በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአርሶ-አደር የሚመራ የተፈጥሮ ዳግም ማገገሚያ ልማት ዘዴ (FMNR) ፕሮጀክት ተግባራት በቦንጋ ከተማ እየተገመገሙ ይገኛል።
የተጎዱ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያገግሙ ለማድረግ በአርሶ-አደር የሚመራ የተፈጥሮ ዳግም ማገገሚያ ልማት ዘዴ (FMNR) ፕሮጀክት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሀብትና የመሬት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ ገልጸዋል።
በክልሉ በወርልድ ቪዥን (FMNR) ፕሮጀክት ድጋፍ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲያገግም እተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መድረክ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ተገምግሞ በቀጣይ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የተለያዩ ስራዎችን እንዲሰራ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሀዋሳ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ እሸቴ በበኩላቸው፤ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በነበሩ በርካታ አካባቢዎች ልጆች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራ እንደነበር ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ይሰራ እንደነበርና ከ22 ዓመታት በኋላ ስራዎቹን ጨርሶ መውጣቱን አስታውሰው፤ FMNR በተሰኘ ፕሮጀክቱ አማካኝነት ቀሪ ስራዎቹን መቀጠሉን ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ጊዜያት ወደ ሌሎች ወረዳዎች ስራዎቹን ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመው፤ የተጎዱ የተፈጥሮ ሀብቶች ወደ ቀድሞ ለምነታቸው እንዲመለሱ አርሶ-አደሮችን በማሣተፍ በዓለም-አቀፍ ደረጃ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ቢሊዮን ሄክታር በላይ መሬትን መልሶ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም የዚህ ፕሮጀክት አካል ናት ብለዋል።
ይህ ስራ እ.ኤ.አ ከ2023 እስከ 2033 ድረስ የ10 ዓመታት እቅድ አለው ያሉት ኃላፊው፤ ያለፉት ሦስት ዓመታት ስራዎች ተገምግመው ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ አስታውቀዋል።
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከገዋታ ወረዳ ከወጣ በኋላ ስራዎች እንዲቀጥሉ በመደረጉ የክልሉን መንግስት አመስግነዋል።
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ሀዋሳ ማስተባበሪያ ቢሮ የፕሮጀክት ማናጀር አቶ ደገፋ ሱጌቦ በበኩላቸው፤ ወርልድ ቪዥን በዓለም ከ100 በላይ ሀገራት ከ75 ዓመታት በላይ በስራ ላይ መቆየቱን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ለ50 ዓመታት እንዲሁም በገዋታ ወረዳ ለ22 ዓመታት በተለያዩ መስኮች መስራቱን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ምክንያት የሚቀጥለው ትውልድ ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ይህንን ለማሣካት በትብብር መስራት እንደሚገባ ያመላከቱት አቶ ደገፋ፤ በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም ለማስቻል ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዞቦች ክልል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ቶማስ ሰነድ ለመድረኩ እያቀረቡ ሲሆን፤ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
በመድረኩ የክልሉ ግብርና ቢሮ ስራ ኃላፊዎች፣ በተለያዩ ወረዳዎች በፕሮጀክቱ ታቅፈው የሚሰሩ አርሶ-አደሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ከቀቤና ልዩ ወረዳ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው
የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ‘ፊተቴ’ በዓል በቆሼ ከተማ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል
ፈጣን፣ ወቅታዊና ተአማኒ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሳውላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ