በበጋ መስኖ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን በማልማት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን በዳውሮ ዞን ከጪ ወረዳ የከጪ ቱታ ቀበሌ አርሶ አደሮች ገለጹ

ከ1ሺህ በላይ ሄ/ር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ285ሺህ በላይ ኩ/ል ምርት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና አከባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።

የከጪ ወረዳ በተለያየ ምቹ አየር ፀባይ ያላት ወረዳ ሲትሆን በዘንድሮ በበጋ መስኖ ስራም የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አርሶ አደር ተስፋዬ ሀይሌ፣ ተሻለ ተስፋዬ እና ዱባለ ታደሰ በከጪ ቱታ ቀበሌ ዩኒ መስኖ በባህላዊ መንገድ ውሃ በመጥለፍ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን እና ፍራፍሬ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬ 0.25 ሄ/ር ጥቅል ጎመን፣ ቀይ ስር፣ ቆስጣ፣ ነጭ ሽንኩርትና ካሮት እንዲሁም በዚሁ አከባቢ ወደ 16 መደብ የሚጠጋ የቡና ችግኝ በማፍላት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀሲስ ተስፋዬ ታምራት የከጪ ቱታ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት አስተባባሪ ሲሆኑ፥ በቀበሌው በጋ መስኖ ስራ 185ሄ/ር መሬት በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከወረዳው F.T.C ተቋም ጋር በመሆን የአረም ቁጥጥርና ሌሎች የድጋፍና ክትትል ስራ በልዩ ትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውንና በቀጠይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

በከጪ ወረዳ ግብርና አከባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ም/ኃላፊና እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታምራት ሀዳሮ በበኩላቸው፥ በዘንድሮ በጋ መስኖ ስራ የተሻለ ምርት ለማግኘት ከሌላው ጊዜ በተለየ አቅደው በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በበጋ ስንዴ በተለይም ለእንሰት ምርት ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውን አመላክተዋል።

አቶ ታምራት አክለውም በወረዳው ከ1ሺህ 40 በላይ ሄ/ር መሬት በበጋ መስኖ፣ ጓሮ አትክልቶች እና ፍራፍሬ እንዲሁም በጋ ስንዴ ልማት ከ285ሺህ 240 ኩ/ል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የተሟላ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ የክትትል እና ቁጥጥር ስራ ከባለሙያዎች ጋር በማድረግ በዘንድሮ ምቹ አየር ፀባይ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ሰዓት ምርቶቹ የደረሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አፈወርቅ ኦሹ – ከዋካ ጣቢያችን