ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በወቅቱ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በወቅቱ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በወቅቱ እንዲቀርቡላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጠየቁ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ለቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው ሽግግር የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ፖኬጆች ላይ በጂንካ ማዕከል ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

በላፉት ሦስት ቀናት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሰብል፣ በፍራፍሬና አትክልት፣ በእንስሳት ምርታማነት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በሌሎች የግብርና ፖኬጆች ስልጠናው ሲሰጥ ቆይቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በየአካባቢያቸው የጀመሩትን የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል አቅም እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ መሰል የግንዛቤ መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል።

ስልጠናውን የሰጡ አካላትም በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት ጤና እና ግብዓት አቅራቦት ዘርፍ ኃላፊና የጂንካ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር አድሱ ኢዮብ፤ በክልሉ አብዛኛው አካባቢ የተጀመሩ የምርት ስራዎችን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የገበያ ፍላጎቱን ለማርካት ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን አብዝቶ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ከቴክኖሎጂ በተጨማሪ በክልሉ ያሉ የውሃ ሀብቶችን አሟጦ በመጠቀም ማህበረሰቡን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅና ምርታማነትን ለማሳደግ በተዋረድ ያሉ የግብርና መዋቅሮች እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ የተለያዩ አካላት በድጋፍ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ጠብቆ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር አድሱ፤ መሰል ድጋፎችን በቀጣይ ክልሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን