“እንደ ስማቸው የኖሩ ተመራማሪ”

“እንደ ስማቸው የኖሩ ተመራማሪ”

የሳምንቱ እንግዳችን ፕሮፌሰር አቻምየለሽ ገ/ፃዲቅ ይባላሉ፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር በመሆን አዲስ ታሪክ ፅፈዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ተመራማሪ እና የጥራት ማረጋገጫና ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲሆኑ በቤተሰብ ደረጃም ስኬታማ ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የሕይወት መንገዳቸውን በማንሳት ስለደረሱበት ስኬት እና ተያያዥ ቤተሰባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡

በካሡ ብርሃኑ

ንጋት፡– በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሠግናለሁ፡፡

ንጋት፡– ሥምዎ እንዴት እንደወጣ ይንገሩን እስቲ…? ምንአልባት ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ታይቷቸው ይሆን ወላጆችዎ አቻምየለሽ ያሉዎት?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– (ረጅም ሳቅ)…እውነት ነው ሰዎች ዛሬ ከደረስኩበት ደረጃ ጋር አያይዘው እውነትም አቻምየለሽ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን ሥሜን ያወጡልኝ እቴሜቴ ብዬ የምጠራቸው የቅርብ ዘመዴ (የእናቴ አጎት ሚስት) ናቸው፡፡ እኔ ስወለድ ከነበሯቸው ላሞች በተጨማሪ በርከት ያሉ ጊደሮች መወለዳቸውን ተከትሎ ምርጥ ከሚባሉት ነው ወተት ተመርጦ ይሰጠኝ የነበረው፡፡ በዚህ ምክንያት እቴሜቴ ይህቺ ልጅ ዕድለኛ በመሆኗ አቻምየላት አሉና አቻምየለሽ አሉኝ (ሳቅ)፡፡ በዚህ ምክንያት እኔም ሥሜን እወደዋለሁ፡፡ ዩኒቨርስቲ ጨምሮ ሥራ በጀመርኩበት ወቅት አንዳንዶች ከዘመኑ ጋር አይሄድም ቀይሪው ቢሉኝም አሻፈረኝ ብዬ በምወደው ሥም እየተጠራሁ ይሄው አለሁ፡፡

ንጋት፡– ፕሮፌሰር የት ተወለዱ? አስተዳደጋቸውስ እንዴት ነበር?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ተወልጄ ያደኩት በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ክብረመንግስት በምትባል ከተማ ነው፡፡ (አሁን በኦሮሚያ ክልል የምትገኝ ስትሆን አዶላ ወዩ ትባላለች)፡፡ ከተማ ተወልጄ ስለሆነ ያደኩት፤ ትምህርቴንም በልጅነቴ ነው የጀመርኩት፡፡ ቤተሰቦቼ ትምህርት ቀመስ በመሆናቸው ጥሩ የሚባል የልጅነት እና የትምህርት ጊዜ እንዲኖረኝ አድርገው ነው ያሳደጉኝ፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል እዛው ነው የተማርኩት፡፡

ንጋት፡– የትምህርት ቤት ቆይታዎስ እንዴት ነበር የሚለውን እናንሳ?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ከመዋዕለ-ህፃናት ነው ትምህርት የጀመርኩት፡፡ ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ያለውን እዛው ክብረ መንግስት ራስ ብሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት፡፡ በመሃል እናቴ ታማ ስለነበር እሷን ለማሳከም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እስከ ስድስት ያለውን ይርባ ሙዳ የሚባል ትንሽዬ ከተማ ተምሬ ነው የተመለስኩት፡፡ ከሰባት እስከ 10ኛ ክፍልም እዛው ክብረመንግስት ራስ ብሩ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት፡፡ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ደግሞ ተመልሼ ቦሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡

እውነት ለመናገር በወቅቱ በትምህርት ከነበረኝ አቅም አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ተጉዣለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ እንደውም አንደኛ ደረጃ ላይ ሶስት ታላላቆቼ ላይ ደርሼባቸው አብረን ነበር የተማርነው። በኋላም አልፌያቸው ቀድሜ ትምህርት መጨረሴን አስታውሳለሁ፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ የምባል ዓይነት ተማሪ ነበርኩ፡፡ የደረጃ ተማሪ ብሆንም ይህን ያህል የተጨበጨበልኝ ነበርኩ ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ አሁን ላይ ከአንዳንድ ጓደኞቼ ጋር ስናወራ እኔ እኮ በመንግስት ትምህርት ቤት ተምሬ ነው እዚህ የደረስኩት እያልኩ እፎክርባቸዋለሁ (ሳቅ…)፡፡

ንጋት፡– የከፍተኛ ትምህርትንስ የት ነው የተከታተሉት?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ከፍተኛ ትምህርቴን ወደ ጎንደር በማቅናት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በመቀላቀል ኮምፕሬሄንሲቭ ነርሲንግ ነው ማጥናት የጀመርኩት፡፡ እንደሚታወቀው ጎንደር ዩኒቨርስቲ በጤና ዘርፍ ጥሩ ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ስለነበር ትምህርቱ ከባድ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ምደባ በጋዜጣ ነበር የሚነገረው፡፡ 96 ተማሪዎች ሆነን ትምህርት ብንጀመርም የጨረስነው ግን 24 ነን፡፡ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት ስለነበር ብዙዎቹ በጊዜ ተሰናብተዋል፡፡ እኔ ግን በ1988 ዓ.ም በዲፕሎማ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል ተሸልሜ በማዕረግ ካጠናቀቁት መካከል ነበርኩ፡፡

ንጋት፡– ከተመረቁ በኋላ ወደ ሥራ ዓለም ነው የገቡት ወይስ ትምህርትዎን ነው የቀጠሉት?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገባሁት፡፡ በወቅቱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀርቼ የማስተምርበት ዕድል ተሰጥቶኝ ነበር። እኔ ግን አስተማሪ ሆኖ የመቅረት ህልም ስላልነበረኝ እና ከቤተሰብም መራቁ ከልጅነት ጋር ተዳምሮ ጥያቄውን አልተቀበልኩም፡፡

በዚህ ምክንያት ሥራ ለማግኘት በወቅቱ በነበረው አሰራር መሰረት ጤና ሚኒስቴር እጣ አንስቼ የቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ነው የደረሰኝ፡፡ ከክልሉም ድጋሚ እጣ ሳነሳ ሲዳማ አካባቢ በንሳ ደርሶኝ በ1989 ዓ.ም የሥራ ዓለም ሕይወትን ጀመርኩ፡፡

እዛም እስከ 1990 ዓ.ም መጨረሻ ከሰራሁ በኋላ፤ ዳራ ወረዳ ቀባዶ ከተማ አዲስ ሆስፒታል መሰራቱን ተከትሎ ተዘዋውሬ ከ1991 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ አገልግያለሁ። በቀባዶ ለሁለት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ተወዳድሬ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ድግሪ ትምህርት በ1994 ዓ.ም ገባሁ፡፡ በመሃል ግን ትዳር መስርቼ ልጆች ወልጄ ስለነበር ክረምት ላይ ስመለስ ተጎድተው ጠበቁኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርቴን በወቅቱ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ወደሚጠራው የአሁኑ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማዘዋወር በ1996 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዬን አጠናቀኩ፡፡

ንጋት፡– ከመጀመሪያ ዲግሪ በኋላ ሥራዎን የት ነው የቀጠሉት?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– አስታውሳለሁ ምርቃቱ ክረምት ላይ ስለነበር ከመስከረም ወር ጀምሮ ወደ ዳራ በማቅናት የቀድሞ ሥራዬን ነው የቀጠልኩት፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ዲግሪ መያዝ ጥሩ ቦታ ያሰጥ ስለነበር የወረዳው በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ በመሆን ከወረዳው ኃላፊ ቀጥሎ ከፍተኛ ደመወዝ /1 ሺህ 780 ብር/ ማግኘት ጀመርኩ (ሳቅ…)፡፡  

በዚህ ኃላፊነት ከሀዋሳ እየተመላለስኩ አንድ ዓመት ገደማ ከሰራሁ በኋላ የሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያወጣውን የረዳት ምሩቅ የሥራ ማስታወቂያ ተፈትኜ በማለፌ ደመወዜን በ680 ብር ቀንሼ ለልጆቼ ስል ከቀባዶ ወደ ሀዋሳ የምገባበት ዕድል በ1997 ዓ.ም ተፈጠረ።

የሚገርመው እዛም ብዙ ሳልቆይ ከሰባት ወር በኋላ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን የሥራ ማስታወቂያ ተከትሎ ዩኒቨርስቲውን የምቀላቀልበት አጋጣሚ ተፈጥሮ በሚያዚያ ወር 1997 ዓ.ም በመምህርነት ተቀጥሬ ሥራ ጀመርኩ፡፡

እዛም አንድ ዓመት ገደማ ከሰራሁ በኋላ የትምህርት ዕድል አግኝቼ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በህብረተሰብ ጤና የሁለተኛ ዲግሪዬን /ማስተርስ/ በ2002 ዓ.ም አጠናቀኩ፡፡ ሀዋሳ ተመልሼ ሥራ በጀመርኩ በዓመቱ የሦስተኛ ዲግሪ /PHD/ የትምህርት ዕድል መጥቶ ከእኔ በላይ የነበሩ ሁለት ባልደረቦቼ እንዲማሩ ተሰጣቸው፡፡ ነገር ግን የመጣው የትምህርት ዕድል እነሱ ከተማሩት ትምህርት ጋር የሚሄድ ባለመሆኑና መውሰድ የሚጠበቅባቸው ኮርስ ስለነበር ለምን እኔ አልጠቀመውም በሚል ዕድሉ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ተሰጠኝ፡፡ በዚህም መሠረት በ2007 ዓ.ም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ከአዲስ ኮንቲኔንታል የሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ፕሮግራም ሦስተኛ ዲግሪዬን (PHD) በሕብረተሰብ ጤና አግኝቻለሁ፡፡

ንጋት፡– ተመራማሪ እንደመሆንዎ የምርምር ሥራዎ ምን ላይ ያተኩራል? የተለየ ምክንያትስ ይኖረው ይሆን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– አብዛኛው ትኩረቴ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ነው። አሁንም ወደፊትም የማተኩርበት ዘርፍ ነው፡፡ እኔ በልጅነቴ ስለሆነ እናት የሆንኩት የልጆችን ነገር በደንብ ነው የማውቀው፡፡ ወደፊት መሆን የምትፈልጊው እንኳን ብባል ከልጆች ጋር የሚያውል ሥራ መሥራት ነው የምፈልገው፡፡ ከዚህም ባለፈ ብዙ አልተሰራምና አሁን የምናያቸው ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ጋር የሚያያዙ የእናቶች ሞት ውስጥን የሚያሳምሙ ናቸው፡፡

እኔ ደግሞ እንደ ሴትነቴ ዝንባሌዬ ወደዛ ነው፡፡ ምንም እንኳን ችግሩ ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም ይህንን ሁኔታ መቀነስ የሚያስችል ሥራ በመሥራት የራሴን አስተዋፅኦ ማበርከት ብችል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በአጠቃላይ ሥነ-ምግቡንም ብትል፣ የጤና ነክ ጉዳዮች እና ሌሎች የምርምር ሥራዎቼን ብትፈትሻቸው ሁሉ ነገሬ ከእናቶችና ህፃናት ጤና ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እንደ አንድ ዜጋ ማድረግ የምችለውን ለማበርከት ትኩረቴን የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ አድርጌያለሁ ማለት ነው፡፡

ንጋት፡– ምን ያህል የምርምር ሥራዎችን ሰርተዋል? ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት እስከመሆን ደርሰዋል የሚል መረጃ አለና እሱን ቢነግሩን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እውነት ለመናገር ብዙ ሥራ ነው የሰራሁት፡፡ ነገር ግን በቁጥር ደረጃ አላውቀውም ማለት ይቻላል፡፡ ጥሩ ሰነድ የማደራጀት ሥራ ስለማንሰራ እንጂ እንደ አሁኑ ትውልድ እያንዳንዷን ነገር ብናደራጅ በርካታ መሆኑን ማሳየት ይቻላል። የአሁኑ ትውልድ ሰነድ ማደራጀት ላይ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ (ሳቅ…)፡፡ እኔን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎች ሥራቸውን በሚገባ በማደራጀት መሰነድ ብንችል በርካታ ሥራዎችን እንደሰራን ያሳያል። ነገር ግን ይህ ብቻውን ለውጥ ስለማያመጣ የሌሎችንም ድጋፍና ቅንጅት ይጠይቃል፡፡

የእናቶችና ሕፃናትን ጤና በተመለከተ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሰርተናል፡፡ እንደው በቁጥር አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እያልኩ ባላስቀምጠውም ትኩረቴን እዛ ላይ አድርጌ በርካታ የምርምር ሥራዎች በመሥራት ለሚመለከታቸው አካላት የሥራ ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡

ለምሳሌ የወጣቶችን ጤና በተመለከተ እኔ ሀገራዊ የቴክኒካል ኮሚቴ አባል ሆኜ የሚቀረፁ ስትራቴጂዎች ላይ በመሳተፍ በምርምር ሥራዎች ያገኘናቸውን እውቀቶችና ግኝቶች መነሻ ያደረገ ሀሳብ በመሥጠት የበኩሌን አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ፡፡

እንግዲህ እዛ እንድሳተፍ ያደረገኝ በምርምር ሥራ ያገኘሁት ነገር ስለሆነ፤ ስራዎቼ ለሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ንጋት፡– ከሰሯቸው የምርምር ሥራዎች መካከል እንኳን ሰራሁት ብለው የሚያነሱት እና በተለየ ሁኔታ የሚያስታውሱት ካለ ቢነግሩን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ብዙ አለ፡፡ ነገር ግን በጣም የሚያስገርመኝና የማልረሳው አንድ ምርምር አለ፡፡ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር መጀመሪያ ሥራውን ስጀምር ብዙም ፍላጎት ኖሮኝ አልነበረም፡፡ የምርምር ሥራው ትኩረት ‹‹የፍል ውሃ የማዳን ሁኔታ እስከምን ነው? ሰዎችስ ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ለምን ይመርጡታል›› የሚለውን በማንሳት ጥቅም ባያገኙበት አይሄዱም የሚለውን መፈተሽና ማየት ነበር፡፡ 

በመጀመሪያ ከብዶን ነበር፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ብዙ ስላልተሰራበት መረጃ ማግኘት ከባድ ሆነ፡፡ ከዜሮ ስለጀመርን ብዙ አታግሎን ቢሆንም ሥራው ተጠናቆ ሲታተም የነበረው ተቀባይነት የሚያስገርም ነበር። በዚህም ምክንያት በርካታ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ጣቢያዎች ሳይቀር ተዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ ፍል ውሃዎች ኤጀንሲ ሳይቀር 60ኛ ዓመት ምስረታውን ሲያከብር በክብር ጋብዞኝ ጥናታዊ ጽሑፉን አቅርቤያለሁ፡፡

ሥራው ካሰብኩት በላይ ተቀባይነት ማግኘቱ ገና ያልተሰሩ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ይበልጥ ከማረጋገጡም በላይ ብዙም ፍላጎት ያላሳየሁበት ጥናት በዚህ ልክ ተቀባይነት ማግኘቱ እንኳንም ሰራሁት የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡ ወደፊት በደንብ እንዲሰራበት ለሚመለከታቸው አካላት ጭምር ባደጉት ሀገራት ያለውን ሕክምና በማሳየት በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ በማካተት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ጠቁመናል፡፡

ንጋት፡– ከሥርዓተ–ምግብ ጋር በተያያዘ ከሰሯቸው የምርምር ሥራዎች በመነሳት የተወሰነ ሃሳቦችን ቢያነሱልን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– የሚገርምህ አሁንም እሱ ላይ እየሰራን ነው፡፡ በጥናታችን ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ ያለውን የጤና እንክብካቤና የሥነ-ምግብ ሁኔታ የሚዳስስ ነው፡፡ አንድ እናት ከማርገዟ ጀምሮ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንዳለባት የሚያሳይ ሲሆን የምግብ ችግር የሚያስከትለውን ሁኔታ ነው የምናጠናው፡፡ ችግሩ እንደ ቀለበት ክብ ሰርቶ የሚጓዝ ሲሆን እናት ጥሩ ካልተመገበች ልጇ እንደሚጎዳ፣ ልጇ ደግሞ በቀጣይ ወደሌላው ልጅ እያለ ማህበረሰብን እንዴት እንደሚያካልል የሚያሳይ ነው፡፡

ይህንን ችግር ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ በማተኮር በሰርቶ ማሳያ የታገዘ የምርምር ሥራ እየሰራን ነው። ይህም ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ልጆች ላይ ያለውን ሁኔታ በማጥናት ለሚመለከታቸው አካላት እና እስከ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድረስ ሪፖርት በማድረግ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል እየተሰራ ነው፡፡ መፍትሄዎቹ ይታወቃሉ ግን አቅም ስለሚጠይቁ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም አሁን ላይ ጥሩ መሻሻሎች አሉ፡፡

ንጋት፡– በሀገራዊ ኮሚቴዎች ጭምር በመሳተፍ እየሰሩ ነውና፤ እየተሳተፉ ያሉባቸውን በማንሳት ጊዜዎትን እንዴት አበቃቅተው እንደሚጠቀሙ ቢነግሩን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እውነት ነው ብዙ ቦታ እሰራለሁ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሴት ተመራማሪዎች ማህበር ውስጥ ምክትል ሊቀመንበር ነኝ፡፡ በሌሎች ቦታዎችም እሳተፋለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ኃላፊነት አለብኝ፡፡

ጊዜ ለሁሉም እኩል ናት፤ ልዩነቱ አጠቃቀማችን ነው፡፡ የእኛ ሥራ ቀን ማታ፤ ቅዳሜና እሁድ ብሎ ነገር የለም፡፡ አንዳንዴ እኔ ራሴ ለነፍስ ነው፤ ለሥጋ የምሰራው እስክል ድረስ በሥራ እጠመዳለሁ፡፡ የምርምር ሥራ በራሱ ስለሚመስጥ ሳታስበው ብዙ ሰዓት እንድትሰራ ያስገድዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ለማንበብና ለመመራመር ረጅም ሰዓት ሥራ ላይ ልትሆን ትችላለህ፡፡

ይህም ማህበራዊ ሕይወትን በተመለከተ ብዙ ተሳትፎ እንዳይኖረን ያደርገናል፡፡ አሁን አሁን እንደውም በተወሰነ ደረጃ ከሰፈር ሰው ጋር በመገናኘት ነገሮችን ለማስተካከል እየሞከርኩ ነው እንጂ ሙሉ ጊዜዬን ሥራ ላይ ነው የማሳልፈው፡፡

ንጋት፡– ከእርስዎ ልምድ በመነሳት በብዙ መንገድ እየተዘናጋ ነው ለሚባለው ወጣት የጊዜ አጠቃቀምን በተመለከተ ምን ይመክራሉ?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እውነት ነው አሁን ላይ ብዙ የሚያዘናጉ ነገሮች አሉ፡፡ ዋናው ነገር ራስን መገደብ ነው፡፡ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ እኔ ለምሳሌ የብዙ ሰዎችን ጊዜ የሚበላውን መዝናኛ ቦታ መሄድ ጨምሮ ግብ የሌለው ቦታ መገኘት አልፈልግም፡፡

አሁን ባለን ጊዜ መሮጥ የምንችለውን ያህል መሮጥ እና መሥራት የምንችለውን ያህል መሥራትን ማስቀደም አለብን ብዬ አስባለሁ። ያንን ለማድረግ ጊዜው ፈታኝ ቢሆንም፤ ወጣቱም ሆነ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ቅድሚያ ለዓላማው በመሮጥ ግቡን ማሳካት አለበት፡፡

እውነት ነው የእኛ ሀገር የሥራ ባህል ደካማ ነው፤ እኔ ግን ሰው አየኝ አላየኝ ብዬ ሳይሆን መሥራት አቅቶኝ እስክወድቅ ነው መሥራት የምፈልገው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋልና ቅድሚያ ለሚፈልጉት ነገር መሥጠት አለባቸው ብዬ እመክራለሁ፡፡

ንጋት፡– አሁን ላይ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጊዜን ከመብላት ባለፈ የሕብረተሰብ ጤና ሥጋት እየሆነ ነው የሚል ሃሳብ ይነሳል፡፡ እርስዎ ዘርፉ ላይ ምርምር እንደሚሰራ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ሰው ሁልጊዜ ራሱን ሊገድብ አይችልም፡፡ እኛ ሀገር አንዳንዴ ቢላዋና ሥጋን አንድ ላይ አስቀምጠህ እንዳትበላ በሚል ለመከልከል እንደመሞከር ነው ያለው ሁኔታ፡፡ ሁሉንም ነገር አሳልፈህ ሰጥተኸው ራስህን ገድበህ ሥራህን ሥራ ማለት አይቻልም ብዬ አምናለሁ። በተቻለ መጠን መገደብ ቢቻል ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በተለይ ከእኛ ሀገር ባህል፣ ሀይማኖትና እሴት ጋር የማይመከሩ ሚዲያዎች አሉ፡፡ የልጆቻችንን አዕምሮ ጠቅልለው እየወሰዱ በመሆናቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቢገደቡ ደስተኛ ነኝ፡፡

እውነት ነው በዚህ መሃል ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው ራሳቸውን ለውጠው ለሌሎች መትረፍ የቻሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። አብዛኛው በሚጠፋው ወገን ነው ያለውና መገደቡ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ንጋት፡– ቆይታችን ደረቅ እንዳይል በመሃል ዘና የሚያደርግ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ፕሮፌሰርን ምን ያዝናናቸዋል ቢባል መልሳቸው ምን ይሆን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– (ረጅም ሳቅ…) እውነት ለመናገር ብዙ ጊዜ ብቻዬን መሆንን ነው የምመርጠው፡፡ መዝናናት እንበለው አላውቅም፡፡ ግን የውስጥ ሰላምን ስፈልግ ብቻዬን መሆን ነው የምፈልገው፡፡ መዝናናት ይሄ ካልሆነ እኔ አላውቀውም ማለት ነው (ሳቅ…)፡፡

እንደ ሰዉ ወጥቼ ጥሩ የመዝናኛ ቦታዎችና ሆቴሎች ለመዝናናት ብዬ ሄጄ አላውቅም፡፡ በተለያየ የሥራ አጋጣሚ ከትንንሽ እስከ ትልልቅ የሚባሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች ጋር ተገኝቼ አውቃለሁ፤ ግን ሥራዬን ሰርቼ ነው የምመለሰው፡፡

እኔ ለመዝናናት በለው አልያም ውስጤን ሰላማዊ ማድረግ ስፈልግ ለምሳሌ የሥራ ጫና ሲበዛብኝ፤ ከስልክም ሆነ ከማንኛውም ነገር ራሴን በማራቅ ፀጥ ወዳለ ሥፍራ በማቅናት ውስጤን ማዳመጥ ነው የምፈልገው፡፡ የሚገርመው አንዳንዴ መፍትሄ ያጣሁላቸውንና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ያጋቡኝን ነገሮች ጨምሮ ብዙ የምርምር ሃሳቦችን መነሻ የማገኘው በእንደዚህ ያለ ጊዜ ነው፡፡  

ንጋት፡– ቤተሰባዊ ሕይወትዎን እናንሳ? በትዳር እና ልጆች የተባረኩ መሆንዎን ሰምተናል እስቲ ይንገሩን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– የትዳር ሕይወቴ የተመሰረተው ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ነው (ረጅም ሳቅ…)፡፡ አብረን እየተማርን ነው ያደግነው ማለት ይቻላል፡፡ ጎንደር ስመደብ እሱ (ባለቤቴ) ያለበት ቦታ ነበር የደረሰኝ፡፡ ስለዚህ ትምህርት እንደጨረስን ቀጥታ ወደ ትዳር ነው የገባነው፡፡ በዚህም ምክንያት በወቅቱ ከሁለታችን ቤተሰቦች ጀምሮ ብዙ ተቃውሞ በማስተናገድ ተፈትነናል፡፡ እኛ ዋናው ፍቅሩ ነው ብለን ተነስተን በ1989 ዓ.ም ትዳር መስርተን እስከ ዛሬ ድረስ ደስተኛ ሕይወት እየመራን ነው፡፡

እንደውም ለየትኛውም ሚዲያ ተናግሬ የማላውቀውንና ወደፊት በመጽሐፌ አካትተዋለሁ ያልኩትን ነገር ልንገርህ፡፡ እኔ ወደዚህች ምድር ከመጣሁበት አንዱ ዓላማ የፈጣሪን ሃሳብ ማሳካት በመሆኑ በመውለድ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ መውለድ አያደኸይም፤ መድረስ ከፈለክበት ቦታም አያስቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንንም በተግባር ማሳየት እፈልግ ስለነበር በተግባር አሳይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ የአራት ወንድ እና የስድስት ሴት በድምሩ የአሥር ልጆች እናት ነኝ፡፡

የመጀመሪያው ልጄ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፤ ሁለተኛው በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ማስተርሱንም በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ጨርሷል፤ ሦስተኛውም ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በውሃ ምህንድስና ተመርቋል፡፡ አራተኛዋ ልጄም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሥነ-ምግብ ሳይንስ (ፉድ ሳይንስ ኤንድ ኒውትሪሽን) ተመርቃ አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ (የማስተርስ) ትምህርቷን እየተከታተለች ነው፡፡ ሌላኛው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ተማሪ ነው፤ የእሱ ተከታዩም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተማረች ነው፡፡ የእነሱ ተከታይም ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ናት(ረጅም ሳቅ…)፡፡

ይህ ሰፊ በመሆኑ በቀጣይ እንዳልኩህ በመጽሐፍ መልክ ጽፌው እኔ የማላምንባቸውን አንዳንድ አስተሳሰቦች እና ጽንሰ ሃሳቦችን ጭምር ትክክል አለመሆናቸውን ማሳየት እፈልጋለሁ። እኛ ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት ሰዎች እንደመሆናችን ያለውን እውነታ ከመካድ ይልቅ ያለንን በማወቅ ብንኖር የተደረገልን ነገር ብዙ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እኔ በግሌ እግዚአብሔር በልጆች በመባረክ ብዙ ነገር አድርጎልኛል ብዬ አምናለሁ፡፡

ንጋት፡– በዚህ ሁሉ የስኬት ጉዞዎ መቼም የትዳር አጋርዎ ድጋፍ ይኖራል እና ተሞክሯችሁን ቢያካፍሉን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– በሚገርም ሁኔታ ይደግፈኝ ነበር፡፤ የሚገርምህ ሳይነጋገሩ የሚግባቡ ዓይነት ሰዎች ነን፡፡ እኔ አልያም እሱ ሳናወራ አንዳችን የሌላችንን ፍላጎት እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እኔ የሆነ ነገር መሥራት ስፈልግ አልያም ስማር እሱ ክፍተት እንዳይፈጠር ይዘጋል፡፡ እኔም በተመሳሳይ እሱ ሳይኖር ሲቀር በመሸፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ የእኔ ስኬት መሠረቱ የቤተሰቡ ደህንነት ነው ብዬ ነው የማስበሰው፡፡ ሰላማዊ የሆነ ቤተሰብ ስለሆነ ያለኝ እና ባለቤቴም ቀና በመሆኑ ነው እዚህ የደረስኩትና ትልቁን ምስጋና መውሰድ ያለበት እሱ ነው፡፡ እኔ በተለያየ ጊዜ ለትምህርት ስሄድ እሱ ልጆችን ከማሳደግ ጀምሮ ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ያግዛል፤ እሱ ሲሄድ ደግሞ እኔ ሸፍናለሁ፤ በዚህ መልክ ነው ተደጋግፈን ለስኬት የበቃነው፡፡

ንጋት፡– ከእርስዎ ልምድ በመነሳት ለሴቶች በተለየ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ቢያነሱልን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እኔ እንደውም ባልወልድ ኖሮ ጠንካራ አልሆንም ነበር ብዬ ነው የማምነው፡፡ በመውለዴ ለልጆቼ የተሻለ ነገር ማሳየት እንዳለብኝ ነው ሁልጊዜ የማስበው፡፡ እኔ ሰርቶ በማሰራት ስለማምን ልጆቼ እንደዛ እንዲሆኑ ነው የማደርገው፡፡ አይቻልም የሚባል እሳቤ እንዳይኖር አድርጌ ስለሆነ የማሳድጋቸው የሚያቅታቸው ነገር እንደሌለ ያምናሉ፡፡

አንድም ቀን ቁጭ በል ላስጠናህ፤ የቤት ሥራ ሥሩ ብዬ ተቆጥቼ አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር ይመሰገን የልጆቹም አዕምሮ ጥሩ ነው፡፡ እርስ በእርስ ይደጋገፋሉ ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንዲያድጉ ያደረኩበት መንገድ ስለሆነ ሁሉም በራሱ መንገድ ውጤታማ እየሆነ ነው፡፡ ለዛ ነው ልጆቼ የጥንካሬዬ ምክንያቶች ናቸው ብዬ የማምነው። ስለበዛን ይህ ነገር አልተሟላልኝም፤ ቀርቶብኛል ብለው እንዲያስቡ አልፈልግም፡፡ ስለዚህ ለእነሱ የተሻለ ነገር ማድረግ ስላለብኝ ሁልጊዜ ራሴን ለማሻሻል እሰራለሁ፡፡ ያ ደግሞ ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት አብቅቶኛል፡፡

ንጋት፡– እንደ ሕብረተሰብ ጤና ተመራማሪነትዎም ሆነ ስኬታማ ቤተሰብ እንዳለው ባለተሞክሮ ለሕብረተሰቡ ያለዎት መልዕክት ምን ይሆን?

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ልጆችን ግቡና አጥኑ በማለት ሳይሆን ወላጆች እነሱም በማንበብ አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ ወላጆች ሶሻል ሚዲያ እና ቴሌቪዥን ቁጭ ብለው እያዩ ልጆችን አትዩ ማለት አይቻልም። ሰው የሚናገረው እንዲደመጥ ብቻ ሳይሆን በተግባር በማሳየት ነው ማስተማር የሚቻለው፡፡ ስህተት ሲሰሩም ኃላፊነት በመውሰድ ጉዳቱን ቁጭ ብሎ እንደ ቤተሰብ በመነጋገር በቀጣይ እንዳይደገም መመካከር ይጠቅማል፡፡

አንድ ነገር ላይ እንደ ቤተሰብ ተነጋግሮ ጥቅሙንና ጉዳቱን በመፈተሽ በጋራ መወሰን ዘላቂ የሆነ ጥቅም ያስገኛል፡፡ እኛ ለምሳሌ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖን የተቋቋምነው እንደ ቤተሰብ ተነጋግረን የጋራ ህግ በማውጣታችን ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚበዛ ከሆነ እያንዳንዱን ነገር በመፈተሽ ለስኬት የሚጠቅመውን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

በተለይ እስከተወሰነ የዕድሜ ገደብ ድረስ ልጆችን በተግባር በማሳየት አርዓያ መሆን ከወላጆች ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ የቤት ሰራተኛ በመቅጠር ስለማላምን ራሴ ነኝ በመሥራት ልጆች ሥራ እንዲለምዱ የማደርገው፡፡ ጊዜ ይወስዳል አዎ፤ ነገር ግን ጊዜዬን አበቃቅቼ ሥራ በማስለመድ ልጆቼ ነገ እንዳይቸገሩ ማድረግ ስላለብኝ በዚህ መርህ ነው ያሳደኳቸው፡፡ የሥራ ጫና ሲኖር እንኳን ሠራተኛ ቢቀጠርም በፕሮግራም ሁሉም ገብቶ በማገዝ ነው የሚሰሩት፡፡ ይህም ሙያ ከመልመድ ባለፈ ኃላፊነት የሚወስዱ ጠንካራ ልጆች እንዲኖሩኝ አድርጓል፡፡

ንጋት፡– በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥዎ እና ቆይታችንን እናጠናቅቅ፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– ለስኬታማ ቤተሰብ መሰረቱ ባልና ሚስት በመሆናቸው ሁለቱ በመግባባት ልጆችን ማሳደግ አለባቸው። እኔ ሳድግ ያየሁትን ቤተሰብ አርዓያ አድርጌ ስለተገበርኩት እና እግዚአብሔር አግዞኝ ውጤታማ ሆኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ችግሮች እንኳን ቢኖሩ ከልጆች ፊት ዞር ብለን በመነጋገር ነው የምንፈታው፡፡ ይህም ጤናማ ቤተሰብ እንዲኖር አድርጓል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ባለቤቴን ስለሁሉም ድጋፉ እና ማበረታታቱ ማመስገን እፈልጋለሁ። ልጆቼ፤ የሀይማኖት መምህሬ እና አባቴ የሆኑትን መምህር ተስፋዬ ሸዋዬ ለማይታክት ምክርና ድጋፋቸው ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ 

በቀጣይ የጀመርኳቸውን ሥራዎች በማጠናከር በተለይም ሴት ልጆች ላይ በመሥራት የራሴን አሻራ ማኖር እሞክራለሁ፡፡ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች በምንቀሳቀስበት ወቅት በብዙ ወንዶች መሃል ብቻዬን ስገኝ እውነት ሌሎች ሴቶች የሉም ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ብቸኛዋ ፕሮፌሰር እየተባልኩ መጠራቴን ራሱ አልወደውም፤ ምቾትም አይሰጠኝም፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲቀየር የራሴን አስተዋፅኦ በማድረግ ሕዝብ የሰጠኝን አደራ ጭምር ለመወጣት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠኝን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ዕድገት ተከትሎ መላው ሕዝብ ላሳየኝ ክብርና ድጋፍ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ይህ በቀጣይ ይበልጥ እንድሰራ የሚያደርግ የአደራ መልዕክት ጭምር በመሆኑ ጠንክሬ ለመሥራት እሞክራለሁ፡፡

ንጋት፡– ለሰጡን ጊዜ እና ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም በድጋሚ አመሠግናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር አቻምየለሽ፡– እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሠግናለሁ፡፡ ሰላም ሁኑ፡፡