያክል መጨነቃችሁ ምክንያቱ አይገባኝም። እኔ የምትቀባባ ሴት አትመቸኝም” አልኳት።

ንግግሬን ከምንም አልቆጠረችውም። ከቦርሳዋ ውስጥ  ብልጭልጭ ቀለም ያለው የዘይት ብልቃጥ አውጥታ ከንፈሯን ካራሰች እና ካዳረሰች በኋላ፦

“እናንተ እንድትወዱን ብለን÷ የግድ ኩበት ኩበት መሽተት ያለብን አይመስለኝም። አብዛኛው የሀበሻ ወንዶች ደግሞ ውሸታችሁ ልክ የለውም። ይኼንን ደግሞ የየዕለት ተግባራችሁ ይናገራል። በየመንገዱ ላይ ካላዘልኩሽ፣ ካልተገለበጥኩልሽ የምትሉት እነማንን እንደሆነ… እኔም አንተም እናውቃለን” አለችኝ።

ሳስበው ሁሉም ወንድ እንዲያ ነው÷ ለማለት አልወደድኩም። ንግግሯ ውስጥ እውነት የለም ማለትም አስቸጋሪ ነው። በእርግጥ በስነ ውበት እሳቤ ብቻ ሳይሆን በብዙ የህይወት ሚዛን ላይ÷ የምንለው እና የምንሆነው ለየቅል ነው።

ወደ መነሻችን “የአልማዝ ቦርሳ” ስንመለስ÷ ጨዋታነቱ የድሮ ቢሆንም÷ ቁምነገር አዘል እና ዘመንን አስታዋሽ ነው። ወደ ሰሞነኛው የልጆች ጨዋታ ስንመጣ “ቦላቦ ፈረሱ” የሚል የልጆች መዝሙር÷ አገሩንም አየሩንም ሞልቶታል። በእርግጥ ዜማው ደስ ይላል። በዝማሬው ውስጥ የሚተላለፉ ሃሳቦችም ለልጆች የሚሆኑ ናቸው። ግን ደግሞ ባልጠፋ የፈረስ ስም÷ ቦላቦ ማለትን ምን ይሉታል?÷ ብዬ ስነጫነጭ የሰማኝ ወዳጄ፦

“እና አባ ዳኘው ይበሉልህ?፣ አባ ታጠቅ፣ አባ በዝብዝ፣ አባ ቃኘው፣ አባ ሻንቆ፣ አባ ጎራው ወይስ አባ ነፍሶ … ይሁንልህ?÷ ሁሉን ነገር መተቸትማ ትክክል አይደለም። ልጆችህን ታሪክ ማስተማር ካለብህ በራስህ መንገድ አስተምራቸው” አለኝ÷ በስጨት ብሎ።

በእርግጥ “ሁሉን ነገር መተቸት ትክክል አይደለም” የሚለው ሃሳብ ትክክል ነው። ተቺነታችን እንዳይተች በመፍራት÷ መተቸት ያለበትን ነገር እንዳላዩ ማለፍም ትክክል አይሆንም።

ለትውልዱ የፈረስ ገጸ ባህሪ ያለበት አዲስ ሙዚቃ መስራት ካስፈለገ÷ ለዜማው እንዲስማማ አድርገው ፈጠራውን ከታሪክ ቢጠቅሱት÷ ልጆችን እያዝናና ያስተምራል። እንደ ወቅት እንደ ዘመኑ ያበጃጁታል እንጂ÷ የድሮ የተባለ ሁሉ የማይጠቅም አይደለም።