የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚዲያ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚዲያ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዲቨሎፕመንት (ECCD) የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለመንግስትና ለግል ሚዲያ ባለሙያዎች በአካል ጉዳተኞች አካታችነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናዉን በንግግር ያስጀመሩት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ አቦ እንደገለጹት፤ ጽሕፈት ቤቱ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች ያለው የተሳሳተ አመለካከት አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉን የተናገሩት ኃላፊው፤ የሚዲያ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ የዜናና ፕሮግራም እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች በሚለቁት የይዘት ስራዎች ለበርካቶች ግንዛቤ መስጠት የሚችሉ በመሆናቸው ይህንን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች እንደሌሎች ጉዳት አልባ ግለሰቦች የስራ እድል የማግኘት እና በማንኛውም ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸው በአለም አቀፍ እና በሀገሪቱ ህግ የተደነገገ በመሆኑ ይህንን መብታቸውን እንዲጠቀሙ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፕሮጀክቱ የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኦፊሰር የሆኑት ወይዘሮ ኤዶምገነት አዳነ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የተሰሩ  ስራዎች ህብረተሰቡ እንዲያውቅ እና ውጤታማ መሆን እንዲቻል የሚዲያ ተቋማት በዘገባ ስራዎች ሊያግዙ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች የይዘት ስራዎችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡን እያዝናኑ ስለ ጉዳዩ የማስተማር ስራን  እየሰሩ መሆናቸውንና በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ስልጠናውን የሰጡት በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የትምህርትና ስነ-ሰብ ኮሌጅ መምህር ዘላለም ታደለ እንዳሉት፤ ህንፃዎች፣ መንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም ሲገነቡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት በማስታወስ፤ የሚዲያ ተቋማትና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ስለ አካል ጉዳተኞች መብትና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ማድረግ ስለሚገባቸው ግዴታዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ አለባቸው ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎችም በቀጣይ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ከዚህ ቀደም  ከሚሰሩት በበለጠ ሁኔታ በመስራት ለህብረተሰቡ ስለ አካል ጉዳተኝነትና አካታችነት እንዲሁም  ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ቲክቶከሮች ተሳትፈዋል።

 ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና  ጣቢያችን