“ችግርን በፀጋ መቀበል ይገባል”
በደረሰ አስፋው
የዛሬው የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን 8ኛ ክፍል እያለ የደረሰበት የመኪና አደጋ ቀኝ እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት ወጣት መምህር ነው፡፡ በልጅነቱ የደረሰበትን ጉዳት ተከትሎ ያስተናገዳቸው ችግሮች ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ ህይወትን በአዲስ መልክ እንዲመለከት አድርጎታል፡፡
ክቡር የሆነውን የመምህርነት ሙያ ተቀላቅሎ ዛሬ ላይ ለሌሎችም አርአያ የሆነ ተግባር እያከናወነ ነው፡፡ ጥንካሬውም በየዓመቱ ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ አልፎም በማህበራዊ ዘርፍ በመሰማራት አካል ጉዳተኞች የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማንቃት፣ ድጋፎችን በማሰባሰብ የዊልቸርና ክራንች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ሌላው ተጠቃሽ ተግባሩ እንደሆነ ሀሳቡን አጋርቶናል።
መምህር ኤልሳ ኤሊያስ በሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን በንሳ ዳዬ ወረዳ ዳዬ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ የ1ኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳዬ ከተማ ሶዳዋሬ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ከ5ኛ እስከ 8ኛ በዳዬ ከተማ ሻንታጉልባ ሁለተኛ ሳይክል ት/ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ደግሞ ቀቤና ጋጣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው፡፡
የ12ኛ ክፍል ውጤቱ ግን ወደ ዩኒቨርስቲ የሚያስገባው አልሆነም፡፡ በዚህም ምክንያት ወረዳው ባወጣው የመምህርነት ምልመላ ዕድሉን አግኝቶ ሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገባ፡፡ የሚሠጠውን የመምህርነት ሙያ ስልጠና ለ3 ዓመታት ተከታትሎ በኬሚስትሪ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ አሁን ላይ ቀድሞ ሲማርበት በነበረው ትምህርት ቤት ምደባ አግኝቶ እያስተማረ ይገኛል፡፡ በስራ ላይ እያለ በሀዋሣ ዩኒቨርሲቲ በንሣ ዳዬ ካምፖስ በሂሳብ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን በዚህ ዓመት መጨረሻ ይመረቃል፡፡
“ከጉዳት አልባ ሰዎች አንሼ መታየትን አልሻም” የሚለው መምህር ኤልሳ ትምህርቱን ለመቀጠልም ይሄው አስተሳሰቡ እንዳነሳሳው ነው የተናገረው፡፡ በዲፕሎማ በተመረቀ በ17 ቀኑ የዲግሪ ትምህርቱን እንደጀመረ ገልጾ 3 ነጥብ 8 በማምጣት ነው የተመረቀው፡፡
አካል ጉዳተኛ ስለሆነበት አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሳል፡- የ1ኛው ወሰነ ትምህርት ተገባዶ ትምህርት ቤት በተዘጋበት ወቅት ለእረፍት ከወላጅ አባቱ ጋር ዘመድ ለመጠየቅ በመኪና ይጓዛሉ፡፡ በጉዞ ላይ እያሉ ድንገት የመኪና መገልበጥ አደጋ አጋጠማቸው፡፡ ከተሳፈሩት አብዛኛዎቹ ህይወታቸውን አጡ፡፡ ወላጅ አባቱ በህይወት ቢተርፉም እሱ ግን በእጁ ላይ ጉዳት አጋጠመው፡፡ ጉዳት ካጋጠመው 15 ዓመታትን ማሳለፉን ነው የተናገረው፡፡
አካል ጉዳተኝነትና መምህርነት አልፈተነህም የሚል ጥያቄ አነሳሁለት፡-
“ከጉዳት አልባዎች ጋር ሳስተምር ለ3 ተከታታይ ዓመታት ተሸልሜያለሁ፡፡ ከ150 መምህራን መካከል በመማር ማስተማሩ ስራ ሞዴል መምህር ተብዬ ነው የተሸለምኩት፡፡ ይህ ዕውቅናና ሽልማት ለስራዬ የሰጠሁትን ክብር ያሳያል፡፡ አካል ጉዳቴን ማሳየት አልፈልግም፡፡ ይቻላል ከተባለ ይቻላል። የሂሳብ ትምህርት ወድጄው የገባሁበት በመሆኑ ለውጤታማነት አግዞኛል”፡፡ ዘንድሮ ማስተማር ከጀመረ 4ኛ ዓመቱ ነው፡፡
አሁን ላይ ጉዳት ቢደርስበትም ባለው ዕውቀት ህዝቡን ማገልገሉ ደስታ አጎናፅፎታል፡፡ ትምህርቱም ቢሆን በዚህ የሚገታ ሳይሆን እስከ ዶክትሬት እንደሚቀጥል ነው የተናገረው፡፡
መምህር ኤልሳ በምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ከማስተማሩ ስራ ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በበንሳ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያም በመገኘት አካል ጉዳተኞች ከተደበቁበት ጓዳ ወጥተው እራሳቸውን ለተሻለ ህይወት እንዲያበቁ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶችንና መጣጥፎችን ያቀርባል፡፡
በዚህም በርካታ አካል ጉዳተኞች ከጓዳ ወጥተው ተምረው እንዲለወጡ ማድረግ አስችሏል፡፡ እርግማን ነው በሚል ከተደበቀበት ወጥቶ በሙዚቃና በትወና አንቱ የተባለ ወጣት የመድረክ ሰው ማፍራትም ችሏል፡፡ ወጣቱ አይነ ስውር ቢሆንም አይነ ስውርነት ከመስራት እንደማያግድ በተግባር ያሳየ መሆኑም ለሌሎች አካል ጉዳተኞች መነቃቃትን እንደፈጠረ ተናግሯል፡፡
ወጣቱ መምህር በማህበራዊ ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የአካል ጉዳተኞች ህይወት እንዲለወጥ ችግራቸውን ይጋራል፡፡ በጎ አድራጊ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶችንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር በርካታ ሰብአዊ ድጋፎችን እያበረከተ ይገኛል፡፡ ገንዘብ በማሰባሰብ እና የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት መማር ያልቻሉ እንዲማሩ አድርጓል፡፡ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀሻ ዊልቸርና ክራንች አግኝተው አካል ጉዳተኞች ትምህርታቸውን እንዲማሩ አድርጓል፡፡ በዚህም መንፈሳዊ እርካታ ይሰማኛል በማለት ስሜቱን ይገልጻል፡፡
ከአካል ጉዳት አስተሳሰብ ለመውጣት ችግርን በፀጋ መቀበል ይገባል፤ ጉዳቱን መቀየር አልችልም ብሎ መውሰድ ይገባል የሚለው መ/ር ኤልሳ በስፖርቱ ዘርፍም ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው፡፡ በቀድሞው የደቡብ ክልል ፓራኦሎምፒክ ተሳትፎ በማድረግ ክልሉን የሜዳሊያ ባለቤት አድርጓል፡፡ አሰላ፣ ሀረር፣ አዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ እና ሀዋሳ ከተሞች የተወዳደረባቸው ናቸው፡፡ በአካል ጉዳተኞች በተካሄዱ ሀገር አቀፍ ውድድሮች በ100 እና 200 ሜትር ሩጫ ተወዳድሮ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ እንደነበርም ያነሳል፡፡
ዛሬ ላይ መምህር ኤልሳ በስፖርቱ ባይቀጥልም ወደ አሰልጣኝነት ዘርፍ ፊቱን አዙሮ ያለውን ልምድ ለውጤት ለማብቃት እየሰራ ነው፡፡ ከመምህርነት ሙያ ጎን ለጎን አካል ጉዳተኞችን በተለያዩ የስፖርት መስኮች በማሰልጠን ውጤታማ እንዲሆኑ ይሰራል፡፡ ክልሉን ወክለው የሚወዳደሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይተጋል፡፡ የሚያጋጥመውን የግብአት ችግር ለመቅረፍም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ እንዲሁም ግለሰቦችን በማስተባበር ድጋፍ ያሰባስባል። ከዚህ ጎን ለጎንም አካል ጉዳተኞች በህገ መንግስቱ የሰፈሩ ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ የማንቃት ስራ ይሰራል፡፡
“በ2006 ዓ.ም በስፖርት እንድሳተፍ ስጠየቅ የሚያፌዙብኝ ነበር የመሰለኝ፡፡ እንዴት አካል ጉዳተኛ ሆኜ ስፖርት እወዳደራለሁ በሚል፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችን ስመለከት አስተሳሰቤ ተለወጠ፡፡ ለመሳተፍ ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ተወዳዳሪ ለመሆን ተግቼ ክልሉ የሚያስጠራ ውጤት አመጣሁ፡፡ ባለፈው ዓመት ታንዛኒያ ላይ በተካሄደው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅተን ነበር። ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ብንቀርም ዝግጅታችንን ዛሬም ቀጥለናል፡፡ ዛሬ ላይ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ይቻላል በማለት በማሰለጥነው ስልጠና ውጤት እያየሁበት ነው፡፡ በርካቶችም ከተደበቁበት ጓዳ ወጥተው መሳተፍ እየቻሉ ነው”
በቅርቡ በሲዳማ ክልል በተካሄደው ሀገራዊ ምክክር አካል ጉዳተኞችን ወክሎ ተሳትፏል፡፡ በዚህ መድረክም አካል ጉዳተኞች ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲረጋገጥ በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን ነው የገለጸው፡፡ አካል ጉዳተኞች እድሉን ካገኙ መስራት ይችላሉ የሚለው መምህር ኤልሳ፤ እግር ጉዳት ካለው እጅ ይሰራል፣ እጅ ከሌለው በእግሩ ይሰራል ያለ ሲሆን በሌላ በኩል በርካታ አካል ጉዳተኞች የማየትና የመስማት ችግሮች ቢኖርባቸውም በበርካታ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ለሀገርና ለማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነው ያመላከተው፡፡
“ሰው ሆነን በመፈጠራችን የራሳችን ሰብአዊ መብት አለን፡፡ ከማንም ሰው ጋር እኩል ነን፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆነው በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ሀብት የፈጠሩ አሉ። ለሌሎች የስራ ዕድል የፈጠሩም አሉ፡፡ አስተሳሰባችን እንጂ አካል ጉዳተኛ መሆን ለመስራትና ለመለወጥ አያግድም፡፡ ስለዚህ በማህበረሰቡ ላይ ያለው ግንዛቤ ሊለወጥ ይገባል፡፡ አካል ጉዳተኞችም ከልመና አስተሳሰብ ወጥተው በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል” ሲል ነው መልዕክቱን ያስተላለፈው፡፡
More Stories
ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም…
ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተገለፀ
“ፓራ ቡላቻ”÷ ቀደምቱ የጋብቻ ስርዓት