የመጨረሻው ስንብት

የመጨረሻው ስንብት

በፈረኦን ደበበ

ወቅታዊ ፖለቲካ ልክ እንደ አውሎነፋሱ ሲዘወር ከርሟል፡፡ ብዙዎችን ሙሉ ለሙሉ ከመንበራቸው ሲያስነሳ ጥቂቶቹን ነቅንቋል፡፡ ትንሽ እንቆይ ያሉ ለዘብተኞችን ደግሞ ሰሞኑን መግቢያ መውጫ አሳጥቷል፡፡

በባህሪው ዓለም አቀፋዊ ሆኖ በዋናነት አደጉ በተባሉ ሀገራት የተቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ጸረ-ህዝብ ተብለው የተጣሉ ቀኝ አክራሪዎችን ከጉድጓድ አውጥቶ ሲያነግሳቸው፤ የዚህኛውና የዚያኛውን ሀሳብ እየተቀበሉ ሥልጣናቸውን ለማራዘም የቋመጡ መሀል ሠፋሪዎችን ደግሞ እያዋረደ መገስገሱን ቀጥሏል፡፡

አዎን ካለፈው ዓመት ወዲህ የታየውን እንኳን ብንወስድ በእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን የመጡ የፖለቲካዊ ለውጦች ጠንካራ መንግሥትን እንጂ አድርባይነት ቦታ እንደሌለው አሳይቷል፡፡ ዓላማ፣ ጽናትና ረጅም እይታ እንጂ በጊዜያዊ ድሎች እየተኮፈሱ የተቀመጡትንም እንደ ጉም እያበነናቸው ይገኛል፡፡

የህዝባዊነት ዋና መለኪያው ሀገር መውደድ እንደሆነ ያሳየው እንቅስቃሴ፤ እንደ ጆ ባይደን ያሉና የሀገርን ጥቅም ለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡትን ሲያዋርድ አንድም መሣሪያ ሳይተኩሱና ሥልጣንን ገና ከመረከባቸው በፊት ሥራዎችን የጨረሱት እነ ዶናልድ ትራምፕና አሎን መስክን ፈጥሯል፡፡

የዛሬው ጽሑፌ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩት ጀስቲን ትሩዶ ዕጣ ፈንታ ላይ ሲያጠነጥን የደረሰባቸው ውጣውረድ ደግሞ በተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መለኮሱ ዓለም በምን ዓይነት የርዕዮተ-ዓለም ጦርነት እንደገባች ያሳያል፡፡

“አሜሪካ ትቅደም” የሚለውን የዶናልድ ትራምፕ መፈክር እውነትም ፍትሀዊ አድርገን መውሰድ እንችላለን የሚያስብል እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በዓለም ዙሪያ ከገባችበት ግጭት የሚያወጣትና በዚህ ምክንያት ህዝባቸውም መስክሮ ዳግም ወደ ሥልጣን የሚመጡበትን መንገድ ከፍቷል፡፡ በማይታመን ሁኔታ አጎራባች ሀገራትን እና መሬታቸውን ለመቆጣጠር እንዲከጅሉም አነሳስቷቸዋል፡፡

አጎራባች በሆኑት ካናዳ እና ሜክስኮ ምክንያት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል እያሉ 25 በመቶ የቀረጥ ኮታ የወሰኑት ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ፤ ከበስተደቡብ በኩል ካለችው ፓናማ ጋርም የቃላት ልውውጥ አድርገው ነበር፤ “እምንት በማይሆን” ምክንያት የወደብ ኪራይ ትጠይቃለች በማለት፡፡

ውዝግቡን ለመፍታት እያሉ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ መኖሪያ ቤታቸው መጥተው ሲያናግሯቸውም ፊት ከመስጠት ይልቅ “እርሶ የእኛ ግዛት አስተዳዳሪ ነዎት” እያሉ የተሳለቁባቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት፤ በአሁኑ ሰዓት ቀጥሎ ያለችው ግሪንላንድ ደሴትንም ወደ ሀገራቸው ለመጠቅለል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

እነዚህ ጥረቶች ሀገራችን የባህር በር ለማግኘት አሁን እያደረገች ካለው ጥረት ጋር መመሳሰላቸው ተስፋ ሲፈጥር፤ በካናዳ መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር ለ9 ዓመታት የመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡

አዎን ጀስቲን ትሩዶ ወደ ተሰናባቾቹ ጎራ ተቀላቅለዋል፡፡ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቁልፍ አጋር በመሆን ከሀገራቸው ህዝብ ይልቅ ለዩክሬን ጦርነት ባደረጉት ድጋፍ ምክንያት ተቀጥተዋል፡፡ ካሁን በፊት ከሀገራቸው ፓርላማ ድጋፍ እያገኙ ሥልጣናቸውን ያቆዩበት ዝቅተኛ የመተማመኛ ድምጽ ሁሉ በማጣት፡፡

አልጀዚራ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው ከሆነ የሀገሪቱ ለዘብተኛ ፓርቲ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ. በ2019 እና በ2021 የተካሄዱ ምርጫዎችን በማሸነፍ መርተዋል፤ ምንም እንኳን በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ የህዝብ ተቃውሞዎች ምክንያት ሠላማዊ ነው የሚባል ጊዜ ባያሳልፉም፡፡

ፓርቲውን በመወከል እ.ኤ.አ. በ2008 ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቱ የህግ አውጪ ምክር ቤት አባል በመሆን የተመረጡና ጠቃሚ የሚባሉ የህግ ማሻሻያዎችን ሁሉ እንዳደረጉ ሲነገር ከእነዚህ መካከል የአየር ንብረት ለውጡን መቀነስ ያስችላል የተባለው የካርቦን ቀረጥ ህግ እና ከአሜሪካ ጋር የተፈራረሙት የንግድ ህግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በቅርቡ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ያጋጠማቸውን ያህል መተማመኛ ድምጹን እንዳያጡ የሰጉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ከራሳቸው ፓርቲ አባላት ሁሉ በደረሰው ጫና ምክንያት ሥልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡ ፓርቲያቸው ተሰባስቦ የሚተካቸውን ሰው ሲመርጥ ለመልቀቅም ቃል ገብተዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ በቆዳ ስፋት ትልቅ የሆነችውን ሀገር ለመምራት ከአባታቸው ፒር ትሩዱ ህልፈት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የፖለቲካ እህል ውኃቸው ሰሞኑን እንዳለቀ ተረጋግጧል፡፡ መራጩ ህዝብም በመኖሪያ ቤት እጥረት፣ በዕቃዎች ዋጋ ግሽበት፣ በመንግሥት ዕዳ፣ በጤና አገልግሎትና ሌሎች እጥረቶች ምክንያት ምሬታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የሦስት ልጆች አባት የሆኑት የ56 ዓመት ጎልማሳው ጠቅላይ ሚንስትር፤ በቅርቡ ከባለቤታቸው ጋር የገቡበት ንትሪክ ሁሉ ሳይበግራቸው እስከ ሥልጣን ጊዜያቸው ማብቂያ ለመቀጠል ያለሙት ህልም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የፖለቲካ ባላንጣቸው ከሆኑት ዶናልድ ትራምፕ እና ኤለን መስክ ወዳሴ የተቸረው ከሥልጣን የመልቀቅ ሀሳባቸው በሥልጣን ዘመናቸው አከናወንኩ ላሏቸው ህገ-ወጥ ተግባራትም መቀጣጫ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕጽና ግለሰቦች በሀኪም በተደገፈ መልክ እራሳቸውን ለማጥፋት የሚያቀርቡትን ጥያቄ ህጋዊ ማድረጋቸው ነቀፌታን በማስከተሉ፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ እራስን የማጥፋትና ህይወታቸውን የማጣት አደጋ ለደረሰባቸው ነባር የህብረተሰብ ክፍሎች በአደባባይ ፍትህን ለመስጠት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ሲሆን ይህንንም እሳቸው ለየት ባለ ሁኔታ ገልጸዋል ከፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ጋር በማገናኘት፡፡

“እ.ኤ.አ. በ2015 የተመረጥነው መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ነገር ለማምጣትና ይህንንም በተጨባጭ አድርገናል ካሉ በኋላ፤ የግብር ጫናቸውንም ቀንሰን ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ችለናል” ብለዋል፤ ምጣኔ ሀብቱም ለሁሉም እንጂ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ አልጠቀመም” ሲሉ እንደ ትራምፕና መስክ ያሉ ባለሀብቶችን በነገር እየሸነቆጡ፡፡

አሜሪካና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የተፈጠረውን የለውጥ ማዕበል መቋቋም የተሳናቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ም/ጠቅላይ ሚንስትርና የገንዘብ ሚንስትራቸው ክሪስቲያ ፍሪላንድን በፈቃደኝነት መልቀቅ ምክንያት ከካቢኔያቸው አጥተዋል፡፡ ይህም እሳቸውን ለመተካት በሚፈልጉ የፓርቲያቸው አባላት መካከል ፉክክርን ሲያስነሳ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ላይ እያሉ ምርጫው ከተደረገ ችግር እንደሚገጥመው የሰጋው የሊበራል ፓርቲ እነ ማርክ ካርኔ፣ ፈራንኮስ ፈሊፕ ቻምፓኔ፣ ክሪስቲ ፈሪላንድ፣ ሜላኒ ጆሊ እና ዶሚኒክ ለ ብላንክ የተባሉ ዕጩዎችን አቅርቧል፤ ምንም እንኳን ፓርቲው የሚያካሄደው የተራዘመ የምክክር ሥርዓት ምርጫውን ያጓትታል ተብሎ ቢሰጋም፡፡

በቀጣዩ ምርጫ የሊበራል ፓርቲን ያሸንፋሉ ተብሎ የሚነገርላቸው የተቃዋሚው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ዕጩ ፒር ፖሊቭርም ትርዶን ደካማ እያሉ በመተቸት እንደ ዶናልድ ትራምፕ “ካናዳ ትቅደም” የሚል ፖሊሲያቸውንም እያጧጦፉ ይገኛሉ፡፡