‎‎የቡናን ጥራት በመጠበቅ  ተጠቃሚ  ለመሆን  እየሰሩ መሆናቸውን  ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ

‎‎የቡናን ጥራት በመጠበቅ  ተጠቃሚ  ለመሆን  እየሰሩ መሆናቸውን  ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ

የቡናን ጥራት በመጠበቅ ተጠቃሚ  ለመሆን  እየሰሩ መሆናቸውን በኮቾሬ ወረዳ ያነጋገርናቸው  ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

‎‎የቡና ጥራትን ለማስጠበቅና  ህገ ወጥነትን  ለመከላከል  እየሰራ መሆኑን  የኮቾሬ  ወረዳ  ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

‎በቀለ በርሱ፣ በዓሉ ፈይሳ እና ሌሎች ያነጋገርናቸው አርሶአደሮች እንዳሉት፤ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የዝናብ መቆራረጥ ስለነበር  ምርት የቀነሰበት  ሁኔታ እንዳለ አንስተው፤ አሁን  የደረሰውን  ቡና በጥራት  ለቅመው  ተጠቃሚ  ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

‎በኮቾሬ ወረዳ  የጎለልቻ ቀበሌ  የሰብል  ባለሙያ  የሆኑት አቶ ደበላሽ አሰፋ  አርሶአደሮች  የቀላ  ቡና ብቻ ለቅመው በተዘጋጀው ቦታ እንዲያደርቁና የቡናን ጥራት  እንዲያስጠብቁ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

‎‎የኮቾሬ  ወረዳ  ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ክጴ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው  ዓመት  በወረዳው 21 ሺህ 480  ቶን  እሸት ቡና ለመሰብሰብ  አቅደው ወደ  ሥራ  መግባታቸውን  ተናግረዋል።

‎‎አያይዘውም በበጀት  ዓመቱ 3 ሺህ 733 ቶን የታጠበ እሸት ቡና እና  2 ሺህ 714 ቶን ደረቅ ቡና  በመሰብሰብ 6 ሺህ 447 ቶን ጥራቱን የጠበቀ  ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ  ዕቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል።

‎‎ለዚህም በወረዳው ካሉ 55 የቡና ኢንዱስትሪዎች 49 የሚሆኑት ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን እና ሃያ ወደ ሥራ መግባታቸውን አቶ አዲሱ ገልፀው፤ ቀሪዎቹም በሂደት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

‎‎የቡና  ጥራትን ከሚያበላሹ ነገሮች መካከል ህገ ወጥ  የቡና  ግብይትና በለቀማ ወቅት  የሚስተዋሉ የጥንቃቄ  ጉድለቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት  የቡና  ግብረ ሃይል አቋቁመው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራና ህገ ወጥነትን የመከላከል  ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን  ኃላፊው አብራርተዋል።

‎ዘጋቢ: ቦጋለ ሉሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

‎

‎