“ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንን ስንጠቀም ዓለም አቀፍ ህጉን መሰረት በማድረግ ነው”

                                                      ዶክተር ተስፋለም አብርሐም

እንግዳችን ዶክተር ተስፋለም አብርሐም ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ በመምህርነትና ተመራማሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በውሃ ሀብት ምህንድስና 3ተኛ ድግሪ አላቸው፡፡ በውሃ ላይ ባደረጉት የምርምር ሥራቸው እንዲሁም በውሃ አጠቃቀም ላይ በሚነሱ ጉዳዮችና ተያያዥ ሀሳቦችን በማንሳት ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!!

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ተስፋለም፦ ለተሰጠኝ እድል እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ ራስዎን በማስተዋወቅ እንጀምር!

ዶክተር ተስፋለም፦ ተስፋለም አብርሐም እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት በሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ ትምህርቴን እዚሁ ሀዋሳ በሚገኘው ሐይቅ አንደኛ ደረጃ እና ኮምቦኒ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ምህንድስና እና ሜካናይዜሽን ትምህርት ክፍል ተምሬ በ2003 ዓ.ም ተመረቅኩኝ፡፡ በውጤቴ መሰረት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግራጁዬት አሲስታንስ ተቀጥሬ ለሁለት ዓመት በማስተማር፤ ዩኒቨርሲቲው በሰጠኝ እድል የሁለተኛ ድግሪዬን በውሀ ሀብት ምህንድስና እና አስተዳደር በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማርኩኝ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ወደ ሌክቸር በማደግ ለሶስት ዓመታት ከሰራሁ በኋላ የሶስተኛ ድግሪ/ፒ.ኤች.ዲ ትምህርቴን ጀርመን ሀገር በሚገኘው ዩኒቨርስቲ በውሀ ሀብት ምህንድስና ተምሬ፤ በሀይድሮሎጂ ስፔሻላይዝ አድርጊያለሁ፡፡ ሀይድሮሎጂ በገፀ ምድር እና ከርሰ ምድር ላይ ያለን የውሀ ሀብት መጠን፣ ሥርጭት እና አስተዳደር ላይ የሚያጠና የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡

ንጋት፦ የምርምር ሥራዎት ትኩረቱ ምን ላይ ነበር?

ዶክተር ተስፋለም፦ የምርምር ጥናት ያደረኩባቸው ሥራዎች ሶስት ናቸው፡፡ እነሱም በዓለም አቀፍ ጆርናል የታተሙ ሲሆን አንደኛው የሚያተኩረው በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ላይ ነው፡፡ በተፋሰሱ ላይ ብዙ ወንዞች ይገኛሉ። እነዚህ ወንዞች ከብዛታቸው አንፃር የተለኩና ያልተለኩ እንዲሁም የፍሰት መጠናቸው የሚታወቅና የማይታወቁ ናቸው፡፡ የተለኩት ወይም የፍሰት መጠናቸው የሚታወቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን የሳይንሱ ዘርፍ በማደጉ መረጃ የሌላቸው ወንዞችን ወደ ኋላ በመመለስና መረጃው ያላቸውን ወንዞች በማጥናት ያልተለኩ ወንዞችን መረጃ ማግኘት ይችላል።

የተለኩ እና ያልተለኩ ወንዞች የራሳቸው መለያ/ሲግኔቸር አላቸው፡፡ በዝናብ መጠን፣ የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን እንዲሁም እንደ አየር ንብረቱ ሁኔታ የወንዞች መጠን ይለያያል። በዚህ መሰረት መረጃቸው የማይታወቁ ወንዞችን ዳታቸውን ወደ ኋላ ሄዶ የማወቅ ሥራ ሰርቻለሁ፡፡ አጠቃላይ 55 የሚሆኑ መረጃ የሌላቸው እና ያልተለኩ ወንዞች መረጃቸውን የማደራጀት ሥራ የመጀመሪያና ትልቁ የምርምር ሥራዬ ነው፡፡

ሁለተኛው እነዚህን መረጃዎች በመያዝ የተለኩትን መረጃዎች በማደራጀት የአየር ንብረት ተጽእኖ ስነ-ምህዳራቸውን (ኢኮሎጂያቸውን) እንዴት እንደሚጎዳ ነው ያጠናሁት፡፡ ወንዞች በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቁት ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ውስጥ ናቸው፡፡ በብዙ የዝናብ መጠን ጎርፍ ይከሰታል፡፡ ዝናብ ሲጠፋ ደግሞ ወደ ድርቅ የመለወጥ እድል አላቸው፡፡

ይህ ሲሆን ኢኮሲስተሙ (ስነምህዳሩ) እንዴት አብሮ ሊለወጥ ይችላል? ወንዝ ውስጥ የሚኖሩ ሥነ ፍጥረታት፣ በውሃ ውስጥና ዳር የሚኖሩ ነፍሳት እና ልዩ ልዩ የተክል አይነቶች እንዲሁም እነሱን ተጠግተው የሚጠቀሙ ሰዎችና ሌሎችም እንዴት ሊጎዱ ይችላሉ? ለሚሉ ጥያቄዎችና የውሃ መጠኑ በመቀነሱ ምክንያት የሚፈጠር ተጽእኖ ብሎም በአየር ንብረት ለውጥ ላለፉት 30 እና በሚቀጥሉት 100 ዓመታት ስለሚያስከትለው ተፅእኖ የሚዳስስ ጥናትና ምርምር አድርጌያለው።

ሶስተኛው ጥናቴ በሀዋሳ ጥቁር ውሃ ወንዝ ላይ ነው፡፡ ከሌሎች ወንዞች አንፃር በተፈጥሮ የተለየ የሚያደርገው የፍሰት መጠኑ ክረምትና በጋ ከፍተኛ ልዩነት አለማሳየቱ ነው፡፡ የዝናብ ሥርጭቱ የውሃውን መጠን የመቀነስና የመጨመር ሁኔታ በወንዙ ላይ በጉልህ አይታይም፡፡ ስለዚህ ይህን የሚያስተጓጉል ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ከወንዶ ገነት ተራራዎች ብዙ ውሃ ይመጣና ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ተጠራቅሞ ይቆያል፡፡ ስለዚህ የወንዝ ውሃው ወደ ሀይቁ የሚደርስበትን ጊዜ ያዘገየዋል። ይህም አብዛኛዎቹ የሀይድሮጂ ሞዴሎች ከተሰሩበት መዋቅር ለየት ያደርገዋል። ስለዚህ ይህንን ለየት ያለ ተፈጥሯዊ አካሄድ ሞዴል የማድረግ ስራ ነው የሰራሁት፡፡ እነዚህን ስራዎች አንድ ላይ በማድረግ ነው የሶስተኛ ድግሪዬን መመረቂያ የሰራሁት፡፡

ንጋት፦ ከውሃ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ጥናታዊ ጽሁፎችን አሳትመዋል?

ዶክተር ተስፋለም፦ የሁለተኛ ድግሪዬን እንደጨረስኩ ነው ጥናታዊ ጽሁፎችን ዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ ማሳተም የጀመርኩት፡፡ እስካሁን 24 የሚሆኑ የታተሙ ጽሁፎች አሉኝ፡፡ አብኛዎቹንም ዶክትሬቴን ከያዝኩ በኋላ ነው ያሳተምኩት፡፡

ሀገር ውስጥና ውጪ ሀገር ካሉ ጓደኞቼ እንዲሁም ከቀድሞ አማካሪዎቼ ጋር በመሆን ባለን የምርምር ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የውሃ አካላት በተለይም አባይ ላይ የሚያተኩር አንድ ፕሮጀክት ነበረን፡፡ ቀድሞ ጀርመን ሀገር እማርበት በነበረው ፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካሉ ሳይንቲስቶች ጋር በመተባበር ይህንን ፕሮጀክት ሰርተናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ትልልቅ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተከዜ፣ አባይና ኦሞ ላይ ምን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ይቻላል፣ የሚመረተውን ኃይል እንዴት መጨመር እንችላለን፣ የሚል የምርምር ስራ አሳትመናል። ይህም ስራ የሚያተኩረው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርስ እንዴት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ማምረት እንደምንችል ያሳያል። ይህም ኢትዮጵያ እና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በሀይል ማምረትና ውሃ አጠቃቀም እንዴት ሚዛናዊ ማድረግ እንደሚቻል ያሳያል።

ንጋት፦ በሀገራችን የውሃ ሀብት ቢኖርም በአጠቃቀምና ማስተዳደር ላይ የሚስተዋል ክፍተት አለ፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው?

ዶክተር ተስፋለም፦ ውሃ ህይወት ነው ይባላል፡፡ ሀገራችን የውሃ ማማ ብትሆንም በሚያስቆጭ ሁኔታ ባለፉት ጊዜያቶች ውሃው በአግባቡ ተጠንቶና መጠኑ ታውቆ መጠቀም አልተቻለም ነበር፡፡ ያለን የኢኮኖሚ ሁኔታ ሊሆን ይችላል እንዳንጠቀም ያደረገን፡፡ ሌሎች ሀገራት ለእድገታቸው ትኩረት ከሚሰጡባቸው ዋነኛው ውሃ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ውሃ ለመጠጥ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለሀይል ማመንጫ እና ለሌሎች ኢኮኖሚን የሚያንቀሳቅሱ ዘርፎች ትልቅ ግብአት ነው፡፡ ነገር ግን ችላ ተብሎ የቆየ ነበር፡፡ ይህንን ለመጠቀም የሚያስችል አቅምም በተወሰነ መልኩ አጥተንም አይመስለኝም፡፡ ይሁንና የውሃ ሀብታችንን መለካት፣ መያዝ እና በአግባቡ ማስተዳደር ደግሞ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ውሃ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ለማደግ እድሉ አላቸው፡፡ ወደ ገጠሩ አካባቢ ብዙ ወንዞች ይፈሳሉ፡፡ ያንን ማጎልበትና አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ለአጠቃቀም በሚመች አኳኋን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

የግብርና አሰራራችንን እና የህዝብ አሰፋፈራችንን ከውሃ ቅርብ በማድረግ ለግብርናና ለመስኖ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ከውሃ ችግር መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ባለው የከተሞች እድገት ሰፊ ስራ መስራት የሚቻለው በውሃ ነው፡፡ ውሃ በሁሉም ዘርፍ ላለው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ስለዚህ ዘርፉ ትልቅ ትኩረትን ይፈልጋል ባይ ነኝ፡፡

ውሃ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ የኤሌክትሪክ ሀይል አመንጭተን ወደ ውጪ እየላክን ነው፡፡ የውጪ ምንዛሪ እያገኘንበትም ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ደረጃ ያለን ሀብት ስለሆነ፣ ያለንን የውሃ ሀብት መለካትና ማወቅ አለብን፡፡ በየቀኑ የሚፈስ የወንዝ መጠን በመለካት ዳታዎችን በአግባቡ ሰንደን ብናዘጋጅ ጥሩ የሆነ የመስኖ ዲዛይን እና ግድቦችን መስራት ይቻላል፡፡ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎች መስራት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በህዝብም ሆነ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ያሻዋል፡፡

ንጋት፦ በውሃ ሀብታችን አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ሚና እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ተስፋለም፦ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል የአንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ የሚማሩ ተማሪዎች አሉን፡፡ በተቋሙ የሚሰጠው ሥርዓተ ትምህርት በስፋት ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት የሚዳስሱ እና በጥሩ ሁኔታ የተዋቀሩ ናቸው፡፡ በስርዓተ ትምህርቱ የውሃ ህግ ውሃን ማስተዳደር የሚል አለ፡፡ ይህ ማለት ሀገራችን ብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሏት፡፡ የውሃ አስተዳደር ወይም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተዳደር ላይ ትምህርት መስጠት ለተማሪዎች አስፈላጊ ነው፡፡ እኛ የምንሰራው በመሰረታዊነት የውሀ ባለሙያ በማፍራት፣ በምርምር እና በማማከር ነው፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ውሃ እንዳለ ሁሉ በሀገር ውስጥ ከክልል ክልል ከዞን ዞን እና ከቀበሌ ቀበሌም እንዲሁ አለ፡፡ ድንበር ተሻጋሪነት አለም አቀፍ ችግር ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥም በውሃ አጠቃቀም በመስኖ፣ በከብቶች መጠጥ እና በሌሎችም ምክንያቶች የተለያዩ ችግሮች ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ በስርዓተ ትምህርቱ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህም ውሃን በፍትሀዊነት እና በእኩልነት መጠቀም እንዳለብን ያሳያል፡፡ ይህ በዩኒቨርስቲው ደረጃ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ዘንድ ወርዶ ደግሞ መስራት ይገባናል፡፡ ትውልድን እንዲሁም ማህበረሰቡን ከማስተማር አንፃር በኛ አቅም ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ባለድርሻ አካላት እገዛ ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰባት የሚሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሏት፡፡ እነዚህም ትልቅ የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ውጪ ይዘው ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ህጉ ምን ይላል፡፡ የሀገር ውስጡስ የውሀ አስተዳደር ህግ ምን ይላል የሚለውን በሥርዓተ ትምህርቱ ተቀርፆ በዩኒቨርስቲ ይማሩታል፡፡

ንጋት፦ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ህጉ ምን ይላል?

ዶክተር ተስፋለም፦ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና አጠቃላይ ውሃ አካላት ሀይቆች እንዲሁም ውቅያኖሶችን ጨምሮ አጠቃቀምን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ህግ አላቸው፡፡ እኛን ስለሚመለከተው የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ስናይ ውሃ የጋራ ሀብት ነው፡፡ የውሃ ሀብት የተፈጥሮን ገፅታ ተከትሎ ከአንድ ሀገር ሊወጣ ወይም ሊገባ ይችላል፡፡ የብዙ ሀገራት ድንበር ለውቅያኖስ የውሀ ሀብት አጠቃቀም ምቹ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን አይነት ሁኔታ ለማስተዳደር ዓለም አቀፍ ህጎች ወጥተዋል፡፡

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተዳደር በሚመለከት ዓለም አቀፍ ህጎች አሉ፡፡ የዚህ ህግ ዋናውና መሰረታዊ ጉዳይ የሚባለው በእኩልነትና ፍትሀዊነት መጠቀም ነው፡፡ ሌላኛው አካባቢ ላይ ጉልህ የሚባል ተጽእኖ ሳያደርስ የውሃ ሀብትን ማልማት ይቻላል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ጉዳዮችን ያካትታል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የውሀ ሀብታችንን መጠቀም ያስችለናል፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን ውስጥ መጠቀም የጀመረችው አንዱ የህዳሴ ግድብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ኦሞ ወንዝ ላይ ልማት ሲጀመር ብዙ ቅሬታዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ለረጅም ዓመታት ወንዙ ወደ እነሱ ሲፈስ ነበር፡፡ ይሁንና ለኃይል ማመንጫ ሲሆን ውሃው ሀይል አምርቶ ተመልሶ የሚፈስበት አካሄድ ነው ያለው፡፡ ይህን ህጉ አይከለክልም፡፡ አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት በተለይ ግብጽ ግድቡ እንዳይገነባ ተቃውሞ ሲያሰሙ መታየቱ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ በየዓመቱ ውሃ ሲሞላ ህግን በመከተል ነው፡፡ ሌሎች እንዳይጎዱ ተብሎ ይለቀቃል፤ ለአካባቢ ወይም ኢንቫይሮንመንት ተብሎም ውሀ ይለቀቃል፡፡

ለመስኖ ልማት እንኳን ሁሉንም ውሃ መጠቀም አንችልም፡፡ ወንዝ ለአካባቢ ወይም ኢንቫይሮንመንታል ፍሰት ተብሎ ፍሰቱ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ሌላው በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት አሳ እና የመሳሰሉት እንዳይጎዱ ከ10 እስከ 20 በመቶ መለቀቅ እንዳለበት ይመከራል፡፡ እኛም ግድቡን ስንሰራ ለአካባቢ ወይም ኢንቫይሮንመንታል ፍሰት ተብሎ ከሚለቀቀው በተጨማሪ ተከታታይ የውሃ መጠን እንዲሄድ እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም የህዳሴው ግድብ ክረምት ተጠብቆ እንዲሞላ የተደረገው ከዚህ አንፃር ነው፡፡

ብዙ ጥናታዊ ጽሁፎች በ2021 ሱዳን ላይ ጎርፍ እንደነበረ አሳይተዋል፤ ግድቡ ባይኖር ደግሞ የበለጠ የጎርፍ ጉዳት ይኖር ነበር፡፡ ግድቡን በምንሞላበት ጊዜ የፍሰት መጠኑ ብዙም አልቀነሰም፡፡ ግድቡን ስንሞላ አሞላሉ ላይ ለነሱ የሚገባውን እየተለቀቀ ነው የተገደበው፡፡ ከዚህ አንፃር ህጉን ተከትለን ነው ግድቡን የሰራነው፡፡ ኃይል ሲያመነጭም ውሃው ተርባይኑን እየመታ ስለሚወጣ የሚፈልጉትን ውሃ ያገኛሉ፡፡

ኃይል ማመንጫው በሰዎች ሬጉሌት የሚደረግ በመሆኑ ደግሞ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከልክ ያለፈ ውሃ ሲመጣ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በጎርፍ እንዳይጎዱ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ስለዚህ የጎረቤት ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንን ስንጠቀም ዓለም አቀፍ ህጉን መሰረት በማድረግ ነው የሚሰራው፡፡

ንጋት፦ ግድብም ሆነ ሌሎች ፕሮጀክቶች በህጉ መሰረት ከተሰራ ስጋቱ ለምን ተፈጠረ?

ዶክተር ተስፋለም፦ ግድቡ ከተሞላ በኋላ ሙሉ በሙሉ ውሃውን የመቆጣጠር ስልቱ በኛ እጅ ነው የሚሆነው፡፡ ሲፈልጉ ሊዘጉብኝ ይችላሉ የሚል ስጋት ያለ ይመስለኛል፡፡ ካለን ታሪካዊ ግንኙነት አንፃር የበላይነት የሚወሰድባቸው ይመስላቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚፈጠር ስጋት የለም፡፡ የአባይ ወንዝ በጣም ትልቅ ወንዝ ነው፤ ለሁሉም በቂ ነው፡፡ ይህንን ካለማወቅ የመጣ ይመስለኛል፡፡

ከዓለም አቀፍ ህጎች በተጨማሪ ልምዶች ምን ያሳዩናል የሚለውን ስናይ፤ አባይ ወንዝ ላይ አራት በዓለም አቀፍ ጆርናል ላይ የታተሙ ጽሁፎች አሉኝ፡፡ እነዚህ ከዶክትሬት ትምህርቴ በኋላ የተፃፉ ናቸው። ስለ ጋራ ተጠቃሚነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሀይድሮ ፓወር ሲስተሙን እንዴት ይጎደዋል የሚልና የግድቡ መሰራት ጎርፍና ድርቅን እንዴት ይከላከላል የሚል ከውጪ ሀገር ከሚገኙ ተባባሪዎች ጋር ስንሰራ እንደተረዳሁት ሁሉም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ወደ ግጭት አያስኬዱም፡፡ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ጉዳይ ጥሩ ታሪክ ያላቸው ሀገራት አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ብራዚል እና ፓራጓይ፣ እንዲሁም ሩሲያ እና ፊንላንድ ይጠቀሳሉ።

በእርግጥ ውሃ ግጭት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ከጎረቤት ሀገራትም ሆነ በሀገር ውስጥ የግጭትም የመልካም ትብብርም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ አጠቃቀማችን ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ አሉ፡፡ በውሃ ጉዳይ ወደ ግጭት የገቡ እንዳሉ ሁሉ በድንበር ላይ በሰሯቸው ፕሮጀክቶች ሁለቱም ተጠቃሚ ሆነው ወደ መልካም ሁኔታ የተመለሱ ሀገራት አሉ፡፡

ለማሳያነትም ከዓመታት በፊት በሩሲያ እና ፊንላንድ ድንበር የሚያልፍ ወንዝ አለ፡፡ በዚያ ወንዝ ላይ ፕሮጀክት ተሰርቶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሁለቱ ሀገራት ቅራኔ ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክት በመተማመን ስለተሰራ ሁለቱም ሀገራት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በጋራ የተሰራው ፕሮጀክት ተጠቃሚ ስላደረጋቸው የድንበር ቁርሾን እንዲቀርፉ አስችሏቸዋል፡፡

ሌላኛው ብራዚል እና ፓራጓይ ድንበር ላይ ፓራና የሚባል ወንዝ አለ፡፡ የፓራና ወንዝ ስምምነት ይባላል፡፡ ሀገራቱ በድንበር የሚጣሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ወንዙ ተገድቦ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ሰርተውበት ስለነበር የነበረውን ቅራኔ ትተው ግንኙነታቸውን ወደ ጥሩ ደረጃ አሻግረዋል፡፡

ስለዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ስንል ጥልና ጭቅጭቅ ያለበት ብቻ አይደለም፡፡ በጋራ ከሰራንበት እድልም የሚያመጣ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወደ ግጭት የሚያመሩም አሉ፡፡ ህንድ እና ፓኪስታንን ማንሳት ይቻላል፡፡ በአካባቢው ወደ ፓኪስታን የሚፈስ ወንዝ አለ፡፡ በወንዙ ላይ በተሰራው ፕሮጀክት አለመስማማት ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ህጎች አልተጠበቁም ይባላል፡፡ አንዱ ተበደልኩ ይላል፡፡ በዚህ ሰአት የነበራቸው ፍትጊያ ከፍ ብሎ ወደ ጦርነት ደረጃ ደርሶ የቆመበት ሁኔታ ነበር፡፡

ንጋት፦ ተጨማሪ ሀሳብ ካለዎት!

ዶክተር ተስፋለም፦ ውሃ አለን ማለት የመስኖ ሥራ በስፋት ይሰራል፤ ይህም የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ይረዳናል፡፡ በኢንቨስትመንት እንዲሁም ለሀገር እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ሥራዎች በውሃ መስራት ስለሚያስችል ለውሃ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡ ትውልዱን ስለ ውሃ አጠቃላይ ግንዛቤውን ማስፋት የሚያስችል ሥራም መሰራት አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ዩኒቨርስቲ ላይም ሥራዎች እየተሰሩ ስለሆነ ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡

የውሃ ሀብታችን ላይ ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት በቂ አይደለም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ እየተሰጠ ካለው ትምህርት በተጨማሪ ስለ ውሃ ሀብታችን ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ ይህም የሚመለከታቸው አካላት ውሃ ሀብታችን በቂ መረጃ እና የመረጃውን ጥራት በማሳደግ ትክክለኛ ዳታ በዘላቂነት መያዝ አለባቸው፡፡

ንጋት፦ ስለሰጡን ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ

ዶክተ ተስፋለም፡– እኔም አመሰግናለሁ